የእነ ጄነራል ጻድቃን ምክር ቤት ፌደራል መንግሥት በትግራይ ጉዳይ "ግዴታውን እንዲወጣ" የሚጠይቅ ሰልፍ ሊያካሂድ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ትግራይ ውስጥ የሚካሄደውን "ወታደራዊ አፈሳ" የሚቃወም እንዲሁም ፌደራል መንግሥት በክልሉ ጉዳይ "መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ" የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ።

በመዲናዋ መስቀል አደባባይ የሚካሄደውን ሰልፍ ያዘጋጀው ግንቦት ላይ የተቋቋመው "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት" እንደሆነ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሁለት ወር በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተው ይህ ምክር ቤት በትግራይ የክልላዊ መንግሥት ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ እና የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት እንደሚንቀሳቀስ ይገልጻል።

ምክር ቤቱ በውስጡ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተለዩ እና የተቃረኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ይዟል።

በምክር ቤቱ ሥር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ ነው።

ከህወሓት በተለዩ አመራሮች የተመሠረተው ሌላኛው ፓርቲ ወለዶ ትግራይ፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) እንዲሁም ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ተጠቃሽ ናቸው።

የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ሊቀ መንበር እና የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ከበደ እንደሚናገሩት ቅዳሜ ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም. ሊካሄድ የታቀደው ሰልፍ ሁለት ዋነኛ ዓላማዎች አሉት። በቀዳሚነት የጠቀሱት በክልሉ የሚካሄደውን "የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ" ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጧቸው መግለጫዎች በክልሉ የሚካሄደው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እንዲቆም መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከበደ "በትግራይ ያለው ኃይል ከሻዕቢያ እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመተባበር የትግራይ ተወላጆችን በየቀኑ እያፈሰ፣ እያፈነ ለሞት፣ ለስደት እያደረጋቸው ነው" ሲሉ ከስሰዋል። በተጨማሪም "የትግራይ ሕዝብን ለማፈን የወጣ አፋኝ አዋጅ አለ" ብለዋል።

የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው የጠቀሱት "የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የወጣ አዋጅ" ህወሓት ወደ ሥራ በመለሰው እና ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገ ምርጫ በተቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት የጸደቀ ነው።

ትግራይ ክልል ውስጥ "የወጣው ምንም ኮሽታ ማድረግ የማያስችል አዋጅ ነው" የሚሉት ከበደ፤ በዚህ አዋጅ ምክንያት ሕዝቡ "እየተሰቃየ፣ እየታፈነ፣ እየተገደለ፣ በግዳጅ የወታደራዊ አፈሳ እየተደረገበት" መሆኑን ያነሳሉ።

ኢሰመኮ እና ሂውማን ራይትስ ዎችም በመግለጫዎቻቸው ይህንን አዋጅ ኮንነዋል።

የክልሉ መንግሥት ግን ሕጉ ላይ "የማጠልሸት ዘመቻ" ተከፍቷል በሚል ያስተባብላል። በህወሓት በሚመራው መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አማኑኤል አሰፋ ሕጉ "የኅልውና አደጋ ውስጥ ያለን ሕዝብ ለማዳን ከሚደረገው ትግል አንጻር ነው" መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።

የቅዳሜው ሰልፍ ላይ እነዚህ ጉዳዮች "ለመኮነን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሰማት" መታቀዱን የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን ሁኔታውን "በዝምታ እየተመለከተ ነው" ላሉት የፌደራል መንግሥት ጥሪ እንደሚቀርብ ይናገራሉ።

"ይህንን እያየ የመንግሥት ዝምታ አግባብነት እንደሌለው፤ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ ለማድረግ ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ በሰልፉ የሚጠየቀው መንግሥታዊ ግዴታ ምን እንደሆነ ለሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ከበደ ጥያቄ አቅርቧል።

"መንግሥት ይህንን ኃይል ከቻለ በሰላማዊ መንገድ ትጥቁን ፈትቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርግ ማድረግ ይጠበቅበታል። ካልሆነም ግን አስፈላጊ የተባለውን ሁሉ አድርጎ ይህንን ሕዝብ ከዚህ ኃይል ነፃ የማውጣት እና ደኅንነቱን የመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ ይህንን ሰልፍ ለምን በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያሂድ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፤ "ጥሪ የምናደርግላቸው አካላት መንግሥትም ሆነ የዓለም አቀፍ ተቋማት እዚህ ስላሉ ነው" ሲሉ አንድ ምክንያት ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ "ጥሪ የሚደረግለት የኢትዮጵያ መንግሥት" መቀመጫ መሆኗን እንዲሁም "ከትግራይ ቀጥሎ [በርካታ] የትግራይ ተወላጅ ያለው" ከተማዋ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ሰልፍ በተመለከተ የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አወጣው የተባለ እና በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በኩል በተሠራጨ መግለጫ "የትግራይ ሕህዝብ እና የትግራይ ሕዝብ ወዳጆች እንዲያወግዙ" ጥሪ አቅርቧል።