ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ መሪው መገደል እና የፈጠረው ስጋት
በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለውን ፀረ አፍሪካውያን ስደተኞች እንቅስቃሴን ከሚመሩት መካከል አንዱ የሆነው አንዲሌ ሶምጋዳ ባልታወቀ ሁኔታ መገደሉ የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴውን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።
ሕገ ወጥ የተባሉ አፍሪካውያን ስደተኞች ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረሩ ባለፉት ወራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሶምጋዳ 'ማርች ኤንድ ማርች' የተባለውን እንቅስቃሴ ከሚመሩት መካከል እንዱ ነበር።
ጋውቴንግ በሚባለው አካባቢ የሚካሄዱ የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ መሪ ወይም አስተባባሪ እንደሆነ የሚነገረው ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት ከሚኖርበት ቤት አካባቢ ነበር በጥይት የተመታው። ግለሰቡ ከጥቃቱ በኋላ ሆስፒታል ለበርካታ ቀናት ከቆየ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።
አንዲሌ ሶምጋዳ ከሞተ በኋላ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ፀረ አፍሪካውያን ስደተኞች እንቅስቃሴን የሚመራው 'ማርች ኤንድ ማርች' እንቅስቃሴ ግድያውን ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ ሌሎች አባላቱም የግድያ ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው አሳውቋል። ነገር ግን ፖሊስ እስካሁን የግድያው ሰበብ ምን እንደሆነ የሰጠው ማረጋገጫ የለም።
ንቅናቄው በአባሉ ሞት በእጅጉ ማዘኑን እና የተጀመረው ፀረ ሕገወጥ አፍሪካውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ እና ተቃውሞ በመላዋ አገሪቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዝቷል።
ንቅናቄው ጥቃቱን በዝርፊያ እና በሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተሳተፉ ቡድኖች ከሚሰነዝሩት የሞት ማስፈራሪያ ጋር አያይዞታል። "ይህ ሁኔታ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ አላስፈላጊ ውጥረትን ስለሚፈጥር የሕግ አስከባሪ አካላት ይህንን ጉዳይ በጥልቀት እንዲመረምሩ እንጠይቃለን" ብሏል።
"በመላ አገሪቱ በተለይም በጋውቴንግ ግዛት ተቃውሞ በሚኖርበት እና አብዛኞቹ መደበኛ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች በሚገኙባቸው" የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደው ሰልፍ ተጠናክሮ እንሚቀጥል አስታውቋል። ይህ ደግሞ ባለፉት ወራት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የወደቁትን ስደተኞች ስጋት የበለጠ የሚያብሰው ይሆናል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በደቡብ አፍሪካ በተከሰቱት አፍሪካውያን የውጭ ዜጎች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች እና የስደኞች ተቃውሞዎች ምክንያት ውጥረት እየጨመረ መጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከመላዋ አገሪቱ ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን ደግፈው አደባባይ ወጥተው ነበር።
የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ መሪ የሆነው ግለሰብ መገደል በቡድኑ አባላት ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናትም ግድያውን እየመረመሩ መሆናቸውን አሳውቀዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳለው የአንዲሌ ሶምጋዳ ግድያን ለመመርመር የተለየ የባለሙያዎች ቡድንን አዋቅሯል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄደውን የፀረ ስደተኞች እንቅስቀሴን የሚያስተባብረው 'ማርች ኤንድ ማርች' መንግሥት በስደተኞቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት እያደረገ ሲሆን፣ ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስም በየሳምነቱ የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄድ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የቡድኑ አባላት ስደተኞች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሚከሰሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጨምሮ በርካቶች ባለፉት ጥቂት ወራት መገደላቸው ተዘግቧል።
እንቅስቃሴው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአፍሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ይፈልጋል። መንግሥት ደግሞ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ማስፈራሪያ እና ጥቃት አጥብቆ ተቃውሞታል።
የተደራጁት የፀረ ስደተኛ ቡድኑ አባላት በቡድን በመንቀሳቀስ ስደተኞች ከአገሪቱ እንዲወጡ ጫና እየፈጠሩ ሲሆን ማክሰኞ ዕለት የተወሰኑ የቡድኑ አባላት የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪ መስለው በመቅረብ የውጭ ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ ሲያስጠነቅቁ በፖሊስ ተይዘዋል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ያልተመዘገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች በሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ጫና ፈጥረዋል በሚል እና በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሥራ አጥነት እና የወንጀል መጠን አባብሰውታል በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ያሰማሉ።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደቡብ አፍሪካውያን በአገሪቱ ከ30 አስከ 40 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ለሚገመተው የሥራ አጦች ቁጥር እንዲሁም በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ተቋማት ላይ ለተፈጠረው ጫና አፍሪካውያን ስደተኞችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ የናይጄሪያ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ኦኬይ-ኡቼ ለቢቢሲ "በደቡብ አፍሪካ ያሉት ስደተኞች ከስምንት በመቶ ያልበለጠ ነው" በማለት በአገሪቱ ውስጥ ላለው ችግር ሁሉ ስደተኞችን እንደምክንያት ማቅረብ ትክክል አይደለም ይላሉ።
በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት እና ጥቃት መበርታቱን ተከትሎ የተለያዩ አገራት የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ አስወጥተዋል።
ባለፉት ሳምንታት ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ዚምባብዌ፣ ማላዊ፣ ጋና እና ሞዛምቢክ ለበርካታ ዓመታት በደቡብ አፍሪካ የኖሩ ዜጎቻቸውን ጨምሮ በደኅንነት ስጋት ምክንያት አገሪቱን ለቀው ለመውጣት የጠየቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው መልሰዋል።
ጫና የበዛበት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአገሪቱ ያሉትን ስደተኞች አያያዝ ለማስተካከል ዘመቻ ከከፈተ በኋላ ከ53,000 በላይ የውጭ ዜጎች ከአገር መባረራቸውን ወይንም እንዲወጡ መደረጋቸውን እና እነዚህም ከማላዊ፣ ከዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ የመጡ መሆናቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ ለተከታታይ ሳምንታት ጸረ ስደተኛ ሰልፎች ከተካሄዱ እንዲሁም አለመረጋጋት፣ ማስፈራራት እና ዘረፋ ከተፈጸመ በኋላ በአገሪቱ ያለ ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሚገኙ ስደተኞች ላይ ሰፊ የተባለ ዘመቻ እያካሄደች ትገኛለች።