ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ በኢቦላ የተያዙት ሁለተኛ ሰው መሞታቸው ተገለጸ
የመጀመሪያውን የኢቦላ ወረርሽኝ እየተቆጣጠረች ያለችው ኬንያ በኢቦላ ምክንያት ሁለተኛውን ሞት መዘገበች።
ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጡት የመጀመሪያው የኢቦላ ሕመምተኛ የቅርብ ቤተሰብ የሆኑት የ65 ዓመት ሴት በለይቶ ማቆያ ከገቡ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ተናግሯል።
ሌሎች ሰባት የኢቦላ ታካሚዎች በሁለት የማቆያ ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ሚኒስቴሩ አክለዋል።
ሁሉም በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች "በአንድ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የማኅበረሰብ ስርጭት ማስረጃ የለም" ሲል ጨምሮ ተናግሯል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቦላ መቀስቀሱ ከተረጋገጠ ወዲህ በአፍሪካ ከ4,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አፏል። ይህም ሁለተኛው ገዳይ የበሽታው ወረርሽኝ ሆኗል።
በኬንያ በቫይረሱ የሞቱት ሴት "ከመጀመሪያው ሟች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያደረጉ እና የቅርብ የቤተሰብ አባል የነበሩ" መሆናቸው ተገልጿል።
ግለሰቧ ጥቅምት 13 "ምልክት ሲያሳዩ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ነበሩ" ሲሉ የጤና ሚኒስቴሩ ተናግረዋል።
በኬንያ የመጀመሪያው ሞት የተመዘገበው ጥቅምት 5 ነበር።
ሟቹ በመስከረም ወር የታመሙ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና የተደረገላቸው ሲሆኑ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ደርሰው ሕክምና እየተደረገላቸው እያሉ ሕይወታቸው አልፏል።
አሁን በአገሪቱ ሕክምና እየተደረገላቸው የሚገኙ ሰዎች የመጀመሪያው ሟች ሦስት ዘመዶች፣ ሦስት የጤና ባለሙያዎች እና አንድ የሆስፒታል የፅዳት ሠራተኛ ናቸው።
አሜሪካ ዜጎቿን ወደ ኬንያ እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀች ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ እና ሶማሊያ ያሉ ጎረቤት አገራት በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።
ኢቦላ በቫይረስ የሚመጣ እና ገዳይ በሽታ ነው። ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሲሠራጭ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ይከሰታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ እና ከሰውነታቸው ውጪ ደም ይፈስሳቸዋል።
በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው እንደ ደም ወይም ትውከት ካሉ ከተበከሉ የሰውነት ፈሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ነው።
የቡንዲቡጋዮ የኢቦላ ዝርያ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ልዩ ሲሆን፤ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ክትባት ወይም ሕክምና የለውም። አሁን ላይ ለዝርያው ሕክምናዎችን ለማግኘት ሙከራዎች እየተካሄዱ ነው።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ9,500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙበት በዚህ ወቅት፤ እንደ ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ኬንያ ድንበር አቋርጠው በሚገቡ ሰዎች አደጋ ተጋርጦባታል።
ኬንያ ከፍተኛ ስጋት ላይ ናቸው ብላ ከመደበቻቸው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ እና ከሌሎች ዘጠኝ አገራት የሚመጡ መንገደኞችን ለመለየት የተሻሻለ ምርመራ ማድረግ ጀምራለች።