አርሰናል ከኒውካስል ዩናይትድ፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች ግምቶች

ማንቸስተር ሲቲ አዲሱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪ መሆኑን አረጋግጧል።
ቡድኑ ቅዳሜ ዕለት በኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ዋንጫ ቅዳሜ ዕለት ዌምብሌይ ላይ ሳውዝሃምፕተንን ይገጥማል።
የሊጉን መሪነት ለሲቲ አሳልፎ የሰጠው አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ ኒውካስልን በሜዳው ያስተናግዳል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታን ክሪስ ሱተን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ካፕ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ገምቷል።
አርብ
ሰንደርላንድ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ፎረስት ባለፈው ሳምንት ቢሸነፍም እስከመጨረሻው ያሳየው ያለመሸነፍ ስሜት አስደናቂ ነበር።
ከ3 ለ 1 በመነሳት 3 ለ 3 መሆን ቢችሉም ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ጎል ተሸንፈዋል።
ቡድኑ ጎሎችን ማስቆጠር እንደሚችል ደጋግሞ ቢያሳይም በዚህ ጨዋታ ግን ጎል የሚቆጠር አይመስልም።
ሆኖም ግን ይህንን ጨዋታ ሰንድርላንድ እንደሚያሽንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 - 0
ቅዳሜ
ፉልሃም ከ አስቶን ቪላ
ቪላ በሚቀጥለው ሳምንት ከፎረስት ጋር በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ከመጫወቱም በላይ በሊጉ ለሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ እየተፎካከረ ነው።
ፉልሃም ለመገመት አስቸጋሪ ቡድን መሆኑን ደጋግሞ አሳይቷል።
ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጎሎችን ባያስቆጥርም በዚህ ጨዋታ ኳስ እና መረብ እንደሚያገናኝ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ሊቨርፑል ከ ክሪስታል ፓላስ

ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት ሂል ዲንክሰን ላይ ተቀናቃኙ ኤቨርንን ማሸነፍ ችሏል።
ፓላስ ዘንድሮ ወደ አንፊልድ አቅንቶ ማሸነፍ በመቻሉ ይህንን ቢደግም አያስገርመኝም።
ቡድኑ በሊጉ ለማሳካት የሚችለው ነገር ካለመኖሩም በላይ በኮንፈረንስ ሊግ ከሻክታር ጋር ጨዋታ ይጠብቀዋል።
ሊቨርፑል እና እንደአሌክሳንደር አይዛክ ያሉ ተጫዋቾች አስተማማኝ አቋም ላይ ባይገኙም ቀያዮቹ ይህንን ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ዌስት ሃም ከ ኤቨርተን
ዌስት ሃም ባለፈው ሳምንት ከፓላስ ጋር ነጥብ ቢጋራም አሁን ከሊጉ ላለመውረድ ጫና ውስጥ ይገኛል።
ዌስት ሃም በከፍተኛ ፍጥነት ለመጫወት ቢሞክርም ኤቨርተንም ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚሰጥ እገምታለሁ።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ግንኙነታቸው 1 አቻ የተለያዩበት ውጤት እንደሚደገም አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ዎልቭስ ከ ቶተንሃም
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ሲገናኙ ቶተንሃም ባለቀ ሰዓት አስቆጥሮ ነው ከመሸነፍ የዳነው።
ቡድኑ ከቀሩት አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፎ ከሊጉ ላለመውረድ የሚያደርገውን ጉዞ በዚህ ጨዋታ መጀመረር ይኖርበታል።
ዎልቭስ ከወዲሁ መውረዱን በማረጋገጡ ጫናው ቶተንሃም ላይ ይወድቃል።
ግምት፡ 0 - 1
ማንቸስተር ሲቲ ከ ሳውዝሃምፕተን (ኤፍኤ ካፕ)

ሳውዝሃምፕተን ባለፈው ሳምንት ከብሪስተል ሲቲ ጋር አቻ እስከተለያየበት ጊዜ ድረስ አርሰናልን ጨምሮ ሰባት ጨዋታዎችን አሸንፏል።
ቡድኑ በ2023 ሲቲን ከሊግ ዋንጫ ውጭ አድርጎታል።
አሁን ተመሳሳይ ውጤት ይደገማል የሚል እምነት የለኝም።
ሲቲ ከበርንሌይ ጋር እንደነበረው ጎሎችን ማስቆጠር ካልተቸገረ ይህንን ጨዋታ ያሸንፋል።
ግምት፡ 3 - 0
አርሰናል ከ ኒውካስል
አርሰናል ባለፈው ሳምንት በሲቲ መሸነፉ የቡድኑን የዋንጫ ተስፋ የሚያጨለም ካለመሆኑም በላይ ሲቲ በርንሌይ ላእ አንድ ጎል ብቻ ደግሞ ተሰፋ የሚሰጥ ነው።
ቡድኑ አሁንም በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ይገኛል።
ኒውካስል እና አርሰናል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።
የኤዲ ሃው ቡድን በአቋም መውረድ እና እና በተጫዋቾች ጉዳት እየተፈተነ ይገኛል።
ግምት፡ 2 - 0
እሑድ
ቼልሲ ከ ሊድስ (ኤፍኤ ካፕ)
ሊያም ሮሰኒየር የቼልሲ ትልቁ ችግር ነበሩ ብዬ አላምንም።
ከብራይትን ጋር አንዳንድ ተጫዋቾች ያሳዩት አቋም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ አሰልጣኙ መናገራቸው ትክክለኛ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ አንዱን ሊድስ ሲያሸንፍ ሌላኛውን አቻ ተለያይተዋል።
ሊድስ ከበርንመዝ ጋር አቻ በመለያየት ጥሩ ውጤት አስመዝገቧል።
ግምት፡ 1 - 2
ሰኞ
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ብሬንትፎርድ

ዩናይትድ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ተገማች ሊሆን ባይችልም ውድድር ዓመቱን በጥሩ አቋም መጨረስ ይኖርበታል።
ማይክል ካሪክ ቡድኑን ለሻምፒዮንስ ሊግ ከወዲሁ እንዳበቃው ቢሰማኝም ይህ ጨዋታ እንዴት ሊጠናቀቅ እንደሚችል መገመት ይከብዳል።
ብሬንትፎርድ በመጀመሪያው ዙር 3 ለ 1 ከማሸነፉም በላይ ኢጎር ቲያጎ ሁለት ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ጨዋታም እንደሚፈትናቸው እገምታለሁ።
ብሬንትፊርድ በተደጋጋሚ አቻ እየወጣ በመሆኑ ይህም በተመሳሳይ ውጤት ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 -1















