ኮሚሽኑ ትግራይን የሚመለከቱ አጀንዳዎችን የሚያቀርበው ለፌዴራል መንግሥቱ መሆኑን ገለፀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከአራት ዓመታት በላይ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮችን በማሰባሰብ ከአንድ ወር በላይ ምክክር ያደረገው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ትግራይን የሚመለከቱ አጀንዳዎችን ለፌደራል መንግሥቱ እንደሚያርብ አስታወቀ።

በዚህም አራት ሺህ የሚሆኑ ተመካካሪዎች የተሳተፉበትን ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክር ውጤት የሆነውን የመጨረሻውን ምክረ-ሃሳብ ከመስከረም 10 በፊት ለመንግሥት እንደሚያቀርብ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በምክክሩ የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችን ለተግባሪ የፌዴራል መንግሥት አካላት ከመስከረም 10 በፊት ለማቅረብ ምክረ-ሃሳቦቹን እያደራጀ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ለሚደረጉ ምክክሮች የሚረዱ አጀንዳዎችን፣ እንዲሁም እነዚህ አካላት ሊፈፅሟቸው የሚገቡ የሕዝብ ጥያቄዎችንም በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠት መግለጫ፣ ነባሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጣዩ አዲስ ዓመት መስከረም 19 እንደሚሸኝ ጠቅሰው "የመጨረሻውን ምክረ-ሃሳብ አጠናቀን ከመስከረም 10 በፊት ለእነርሱ [ለነባር ምክር ቤት አባላት] ለማቅረብ ተግተን እየሠራን ነው" ብለዋል።

ይህ የሚሆነው ኮሚሽኑ የተቋቋመው በነባሩ ምክር ቤት በመሆኑ፣ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ምክረ-ሃሳቦቹ መቅረብ ስላለባቸው መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰዋል።

ትግራይን ጨምሮ ክልሎችን እና የከተማ አስተዳደሮችን የተመለከቱ በርካታ አጀንዳዎችንም ኮሚሽኑ መሰብሰቡን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ትግራይን የሚመለከቱ አጀንዳዎችን "አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ለክልሉ ማቅረብ ስለማንችል ለፌዴራል መንግሥት እናስረክባለን" ሲሉ ተናግረዋል። "ሁኔታዎች የሚመቻቹ ከሆነ ደግሞ አጀንዳዎቹን እዚያም ላለው ለሚመለከተው አካል የምናቀርብ ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።

በትግራይ ክልል የምክክሩን ሂደት ማከናወን ባለመቻሉ፣ አጀንዳዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሰብሰባቸውን አስታውሰው፣ ፍላጎቱ ያላቸው የክልሉ ተወላጆች በሙሉ በምክክሩ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ በሩን ክፍት ማድረጉን ገልፀዋል።

በመሆኑም በግል እና "በተወሰነ መልኩ ደግሞ የክልሉን የማኅበረሰብ ክፍል ወክለው የመጡ 164 ተጋሩ በዚህ ምክክር ላይ ተሳትፈዋል" ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ።

ይህም ሌሎች ክልሎች ካሳተፉት ቁጥር "ያነሰ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 መሠረት በቀጣይነት ከሚጠበቁበት ሥራዎች መካከል በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን ለመንግሥት ከማቅረብ በተጨማሪ ምክረ-ሃሳቦቹ ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ስልት የሚገልፅ ሰነድ ማዘጋጀትም ይገኝበታል።

ይህን ስልት አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የማቅረብ እና ለሕዝብም ይፋ የማድረግ ኃላፊነት አለው።

በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ስልቶቹን እያዘጋጀ መሆኑን እና በቅርቡ ለመንግሥት አቅርቦ ለሕዝብም እንደሚያሳውቅ ፕሮፌሰር መስፍን በመግለጫቸው አብራርተዋል።

መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ማዋል የሚያስችለውን ግልፅ እና ተጨባጭ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የሚረዳውን ስትራቴጂ ኮሚሽኑ በመንደፍ ላይ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት።

በአዋጁ በተደነገገው መልኩ፣ የምክረ-ሃሳቦቹን አፈፃፀም ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት ኮሚሽነሮቹ እየዘረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ከተቋቋመ አምስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ኮሚሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመለት የ8 ወራት የሥራ ጊዜው ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. ያበቃል።

ኮሚሽኑ ባለው ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ውስጥ የቀሩትን ሥራዎች ማጠናቀቅ እንደሚያዳግተው የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የኮሚሽኑ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በአዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወሰን ጠቅሰዋል።

ከሐምሌ 8 አስከ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም የተካሔደው አገራዊ ምክክር መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በአንዳንድ ኮሚሽነሮች ገለልተኝነት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱም ነበር። እንዲሁም የገዢው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት እንደነበረበት የሚያነሱ አካላትም አሉ።

ፕሮፌሰር መስፍን ግን፣ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ እነዚህን ውንጀላዎች አስተባብለዋል።

ኮሚሽኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ አካላት ከእገዛ ያለፈ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ሳይኖርበት ሂደቱን እስከ ፍጻሜው መምራቱንም ተናግረዋል።

ከታች ጀምሮ በምክክሩ የቀረቡትን ምክረ-ሃሳቦች በሙሉ ኮሚሽኑ ለተግባሪው አካል እንደሚያቀርብ የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ከቀረቡት 400 ምክረ-ሃሳቦች ውስጥ በልዩነት የቀረቡትን በተመለከተ ተግባሪው አካል የተለያዩ አማራጮችን ለሕዝብ አቅርቦ በሕዝበ-ውሳኔ አሊያም በሌላ መንገድ ሊያስፈፅም እንደሚችል ጠቁመዋል።

የምክክር ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ኮሚሽኑ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጥ የዛሬው የመጀመሪያው ነው።