የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ከሚያመለክቱ ስደተኞች አብዛኞቹ ከአገሪቱ መውጣት እንዳለባቸው ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ከሚያመለክቱ ስደተኞች አብዛኞቹ አገሪቱን ለቅቀው ወጥተው በሌላ አገር ከሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንጽላ ጉዳያቸውን መከታተል እንዳለባቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ይፋ ያደረገው አዲስ ፖሊሲ፤ አብዛኞቹ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ (green card) ጥያቄ ለማቅረብ ከአገሪቱ እንዲወጡ ያዝዛል።
ስደተኞች አሜሪካን ለቅቀው ከወጡ በኋላ በሌላ አገር በሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንጽላ ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም ተገልጿል። ይሄ አሠራር የማይተገበረው "በጣም ልዩ በሆኑ" ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ እንደሆነም ተቋሙ አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሕገ ወጥ ስደትን ለመግታት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ ነው።
የአሜሪካ ቪዛ ያላቸው ሰዎች በአገሪቱ እያሉ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንዲያመለክቱ የሚያስችላቸውን አሠራር ይቀለብሳል።
አዲስ የወጣው ፖሊሲ የአሜሪካን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያመለከቱ ቤተሰቦችን የሚነጣጥል ነው በሚል ተተችቷል። ቤተሰቦች የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ማለፍ ያለባቸውን ረዥም ሒደት በጋራ እንዳያከናውኑ ያግዳል ተብሏል።
በሌላ በኩል መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ብለው ከአሜሪካ የሚወጡ ስደተኞችን የመመለስ ዕድል የሚዘጋ እንደሆነም ተገልጿል።
የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት እንዳለው ተማሪዎች፣ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ያላቸው ወይም ቱሪስቶች ከአሜሪካ ውጭ ሆነው በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ጉዳያቸውን ማስፈጸም ይጠበቅባቸዋል።
"የመኖሪያ ፈቃድ ሲከለከሉ በአሜሪካ በድብቅ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ" ስደተኞች በአገራቸው ሆነው ማመልከት እንዳለባቸው መሥሪያ ቤቱ ደንግጓል።
አዲስ የሚዘረጋው ሥርዓት "ፍትሐዊ እና ውጤታማ" እንደሆነ ተቋሙ ገልጿል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በኤክስ ገጹ "የአገራችን የስደተኞች አሠራር የሚበዘበዝበት ዘመን አክትሟል" ብሏል።
የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ቃል አቀባይ ዛክ ካህለር "ስደተኞች የአገራችንን አሠራር በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ነው" ብለዋል።
"ከዚህ በኋላ አሜሪካ ወስጥ በጊዜያዊነት የሚኖሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው፤ ከመጠን ያለፈ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልሆኑ በስተቀር" ሲሉም አክለዋል።
ለስደተኞች የወጡ ሕግጋት "በወጡበት ዓላማ መሠረት በአግባቡ እንዲተገበሩ" እንዲሁም "ያሉባቸው ክፍተቶች እንዲደፈኑ" በሚል አዲሱ ፖሊስ እንደተረቀቀ አስረድተዋል።
አሜሪካን መጎብኘት "የመኖሪያ ፈቃድ ፍለጋ የመጀመሪያ ደረጃ" ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል።
አሁን ላይ የመኖሪያ ፈቃድ ጠይቀው እየተጠባበቁ ያሉ ስደተኞች ላይ አዲሱ ፖሊሲ የሚያሳድረው ጫና ግልጽ አይደለም።
የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ "ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ወይም ብሔራዊ ፍላጎት ጠቃሚ የሆኑ" ስደተኞች ጥያቄያቸውን ባሉበት ሁኔታ መቀጠል ይችላሉ።
"ሌሎች ሰዎች ባላቸው ግለሰባዊ ሁኔታ መሠረት ከውጭ ሆነው እንዲያመለክቱ ይደረጋል" ብለዋል።
የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በአሜሪካ መሥራት እና በቋሚነት መኖር ይችላሉ። ሒደቱ ከወራት እስከ ዓመታት ይወስዳል።
በሕጋዊ መንገድ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ሰነዳቸው ይሁንታ እስከሚያገኝ እየተጠባበቁ ያሉ ስደተኞች በሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ የስደተኞች ጥናት ተቋም የሆነው ካቶ ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት አብዛኞቹ የመኖሪያ ፈቃድ ጥያቄዎች ከአሜሪካ ውጭ ሆነው እንዲስተናገዱ መደረጉ፤ የዜግነት እና ስደተኞች አገልግሎት ሌሎች ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩር ያስችላል።
መሥሪያ ቤቱ ቅድሚያ ሰጥቶ ያተኩርባቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል የሕገ ወጥ የሰው ዝውውር እና የጥቃት ሰለባዎች የቪዛ ጥያቄ ይገኝበታል።
የስደተኞችን ጥያቄ የሚመለከቱ ባለሙያዎች "ለእያንዳንዱ ጉዳይ የቀረበውን መረጃ በመመልከት እጅግ አንገብጋቢ የሆኑትን ይለያሉ" ብለዋል።
የቀድሞ የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ የነበሩት ማይክል ቫለንደር አዲሱ ፖሊሲ "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እና ሠራተኞችን ዕቅድ የሚያዛባ ነው" በማለት ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"ሕጋዊ ስደትን የሚያስተጓጉል ያልተጠበቀ ውሳኔ ነው። ሕጉን የተከተሉ ሰዎችን ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ይከትታል" ሲሉም አክለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ከ40 በላይ በሚሆኑ አገራት ላይ የቪዛ ገደብ ወይም ማዕቀብ ጥሏል።
የቪዛ ቆይታ ጊዜን ማሳለፍ ከአሜሪካ መባረር እንዲሁም በቀጣይ እስከ 10 ዓመት ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከልን ያስከትላል።















