ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ጋዛ ሲጓዙ የተያዙት ተሟጋቾች በእስራኤል ኃይሎች ግፍ እንደተፈጸመባቸው ተናገሩ
ወደ ጋዛ እርዳታ ለማድረስ በቡድን በተለያዩ መርከቦች እየተጓዙ ሳለ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ በእስራኤል ኃይሎች ከተጠለፉ በኋላ ወደ አገራቸው የተባረሩት ፍልስጤምን ደጋፊ ተሟጋቾች፤ በእስራኤል ውስጥ በታሰሩበት ወቅት ግፍ እንደተፈጸመባቸው ተናገሩ።
ካናዳ ከተሟጋቾቹ መካከል በነበሩት ዜጎቿ ላይ ስለተፈጸመው "አስፈሪ በደል" ዝርዝር መረጃ እንደደረሳት አስታውቃለች። ጀርመን እና ስፔንም በርካታ ዜጎቻቸው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠዋል።
የቡድን መርከብ ጉዞው አዘጋጆች "ቢያንስ 15 የወሲብ ጥቃት ኬዞች" የገለጹ ሲሆን ታስረው የነበሩ ሌሎች ተሟጋቾች ደግሞ ድብደባ እና እንግልት እንደደረሰባቸው አረስድተዋል።
ቢቢሲ እነዚህን ክሶች በራሱ ማረጋገጥ አልቻለም። የእስራኤል የእስር ቤት አገልግሎት ሁሉም ታሳሪዎች "በሕጉ መሠረት ተይዘው እንደነበር" በመግለጽ ክሶቹን ሐሰተኛ ብሏቸዋል።
ቢቢሲ ስለ ክሶቹ ከእስራኤል ጦር ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ዘገባ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝር ውንጀላዎችን ይዟል።
'ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ' የተባለው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ አካል የሆኑ ከ50 በላይ መርከቦች እስራኤል ጋዛ ላይ የጣለችውን የባሕር ጉዞ እገዳ ለመስበር እንዲሁም ምግብ እና የሕክምና እርዳታ ለማድረስ ከቱርክ የተነሱት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ጉዞውን፤ የፍልስጤሙን ታጣቂ ቡድን ሐማስ የሚጠቅም "የሕዝብ ግንኙነት ትርኢት" ሲል የጠራው የእስራኤል መንግሥት፤ ሰኞ እና ማክሰኞ ዕለት ከቆጵሮስ በስተምዕራብ እየተጓዙ የነበሩት መርከቦች በልዩ ኃይሎች እንዲያዙ አድርጓል።
ተሟጋቾቹ ወደ እስራኤል መርከብ ከተዛወሩ በኋላ ወደ አገሪቱ እስር ቤት ተወስደዋል። ሐሙስ ዕለት የተያዙት 422 ሰዎች ወደመጡባቸው 41 አገራት ተባርረዋል። አብዛኛዎቹም ወደ አገራቸው ደርሰዋል።
በርካታ ተሟጋቾች ከእስራኤል ከተባረሩ በኋላ ደርሶብናል ስላሉት በደል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የ'ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ' አዘጋጆች "መድፈርን ጨምሮ ቢያንስ 15 የወሲባዊ ጥቃት ኬዞች ተፈጽመዋል። ከቅርብ ርቀት በፕላስቲን ጥይት ተመትተዋል። በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎች አጥንት ተሰብሯል" ብሏል።
የፈረንሳይዋ አክቲቪስት መሪየም ሃጃል "ወሲባዊ ጥቃት እና አላግባብ የሆነ መነካት እንደደረሰባት" አርብ ዕለት ፓሪስ ከደረሰች በኋላ ለጋዜጠኞች ገልጻለች።
"ተደብድቤያለሁ፣ በጥፊ ተመትቻለሁ፣ ተነክቻለሁ፣ በጉልበት የጎድን አጥንቶቼን ተመትቻለሁ፣ ጸጉሬ ተጎትቷል። ለሰዓታት ያህል የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶብኛል" ብላለች።
ጣልያናዊው ጋዜጠኛ አሌሳንድሮ ማንቶቫኒ ደግሞ "የሽብር ስፍራ" ሲል ወደ ገለጸው ከመርከብ ኮንቴነሮች የተሰራ እስር ስፍራ ከተወሰደ በኋላ በእስራኤል ኃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመበት ተናግሯል።
እንግሊዛዊው ተሟጋች ሪቻርድ ጆሃን አንደርሰን በበኩሉ "ተደብድበናል፣ ስቅይት ደርሶብናል፣ ስለልታዊ በሆነ መንገድ ሰብአዊነታች ተገፍፏል… ፍልስጤማውያን በየዕለቱ የሚያሳልፉትን ነገር በትንሹ ቀምሰነዋል" ሲል የደረሰበትን ዘርዝርሯል።
ታሳሪዎቹን የወከለው አዳላህ የተሰኘ የእስራኤል የመብት ተሟጋቾች ቡድንም በተመሳሳይ "ከፍተኛ፣ መጠነ ሰፊ አካላዊ ጉዳቶች" መድረሳቸውን ገልጿል። ቢያንስ ሦስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱም ገልጿል።
የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒታ አናንድ "እስራኤል ውስጥ ታስረው በነበሩት ካናዳውያን ላይ ስለተፈጸመው አስፈሪ በደል የሚዘረዝር መረጃ ከባለሥልጣናቶቼ ደርሶኛል" ብለዋል።
ስለ ውንጀላው ግን ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ካናዳ ድርጊቱን እንደምታወግዝ ገልጸዋል። "ለዚህ አስከፊ በደል ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ብለዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ "የቀረቡት አንዳንድ ውንጀላዎች ከባድ በመሆናቸው ሙሉ ማብራሪያ እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆዜ ማኑኤል አልባሬስ ደግሞ አራት ስፔናውያን ተሟጋቾች ለደረሰባቸው ጉዳት የሕክምና እርዳታ እንዳገኙ ገልጸዋል።
የእስራኤል እስር ቤት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ክሶቹ "ሐሰት እና ሙሉ በሙሉ እውነትን መሠረት ያላደረጉ ናቸው" ብሏል።
"ሁሉም እስረኞች እና ታሳሪዎች የተያዙት በሕጉ መሠረት መሠረታዊ መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ተጠብቆ፣ ሙያዊ በሆኑ እና በሰለጠኑ የእስር ቤት ሠራተኞች ክትትል ስር ነበር" ሲል ውንጀላዎቹን ውድቅ አድርጓል።
"የሕክምና እርዳታ የሚሰጠው በባለሙያ የሕክምና ውሳኔ እና በጤና ሚኒስቴር መመሪያዎች መሠረት" እንደሆነም ገልጿል።