አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ ለመጣስ የሞከረ መርከብን መምታቷን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, U.S. Central Command
የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለውን እገዳ በመጣስ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ሊጓዝ የሞከረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ተኩስ ከፍቶ ማስቆሙን አስታወቀ።
አሜሪካ በዚህ ሐምሌ መጀመሪያ በድጋሚ የጉዞ እገዳ ከጣለች ወዲህ የንግድ መርከብ ላይ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
አሁን የተመታው መርከብ ለአራት ጊዜ ያህል እገዳ በተጣለበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ መሞከሩን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ናቪ ካፒቴን ቲም ሀውኪንስ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፣ "የመርከቧ ሠራተኞች ቢያንስ አራት ጊዜ እገዳውን ጥሰው ለማለፍ ከሞከሩ በኋላ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ እንዳይንቀሳቀስ አድርገዋል” ብለዋል።
"የመርከቡ ሠራተኞች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው፤ ትዕዛዙን አላከበሩትም። በሥፍራው የነበሩት የአሜሪካ ኃይሎች ወደ መርከቡ የሞተር ክፍል በመተኮስ መርከቡ እንዳይሠራ አድርገውታል” ሲሉም አብራርተዋል።
"መርከቡ አሁን ወደ ኢራን እየተጓዘ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ፤ የኦማን ልዑክ አባላት ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመነጋገር በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መድረሳቸውን የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል። ኦማን በወሽመጡ ደቡባዊ ክፍል የሚገኘውን የባሕር ዳርቻ ትቆጣጠራለች።
አሜሪካ እና ኢራን ላለፈው ሁለት ሳምንታት ገደማ ተኩስ ሲለዋወጡ ቆይተዋል። ሐሙስ ሌሊት አሜሪካ ለ13ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ቴህራን በመላው መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን እና ጦር ሠፈሮችን ማጥቃቷን አስታውቃለች።
አርብ ምሽት በዋይት ሀውስ ከጋዜጠኞች ጋር የተገናኙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድሩ መቀጠሉን ቢገልጹም፣ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመፈጸም ዝተዋል።
"እያናገርናቸው ነው። ቁም ነገረኛ እየሆኑ ይመስላል። እንደማስበው... እስካሁን ስናያቸው ከነበረው በበለጠ ከልባቸው እየተነጋገሩ ነው። ያ ማለት ግን [ስምምነት ላይ] እንደርሳለን ማለት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።



















