ዮሚፍ ቀጀልቻ የዓለም የወንዶች ግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰንን በ29 ሰከንዶች አሻሻለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጀልቻ ዛሬ እሁድ በአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ ውስጥ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ውድድር የዓለም የወንዶች የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰበረ።
ዮሚፍ አሁን ያሻሻለውን የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰንን ከሁለት ዓመት በፊት ስፔን ቫሌንሺያ ላይ በተደረገ ውድድር 57 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን ይዞት ነበር።
ነገር ግን ከወራት በኋላ ኡጋንዳዊው ጄኮብ ኪፕሊሞ ክብረ ወሰኑን በማሻሻል ይዞት የቆየ ሲሆን፣ በተጨማሪም በዚህ ዓመት ፖርቹጋል ሊዝበን ውስጥ በተደረገ ውድድር ሰዓቱን በ10 ሰከንዶች በማሻሻል ወደ 57 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በማውረድ የክብረ ወሰኑን ባለቤትነቱ አጠናክሮት ነበር።
የ29 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ አሁን በተደረገው ውድድር ክብረ ወሰኑን በ29 ሰከንድ በማሻሻል 56 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ገብቷል።
ይህ ዮሚፍ አርጀንቲና ላይ ያስመዘገበው አዲስ ክብረ ወሰን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ስፖርት የበላይ አካል ተቀባይነትን አግኝቶ መጽደቅ ይኖርበታል።
በ10 ሺህ ሜትር ውድድር የትራክ ውድድር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ዮሚፍ የ10 ሺህ ሜትር የወንዶች የጎዳና ላይ ውድድር ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።
በተጨማሪም በዚህ ዓመት ኬንያዊው ሴባስቲያን ሳዌ ለንደን ላይ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት ታሪክ ባስመዘገበበት ውድድር ዮሚፍ ሁለተኛ በመውጣት ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች የሮጠ ሁለተኛው ሰው ለመሆን ችሏል።
















