ቀጥታ, ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚቆም ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች አሉ። የአጋማሽ ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ በኖርዝ ካሮላይና የተገኙት ትራምፕ “ጦርነቱን ለማቆም ተቃርበናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እንዴት እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የአሜሪካን ድሮን መትታ መጣሏን አስታወቀች

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሐሙስ ዕለት ኤምኪው -9 የተሰኘ የአሜሪካ ድሮን በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ መትቶ መጣሉን አስታወቀ።

    አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ሰው አልባ አውሮፕላኑን መትቶ የጣለው በቄሸም ደሴት መሆኑን ገልጿል።

    አክሎም በኢራን ጦር ኃይሎች ተመትቶ የወደቀ 53ኛ ኤምኪው-9 ድሮን መሆኑን ጠቅሷል። የአሜሪካ ጦር ተመትቶ ወድቋል ስለተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።

    አብዮታዊ ዘቡ ድሮኑ ተመትቶ የወደቀው ሐሙስ ዕለት ማለዳ መሆኑን ገልጾ፣ በተሻሻለ የአየር መከላከያ ስርዓት በመጠቀም መለየቱን እና ማውደሙን አስታውቋል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ የሚደረጉ የድሮን በረራዎችን እንደምትጠልፍ እና እንደምትመታ አስታውቃለች።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ ኢራን የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ በባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ የእስላማዊ ሪፐብሊኩ መሪ የፖለቲካ አማካሪ የሆኑት ሞሐመድ ባቃር ዞልቃድር ኢራን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር “ከሥልጣን እስኪወርዱ ድረስ” የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደማትከፍት ተናግረዋል።

    አማካሪው የጦርነቱ የተጀመረበት 200ኛ ቀንን በማስመልከት በሰጡት ቃለ ምልልስ አገራቸው አሜሪካን እና እስራኤልን መገዳደሯን እንደምትቀጥል እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት “የኢራን ሕዝብ የመጀመርያ ደረጃ የበቀል እርምጃ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት በሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ላይ ያተኮረ ሆኗል።

  2. የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጆሃንስበርግ ተገድላ የተጣለች ዘጠነኛዋን ሴት አስከሬን ማግኘቱን አስታወቀ

    የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጆሃንስበርግ ከተማ በተከታታይ የተገደሉ ሴቶችን ጉዳይ እየመረመረ ባለበት ወቅት የዘጠነኛዋን ሴት አስከሬን ማግኘቱን አስታወቀ።

    የዘጠኙ ሴቶች ገዳዮች ያልተያዙ ሲሆን በጆሃንስበርግ ነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃትን እና ቁጣን ቀስቅሷል።

    ፖሊስ ሐሙስ ማለዳ አስከሬኗን ያገኛት ይህች ሴት በከፊል እርቃኗን የነበረች ሲሆን በከፊል በጨርቅ ተጠቅልላ ከመንገድ ዳር ተጥላ ነበር ተብሏል።

    የሟቿ ማንነት እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

    ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በጆሃንስበርግ ከተማ ተገድለው የተጣሉ ሴቶች ቁጥር ስምንት ደርሶ ነበር።

    በርካታዎቹ ሴቶች በከፊል ተራቁተው፣ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከሚያሳይ ግልጽ ምልክት ጋር የተገኙ ሲሆን ፖሊስ የሁሉም ሞት የተያያዘ ስለመሆኑ የሚያሳይ መረጃ እስካሁን አለማግኘቱን አስታውቋል።

    ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሴቶቹን ገዳይ በቁጥጥር ስር ለማዋል “የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፖሊስ ግድያዎቹን አንድ ግለሰብ የፈጸማቸው ወንጀሎች ስለመሆናቸው ድምዳሜ ላይ ባይደርስም ቡድኖች ከወንጀሉ ጀርባ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል።

    የፖሊስ ቃል አቀባይ ብርጋዴር አትሌንዳ ማቴ "እነዚህ እዚህም እዚያም የሚፈጸሙ ተመሳሳይ ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገርግን እስካሁን ድረስ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ፍንጭ አላገኘንም" ብሏል።

    ከመጀመርያው አስከሬን ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

  3. የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች አሜሪካ 'በኢራን የጦር ወንጀል ፈጽማለች ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለ' አሉ

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ሐሙስ ዕለት አሜሪካ በኢራን ጦርነት የመጀመርያ ቀን በፈጸመቻቸው ሁለት ጥቃቶች የጦር ወንጀሎች ፈጽማለች ብሎ ለማመን የሚያስችል “አሳማኝ ምክንያት” መኖሩን ተናገሩ።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከተው ቡድን የመደባቸው ባለሙያዎች አሜሪካ በፈጸማቻቸው እና ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 178 ሰዎችን በገደሉት ሁለት ጥቃቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ምርመራ አድርገዋል።

    በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ቡድን "በግልጽ ሊለይ በሚችል" ትምህርት ቤት እና በደቡባዊቷ ላሜርድ ከተማ "በግልጽ ሊለይ በሚችል የስፖርት ማዕከል እና የመኖሪያ አካባቢ" ላይ በተፈጸሙት ሁለት የሚሳዔል ጥቃቶች የተነሳ የጦር ወንጀል ክሶችን አቅርቧል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት እውነት አፈላላጊ ቡድን የኢራን ባለሥልጣናት የጸረ መንግሥት ሠልፎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲልም ተናግሯል።

    በጄኔቫ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚቀርበው ይህ አዲስ ሪፖርት፤ በየካቲት ወር በተጀመረው የኢራን ጦርነት ወቅት የአሜሪካን ጥቃት እንዲሁም በታህሳስ ወር መጨረሻ በተቀሰቀሰው አገር አቀፍ ሁከት ላይ የኢራን መንግሥት የወሰደውን እርምጃ መርምሯል።

    ሮይተርስ በጄኔቫ ለሚገኙት የኢራን እና የአሜሪካ ቋሚ ተወካዮች ጥያቄ ቢያቀርቡም ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል እንደገለጹት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑት በግጭት ወቅት ተግባራዊ የሚሆኑ ሕጎችን መሠረት በማድረግ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በሌላ በኩል ኢራን ስልታዊ የመብት ጥሰት ፈጽማለች የሚሉ ክሶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

    የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ በሚናብ በሚገኘው ሻጃሬህ ታይዬቤህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ለተፈጸመውና ከ120 የሚበልጡ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች ለሞቱበት ጥቃት የአሜሪካ ኃይሎች ተጠያቂ እንደሆኑ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አግኝተዋል።

    ይህ ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ያስከተለ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጦር ወንጀል የሚያስቆጥር ጥቃት እንደነበር ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

  4. አሜሪካ ለሁለተኛ ጊዜ የፍልስጤም መሪ በተመድ ጉባዔ እንዳይሳተፉ አገደች

    አሜሪካ ለፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ቪዛ በመከልከል በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይታደሙ ማገዷን ሁለት የፍልስጤም ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

    አሜሪካ አባስን በስም ሳትጠቅስ የቪዛ ክልከላውን ማራዘሟን አስታውቃለች። የቪዛ ክልከላው የተራዘመው ከሰላም ኮሚቴው የሚጠበቅባቸውን ባለመወጣታቸው ነው ተብሏል።

    ማዕቀቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣለው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ነበር።

    አምና 80 ፍልስጤማውያን ባለሥልጣናት ቪዛ በመከልከላቸው በኒው ዮርክ የሚካሄደው ዓመታዊ የተመድ ጉባዔ ላይ መታደም አልቻሉም።

    አሜሪካ ባወጣችው መግለጫ የፍልስጤም አስተዳደር እና የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት “ሽብርን ያወድሳሉ” ስትል ከስሳለች። የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭትን “ዓለም አቀፋዊ” ለማድረግ ሞክረዋል በማለትም ወንጅላለች።

    የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

    ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ከትራምፕ አስተዳደር እና ከእስራኤል የቀረቡባቸውን ክሶች በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።

    በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ወራሪ ኃይል ተጠያቂ እንዲደረግ የመጠየቅ መብት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

    አምና አሜሪካ የቪዛ ክልከላ መጣሏን ተከትሎ የአባስ ተወካይ “ይሄ ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የተመድ ስምምነት ጥሰት ነው” ብለዋል።

  5. በኢራን እና ሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የቀረበውን ረቂቅ የአሜሪካ ምክር ቤት አጸደቀ

    የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢራን እና ሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የቀረበውን ረቂቅ 262 ለ159 በሆነ ድምጽ አጸደቀ።

    ከምክር ቤቱ አስቀድሞ ሴኔት ያጸደቀው ረቂቅ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲፈርሙበት የሚቀርብ ይሆናል።

    በረቂቁ ከቀረቡ ዕቅዶች መካከል የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ባንኮች እንዲሁም የኢነርጂ እና መከላከያ ዘርፍ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ይጠቀሳል።

    ሩሲያ የተጣለባትን የነዳጅ ማዕቀብ በማለፍ ነዳጅ የምታዘዋውርባቸው መርከቦች (ሻዶ ፍሊት) ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችም ይገኙበታል።

    በረቂቁ መሠረት ትራምፕ ከሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ የሚገዙ አገራት ላይ 100% ታሪፍ መጣል ይችላሉ።

    ከሩሲያ ጋር ትስስር ያላት ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ማስፋፋትም የረቂቁ አካል ነው።

    ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት በሴኔት 86 ለ11 በሆነ ድምጽ ጸድቋል።

    በአውሮፓውያኑ 1996 ኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ከ2026 እስከ 2031 የሚያራዝም ነው።

    ረቂቁ አሁን ያለውን ማዕቀብ ሕጋዊ ትግበራ የሚያስጠብቅ ሲሆን፤ ተጨማሪ ግለሰቦች እና ተቋማት በማዕቀቡ ውስጥ አልተካተቱም።

    ሆኖም ግን ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ያላቸው ተቋማት ላይ ማዕቀብ ይጥላል።

  6. ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት “ተባባሪ አባል” ከሆነች ኅብረቱ ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ትራምፕ አስታወቁ

    ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት “ተባባሪ አባል” ከሆነች ኅብረቱ ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቱ።

    የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር “ልዩ ጥምረት” እንደሚፈልጉ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

    ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የገባችበት የንግድ ጦርነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት አጠልሽቷል።

    ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት የመጀመሪያዋ “ተባባሪ አባል” እንድትሆን የቀረበውን ሐሳብ እንደሚደግፉት የኅብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ኧርሰላ ቮን ደር ሊን ተናግረዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው “ይሄንን ካደረጉ እንደ ነውጠኛ ድርጊት የሚቆጠር ይመስለኛል። ጠንካራ ታሪፍ እጥልባቸዋለሁ፤ አልያም በብዙ ሸቀጦች ከአውሮፓ ጋር ንግድ እናቆማለን” ብለዋል።

    ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት “ተባባሪ አባል” ለመሆን ያቀረበችው ሐሳብ “የሚያስቅ ነው” ሲሉም ትራምፕ አጣጥለዋል።

    “ካናዳ ጥሩ የንግድ አጋር አይደለችም። ሐሳቡ ቀና ቢሆን ጥሩ ነበር። ግን ዓላማው መጥፎ ነው። አውሮፓ ላይ ከባድ ታሪፍ እንጥላለን” ብለዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤ ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም፤ካናዳ በኅብረቱ የሚኖራት አባልነት “ለጋራ ጥቅም እንጂ ከማንም በተቃራኒ ለመቆም ያለመ አይደለም” ብለዋል።

  7. ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚቆም ትራምፕ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች አሉ።

    የአጋማሽ ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ በኖርዝ ካሮላይና የተገኙት ትራምፕ “ጦርነቱን ለማቆም ተቃርበናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እንዴት እንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

    ኢራን ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ ትራምፕ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ነገር ግን ባለፉት ወራት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገ ድርድር ወደ ተጨባጭ ስምምነት አላመራም።

    ኢራን እና አሜሪካ አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት ቀጥለዋል።

    ጦርነቱ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያባባሰው በአሜሪካ ያለው የዋጋ ንረት፣ ታሪፍ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር አገሬውን አስግቷል።

    የአጋማሽ ዘመን ምርጫው ከመቃረቡም አንጻር ሪፐብሊካን እጩዎች ፈተና ገጥሟቸዋል።

    ትራምፕ በዚህ ጫና ምክንያት ስለ ድርድር እና ጦርነቱን የመግታት ጉዳይ በአደባባይ ንግግር ማድረጋቸውንም ቀጥለዋል።

  8. ቻይና የኢራንን መብት “ለመጠበቅ” ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸች

    ከቴህራኑ አቻቸው ጋር ዛሬ ረቡዕ የተወያዩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ፤ አገራቸው የኢራንን መብት “ለመጠበቅ” ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቁ።

    በቤይጂንግ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ “ቻይና ከኢራን ጋር ውይይት ለማጠናከር እና የኢራንን ሕጋዊ መብት እና ፍላጎቶች ለማስጠበቅ ዝግጁ ናት” ብለዋል።

    የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ኢራን እና አሜሪካ ምክንያታዊ እንዲሆኑ እና እንዲቆጠቡ እናሳስባለን” ሲሉም አክለዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በቀጣይ ሳምንት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

    የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ግጭቱን ለማርገብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

    “ቀጣናዊ ውጥረቱ ወደ የመን እና ቀይ ባሕር እንዲሻገር አንሻም” ሲሉ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

  9. ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት “ተባባሪ አባል” እንድትሆን የቀረበው ጥያቄ ከኅብረቱ መሪ ድጋፍ ተሰጠው

    ካናዳ የአውሮፓ ኅብረት የመጀመሪያዋ “ተባባሪ አባል” እንድትሆን የቀረበውን ምክረ ሐሳብ እንደሚደግፉት የኅብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ኧርሰላ ቮን ደር ሊን ገለጹ።

    ፕሬዝዳንቷ ዛሬ ረቡዕ ለአውሮፓ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ ለካናዳ “በሩን ለመክፈት” የሚጠበቅባቸውን ማከናወን ይፈልጋሉ።

    ይህም በተለያዩ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትስስር መፍጠርን ያካትታል።

    የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር “ልዩ ጥምረት” እንደሚፈልጉ ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።

    ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የገባችበት የንግድ ጦርነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት አጠልሽቷል።

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤ ዶናልድ ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም፤ ካናዳ በኅብረቱ የሚኖራት አባልነት “ለጋራ ጥቅም እንጂ ከማንም በተቃራኒ ለመቆም ያለመ አይደለም” ብለዋል።

  10. በጋዛ በጦርነት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገደሉ

    በጋዛ ሰርጥ በጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ ተደርምሶ ስምንት ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ገለጹ።

    በጋዛ፣ ታል አል-ሀዋ አካባቢ የሚገኘው ስድስት ፎቅ የነበረው ሕንጻ ፍርስራሽ ሥር በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለማግኘት እና አስከሬን ለማውጣት ርብርብ እየተደረገ ነው።

    ሕንጻው ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑ ቢገለጽም እንኳን ወደ 10 የሚጠጉ ቤተሰቦች ይኖሩበት እንደነበረ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

    በሐማስ የሚመራው የሰብአዊ መከላከያ አገልግሎት እንዳለው፤ ወደ ጋዛ የሚገቡ የእርዳታ መሣሪያዎች ላይ በእስራኤል በተጣለው ክልከላ ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች “ባዶ እጃቸውን” ሲሠሩ ነበር።

    የሰብአዊ መከላከያው ዳይሬክተር ራይድ አል-ዳህሻን “አሁንም ድረስ ከፍርስራሽ ሥር ድምጽ ይሰማናል፤ ሰዎችን እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    በጋዛ ያለው የመጠለያ ውስንነት ሰዎች በሕንጻው እንዲኖሩ እንዳስገዳቸው ተናግረዋል።

    “ነገር ግን ሰዎች በተኙበት በሚያሳዝን ሁኔታ ሕንጻው ተደረመሰ” ብለዋል።

  11. በናይጄሪያ አደገኛ እፅ የሚያመርት ቡድን መሪ እንደሆነ የተጠረጠረ ሜክሲኳዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

    ባለፈው ወር አደገኛ እፅ የሚያመርት ቡድን መሪ እንደሆነ የተጠረጠረ ሜክሲኳዊ አገሪቷን ለቅቆ ለመውጣት ሲሞክር በናይጄሪያ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይፋ አደረገ።

    የግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋል በተቋም ደረጃ ‘ሜታምፔታማይን’ የተባለውን እፅ የሚያመርት ቤተ ሙከራ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። በአራት ወር ውስጥ ከሜክሲኳውያን ጋር የተገናኘ እንደሆነ የተገለጸ መሰል ቤተ ሙከራ ሲገኝ ይህ ሦስተኛው ነው።

    ሜታምፔታማይን ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን የሚያነቃቃ አደገኛ ሰው ሠራሽ እፅ ነው።

    አርቱሮ ኬሬራ ሎይዛ የተባለው የ40 ዓመቱ ግለሰብ በሌጎስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ሲውል ባለሥልጣናት ቤተ ሙከራ ውስጥ የሚለበስ ኮት እንደሆነ ያመኑትን ልብስ ለብሶ የተነሳቸውን ዲጂታል ምሥሎች እንዲሁም ሜት ለማምረት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን እንዳገኙ ገልጸዋል።

    ምሥሎቹ የተነሱበት ቦታም መርማሪዎችን በኢቦንይ ግዛት ወደሚገኘው ቤት የመራቸው ሲሆን እዚያም ኬሚካሎች እና እፁን ለመስራት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን እንዳገኙ ተናግረዋል።

    ሎይዛ ሜታምፔታማይን በማምረት ተሳትፏል መባሉን ውድቅ አድርጓል። ወደ ናይጄሪያ ያቀናውም አንድ የአካባቢው ምግብ ቤት ባለቤት ተጋብዞ እንደሆነ መግለጹን ብሔራዊው የእፅ ተቆጣጣሪ ተቋም በመግለጫው ጠቅሷል።

    የተቋሙ መርማሪዎች በተጠረጠረው ቤተ ሙከራ ውስጥ የደኅንነት ካሜራ ውስጥ በተገኘው ሜሞሪ ሎይዛን የሚመስል ግለሰብ ሰማያዊ የቤተ ሙከራ ልብስ ለብሶ ታይቷል።

    ከዚህ በተጨማሪም አንድ ናይጄሪያዊ ከአካባቢው ኬሚካሎችን እና መሣሪያዎች እንዲነሱ ለሌሎች ሰዎች ትዕዛዝ ሲሰጥ ታይቷል።

    የተጠረጠረው ቤተ ሙከራ ምን ያህል ሜታምፔታማይን ማምረት እንደሚችል የተሰጠ ግምት የለም።

    መርማሪዎች ሜክሲኳዊው ሎይዛ በኦዮ ግዛት በጫካ ውስጥ ድብቅ ሥፍራ እንደተገኘ በተገለጸ ቤተ ሙከራ እንዲሰሩ ሌሎች ሜክሲኳውያንን መልምሎ እንዳመጣም ገልጸዋል። ሰኔ ወር ላይ አካባቢው በፖሊስ ከተፈተሸ በኋላ አራት ናይጀሪያውያን በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ከአንድ ወር በፊትም መርማሪዎች የሜክሲኮ ዜጎችን እና ሰባት ናይጄሪያውያንን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

    በዚህ የወንጀል ቡድን ሰንሰለት ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራም እንደቀጠለ ተገልጿል።

    እንደ ኮኬይን ወይም ሄሮይን ያሉ ከእፅዋት የሚቀመሙ እፆች ካልሆኑ በስተቀር እንደ ሜት ያለ ሰው ሰራሽ እፅ የሚያስፈልገውን ኬሚካል እና ባለሙያዎች ካሉ የትም ቦታ ሊመረት ይችላል።

    ይህም ለተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እፁን በፍጥነት እንዲያመርቱ ቀላል አድርጎላቸዋል።

  12. ሳዑዲ አረቢያ የሁቲ ታጣቂዎች ወደ መካ የተኮሱትን ድሮን ማክሸፏን ገለጸች

    ሳዑዲ አረቢያ ማክሰኞ ሌሊት በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች መካን ለማጥቃት መሞከራቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አወገዘች።

    ሳዑዲ አረቢያ በመግለጫዋ መካ ላይ የሚፈጸም ጥቃት “ቀይ መስመር” መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቃለች።

    የሁቲ ባለሥልጣናት ወደ መካ ድሮኖች አለመተኮሳቸውን በመግለጽ በድርጊቱ እጃችን የለበትም ብለዋል።

    መካ ከየመን ድንበር 1 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች።

    መካ የነብዩ ሙሐመድ የትውልድ ቦታ እና ቅዱስ ቁርዓን የተቀበሉበት ሥፍራም ነው።

    በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት የአገሪቱ አየር ኃይል በሁቲዎች ወደ መካ የተተኮሰን ድሮን ማክሸፋቸውን እና ማውደማቸውን ያስታወቀው ረበዕ ዕለት ማለዳ ነበር።

    የጥምረቱ ቃል አቀባይ ቱርኪ አል ማልኪ ድሮኑ የተተኮሰው ሌሊት መሆኑን አስታውቀው ወደ ተከለከለ ክልል ከመግባቱ በፊት ተመትቶ ስብርባሪው በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ወድቋል ብለዋል።

    አል ማልኪ ሁቲዎች መካን ዒላማ ያደረጉት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ባሌስቲክ ሚሳዔል መተኮሳቸውን አስታውሰዋል።

    ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ከተማ በሆነችው መካ ላይ የሚፈጸም ጥቃት “ቀይ መስመር” ነው በማለት ጥምረቱ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

    ሁቲዎች በበኩላቸው ሳዑዲ ድሮን ተኩሰዋል ስትል ያቀረበችውን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።

    የሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት አባል ሄዛም አል-አሳድ ባወጡት መግለጫ “መካን ዒላማ የማድረግ ውንጀላዎች ከዚህ ቀደምም የተሰሙና አሁን ላይ ግን ማንንም የማያታልሉ ውሸቶች ናቸው” ብለዋል።

    ወደ መካ ድሮን መተኮሱ የተገለጸው ሁቲዎች ወደ ሳዑዲ በተኮሱት ድሮን እና ሚሳዔል በኻሚስ ሙሻይት፣ አብሃ እና ታይፍ በአጠቃላይ 13 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው፣ ሰባት ቤቶች እና ሁለት መኪናዎች መውደማቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

    "ከየመን ወደ ቅዱሳን ሥፍራዎች የሚሰነዘር ምንም ዓይነት ስጋት የለም። የእኛ ዘመቻዎች የሚያነጣጥሩት በነዳጅ ማጣሪያ ተቋሞቻቸው እና በወታደራዊ ካምፖቻቸው ላይ ሲሆን፣ ከቅዱስ ሥፍራዎችም እጅግ የራቁ ናቸው" ሲሉ የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ ተናግረዋል።

    ሳሪያ አክለው እንደገለጹት፣ ሁቲዎች ባለፈው ሳምንት በግዛታቸው ላይ በተፈጸሙ ከ450 በላይ የሳዑዲ የአየር ጥቃቶች የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት፣ በሳዑዲ አረቢያ ላይ ድሮኖችን እና ሚሳይሎችን ተኩሰዋል።

    እንዲሁም በማሪብ ግዛት ላይ የሳዑዲ የጦር ጄት መትተው መጣላቸውን ተናግረዋል። ይህንን በሚመለከት ግን ሳዑዲ እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።

  13. ጀርመን የብርጌድ ንሃመዱ አባላት ናቸው ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች አሰረች

    የጀርመን መንግሥት በአውሮፓ እና አሜሪካ የኤርትራን መንግሥት በመቃወም የሚታወቁት ብርጌድ ንሃመዱ አባላት ናቸው በሚል የጠረጠራቸውን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አዋለ።

    የጀርመን ፌዴራል አቃቤ ሕግ ቢሮ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ሁለት የብርጌድ ንሃመዱ አባላት በመንግሥት ደጋፊዎች በዓላት እና በፖሊስ ኃይሎች ላይ አመፅ በማደራጀት ተጠርጥረው መያዛቸውን አስታውቋል።

    የጀርመን ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መርማሪ ዳኛ ባወጣው ማዘዣ መሠረት የታሰሩት ግለሰቦች ኤርትራዊው መርሃዊ እና የጀርመን ዜግነት ያለው ትውልደ ኤርትራዊው ሽማንጉስ ናቸው።

    ሁለቱ ተከሳሾች የእንቅስቃሴው አባላት በመሆናቸው ተጠርጥረው በስቱትጋርት አቅራቢያ በሳርባሩከን በፌዴራል የወንጀል ፖሊስ መያዛቸውን አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

    መርሃዊ "የሕዝብ ሰላምን በማወክ" በሚል ተከሷል።

    በጽሕፈት ቤቱ መግለጫ መሠረት በጀርመን የአገር ውስጥ አሸባሪ ድርጅት በሚል የተፈረጀው ብርጌድ ንሃመዱ የተቋቋመው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ነሐሴ ወር ሲሆን “የኤርትራን መንግሥት ለመጣል” ያለመ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ነው።

    ንቅናቄው በጀርመን የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች በሚያዘጋጇቸው በዓላት ላይ አመጽን መቀስቀስ ግቦቹን ለማሳካት እንደተጠቀመበት አስታውቋል።

    በጀርመን የመንግሥት ተቋማት እና በፖሊስ ኃይሎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ግቦቹን ለማሳካት "ተቀባይነት ያለው መንገድ" አድርጎ እንደሚመለከተው አክሏል።

    በእስር ማዘዣው መሠረት፣ የንቅናቄው አባላት በጊሰን እና ስቱትጋርት በተደረጉ በዓላት እና ሠልፎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተሳታፊዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

    አቃቤ ሕግ ጥቃቱ በንቅናቄው መሪዎች የተደራጀ ነው ሲል ከስሶ ይህም 'ለሕይወት አስጊ የሆነ መሣሪያ' መጠቀምን ያካትታል ብሏል።

    መርሃዊ በጀርመን የብርጌድ ንሃመዱ ዋና ጸሐፊ እንደነበር እና ሽማንጉስ የንቅናቄው ሊቀመንበር ሆኖ ማገልገሉን መግለጫው ጠቅሷል።

    መርሃዊ በጊሰን ከተማ በተነሳው ሁከትም መሳተፉን የገለጸው አቃቤ ሕግ በአንድ ወቅትም የጥቃት ቡድንን መርቷል ሲል በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    ባለፈው ዓመት በተለያዩ የውጭ አገራት ሁከትና ብጥብጥ አስነስቷል የተባለው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚው ብርጌድ ንሃመዱ በጀርመን ሕግ መሰረት "በአገር ውስጥ አሸባሪነት" ተፈርጇል።

    በጀርመን፣ ቡድኑ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ፌስቲቫሎች ላይ በተቀናጁ ሁከቶች ተሳታፊ ነው በሚል ተወንጅሏል።

    አቃቤ ሕግ በነሐሴ 2022 በጊሰን የተካሄዱ ፌስቲቫሎች እንዲሁም በመስከረም 2023 በስቱትጋርት የነበረ የኤርትራውያን ማኅበር ስብሰባን ዋቢ አድርጓል።

    በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የከፋ ጉዳትን ጨምሮ በርካታ የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን እንዲሁም በርካታ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው ተገልጿል።

    "ብርጌድ ንሃመዱ" ባለፉት ዓመታት በተለይም በምዕራባውያን እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት እየተስፋፋ እና ትኩረት እየሳበ የመጣ የኤርትራውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነበር።

    የብርጌድ ንሃመዱ ደጋፊዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ሀገራት የሚያዘጋጃቸውን ክብረ በዓሎች እና ዝግጅቶች በማወክ ነው። አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ስዊድን እና ስዊትዘርላንድ የኤርትራ መንግሥትን በሚደግፉ ፌስቲቫሎች ላይ ረብሻ ያጋጠመባቸው አገራት ናቸው።

    በእነዚህ ረብሻዎች ወቅት የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ እና በተቃዋሚ ኤርትራውያን መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በተደጋጋሚ የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

    በዚህ ዓይነቱ አመጽ ላይ የተሳተፉ ኤርትራውያን በተለያዩ አገራት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2023 በስቱትጋርት የተቀሰቀውን ረብሻ ተከትሎ 56 ሰዎች በእስር እንዲቀጡ ተደርገዋል።

  14. ዴንማርክ የሩሲያ የጦር መርከቦች በሄሊኮፕተሬ ላይ ድንገተኛ ብርሃን ለቅቀዋል ስትል ከሰሰች

    ዴንማርክ የሩሲያ የጦር መርከቦች በባልቲክ ባሕር ላይ ቅኝት ሲያደርግ በነበረ ሄሊኮፕተሬ ላይ ሁለት የድንገተኛ አደጋ ምልክት መስጫ ርችት ተኩሰዋል ስትል ከሰሰች።

    የዴንማርክ መንግሥት ሰኞ እለት በተለመደ የቅኝት ሥራ ላይ በነበረው ሄሊኮፕተሩ ላይ የተፈፀመውን ክስተት ተከትሎ የሩሲያን አምባሳደር ጠርቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሚት ፍሬድሪክሰን የሩሲያን ድርጊት “ ያልተገባ እና “ ለትንኮሳ እና ለመከፋፈል የተሰራ” ሲል ገልጾታል።

    ሩሲያ በበኩሏ ክስተቱን እንደምትመረምር ገልጻ፣ የዴንማርክ ሄሊኮፕተሮች በሩሲያ የጦር መርከቦች ላይ አደገኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር ስትል በምላሹ ከሳለች።

    የሩሲያ አምባሳደር ቭላድሚር ባርቢን፣ የዴንማርክ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች በሩሲያ የጦር መርከቦች ላይ አደገኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ክስተት እንዳጋጠመ የገለጹት አምባሳደሩ፣ የአሁኑ ክስተት ላይ ያጋጠመው የግንኙነት ችግር ከሩሲያ መርከቦች በኩል ሳይሆን በዴንማርክ በኩል ያጋጠመ ነው ብለዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ዲር ሊየን በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ሩሲያ ያሳየችው ባሕርይ “ ግድየለሽ እና አደገኛ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ይህ የሆነው የኔቶ ኃይሎች በሊቱኒያ አንድ ድሮን መትተው በጣሉ በተመሳሳይ ቀን ነው።

    በባልቲክ ባሕር ላይ የተከሰተውን ክስተት ተከትሎ የዴንማርክ ጦር በሰጠው መግለጫ “ የአየር ኃይሉ አንድ ሄሊኮፕተር በተለመደ የፎቶግራፍ ማንሳት ሥራ ላይ ሳለ ተተኩሶበታል” ብሏል።

    አንደኛው ማስጠንቀቂያ በሄሊኮፕተሩ ላይ የተተኮሰ ሲሆን አንደኛው በአቅራቢያው አልፏል ብሏል።

    የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱን “ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ኮንነውታል።

  15. ከአሜሪካ ቤተ መጽሐፍት በውሰት የተወሰደ መጽሔት ከ132 ዓመታት በኋላ ተመለሰ

    በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካዋ ግዛት ኒው ሄምፕሻየር ቤተ መጽሐፍት በውሰት የተወሰደ መጽሔት ከ132 ዓመታት በኋላ ተመለሰ።

    ኮንኮርድ ቤተ መጽሐፍት እንዳለው መጽሔቱ በ1894 መስከረም ወር የወጣ እትም ሲሆን ባለፈው ሳምንት ቤተ መጽሐፍቱ መመለሻ ጊዜያቸው ላለፈባቸው የሚጥለውን ቅጣት ለአንድ ዓመት ማንሳቱን ካሳወቀ በኋላ ሊመለስ ችሏል።

    'ዘ ሴንቸሪ ኢሉስትሬትድ መንዝሊ ሜጋዚን' የተሰኘው ይህ ታሪካዊ መጽሔት መመለስ ከነበረበት ጊዜ በ48 ሺህ 220 ቀናት የዘገየ ሲሆን 12 ሺህ 55 ዶላር ቅጣትን ያስከትል ነበር።

    መጽሔቱን የመለሰው የቤተ መጽሐፍቱ ደንበኛ ጆን፣ መጽሔቱ ለአስርተ ዓመታት ቤቱ ውስጥ እንደነበር፤ ነገር ግን ቤቱ ውስጥ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ እንደማያውቅ ተናግሯል።

    በአካባቢው በሚወጣ ጋዜጣ ላይ ቤተ መጽሐፍቱ የቅጣት ምህረት ማድረጉን ገልጾ ያወጣውን ማስታወቂያ ከተመለከተ በኋላም ለመመለስ እንደወሰነ ገልጿል።

    ቤተ መጽሐፍቱ በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ “ ቅጣቱ መነሳቱን ካስታወቅን በኋላ በርካታ ደስተኛ ፊቶች ተመልከተናል” ብሏል።

    “በእርግጥ ብዙ የመመለሻ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መጽሐፍትን እንጠብቃለን። ነገር ግን እንደዚህኛው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የተወሰዱ አይደሉም” ሲልም ሎሎች ያልተመለሱ በርካታ መጽሐፍት እንዳሉ ገልጿል።

    ኮንኮርድ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ከቅጣት ነጻ የሆነ ቤተ መጽሐፍ የሚያመጣውን ውጤት ለመገምገም የመመለሻ ጊዜ ላለፈባቸው ከአውሮፓውያኑ መስከረም አንድ ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የቅጣት ምህረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራው ጽሑፍም መጽሔቱ ከዚህ በኋላ በውሰት የሚወጣ ባይሆንም በቤተ መጽሐፍቱ አንድ ጥግ ቦታ ይገባዋል” ሲል በቤተ መጽሐፍቱ ለታሪክ በተለየ ምድብ እንደሚቀመጥ ገልጿል።

  16. በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራን ሚሳዔል በአሜሪካ ጦር ላይ ያደረሳቸውን ጉዳቶች የሚያሳይ ምስል ይፋ ተደረገ

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች የወደሙ የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖችን ምስል ለመጀመርያ ጊዜ ማክሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል።

    እነዚህ ምስሎች የአሜሪካ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የጦር ሠፈሮቹ ላይ በተፈጸመበት ጥቃት የደረሰውን ከባድ ጉዳት የሚያሳዩ ናቸው።

    የኢራን ጥቃቶች የጦር አውሮፕላን፣ ሕንጻዎች እና መኪኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ምስሎቹ አሳይተዋል።

    ምስሎቹ ለሲቢኤስ የተላኩት ስሙ እንዳይገለጽ በጠየቀ እና አሁንም በቀጣናው እያገለገለ ከሚገኝ የአሜሪካ ጦር አባል ነው።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር አባል ስለጥቃቶቹ ለሲቢኤስ ሲናገር “በጦር ሠፈራችን ላይ የደረሰው ከፍተኛ ኪሳራ ነው፤ ነገር ግን የደረሰው ውድመት ለአሜሪካ ሕዝብ ይፋ አልሆነም። እኛ እዚያ ተቀምጠን የሚደርስብንን ድብደባ በጸጋ መቀበል ሆኗል ሥራችን” ብሏል።

    ምስሎቹ የተገኙት በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው ልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል የጦር ሠፈር ሲሆን ባለ አራት ሞተር ቦይንግ ጦር አውሮፕላን ተመትቶ ይታያል።

    ምስሉ የአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል ከፊተኛው ጋር ተለያይቶ የሚያሳይ ሲሆን አውሮፕላኑ የአየር ላይ እንቅስቃሴዎችን መከታተል የሚያስችል ራዳር የተገጠመለት ነበር ተብሏል።

  17. በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ደርሶ ሁለት መርከበኞች ተገደሉ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ደርሶ ሁለት መርከበኞች ሲሞቱ 23ቱን ማትረፍ መቻሉን ኦማን አስታወቀች።

    የኦማን የባሕር ላይ ደህንነት ማዕከል የፓናማን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልበው ኤል ጋይያ የተባለች መርከብ ማክሰኞ ዕለት በሞተር ክፍሏ ላይ እሳት ከተነሳ በኋላ በኦማን ወደብ መልህቋን እንድትጥል መደረጉን አስታውቋል።

    አክሎም መርከቧ ጥቃት የደረሰባት ከሙሳንዳም ባህረገብ መሬት 2.4 ኪሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

    ሰኞ ዕለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ መርከቧ በተከለከለ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ መስመር ስትጓዝ ባህር ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ መመታቷን እና በእሳት መያያዟን አስታውቆ ነበር።

    ነገር ግን የአሜሪካ ጦር የኢራን መግለጫ የተሳሳተ ነው ብሏል።

    ጦሩ አክሎም መርከቧ ባለፈው ወር በኢራን በተተኮሰ ሚሳዔል መመታቷን እና በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ የድሮን ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቋል።

    የዩኬ የባሕር ላይ ንግድ እንቅስቃሴዎች ማዕከል ደግሞ እሁድ እለት በሆርሙዝ ወሽመጥ እያለፈች የነበረች መርከብ ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ መመታቷን እና በእሳት መያያዟን መረጃ እንደደረሰው አስታውቆ ነበር።

    በዚህ ወር መጀመርያ ላይ ኢራን በወሽመጡ በኩል እያለፈ የነበረ የሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መድረሱን አስታውቃ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሁለት ፊሊፒንሳውያን መርከበኞች ተገድለዋል።

    በወቅቱ አብዮታዊ ዘቡ ሲዲር የተባለችው መርከቧ በእሳት የተያያዘችው ውሃ ውስጥ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ መሆኑን አስታውቋል።

    ነገር ግን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ኢራን ጥቃት መፈጸሟን ሲናገሩ የባህር ላይ ትራንስፖርት ደህንነት ተቋማት መርከቧ በሰሜናዊ ሙሳንዳም በተተኳሽ መመታቷን አስታውቀዋል።

    የዓለም አቀፉ የባህር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ የሞከሩ መርከቦች ላይ በተፈጸሙ የተረጋገጡ 79 ጥቃት 22 ባህረተኞች መገደላቸውን አስታውቋል።

    ማክሰኞ ዕለት ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው "የጠላት ድሮኖች" ከሙሳንዳም በስተሰሜን ምሥራቅ 80 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለ የኢራን ወደብ አቅራቢያ ሌሊት እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    ከአብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል የሆርሞዝጋን ግዛት ምክትል ገዥን ጠቅሶ፣ ክስተቱን ተከትሎ በርካታ ዓሣ አጥማጆች እንደጠፉ እና የፍለጋ እና የማዳን ጥረት እየተካሄደ መሆኑን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ኮማንድ፣ ሴንቲኮም፣ ቃል አቀባይ ለአክሲዮስ የዜና ድረ ገጽ ጦሩ የባህር ድሮን ለመስረቅ የሞከሩ ሁለት ጀልባዎችን ​​መምታቱን አስታውቀዋል።

    “የኢራን ትናንሽ ጀልባዎች በቅርቡ የአሜሪካን ሰው አልባ መርከብ ለመቆጣጠር ሞክረዋል፣ ነገር ግን ሴንቲኮም ጠንከር ያለ ምላሽ በመስጠቱ አልተሳካላቸውም” ሲሉ ካፒቴን ቲም ሃውኪንስ ተናግረዋል።

    የዓለማችን አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በሚያልፍበት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከኢራን በሚተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች የተነሳ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

  18. የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ቢን ሳልማን ለጉብኝት ካይሮ ገቡ

    በጎረቤት የመን ባሉት የሁቲ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመባት ሳዑዲ አረቢያ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ዛሬ ማክሰኞ ለይፋዊ ጉብኝት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ገብተዋል።

    ልዑሉ በጉብኝታቸው የመጀመሪያ ዕለት ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል-ሲሲ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።

    የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ አል ሲሲ እና መሐመድ ቢን ሳልማን ውይይታቸው ሁቲዎች ስጋት በፈጠሩበት የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ እንዲሁም በቀይ ባሕር የመርከብ እንቅስቃሴ ነጻነት እና ደኅንነት ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ተነጋግረዋል።

    በተጨማሪም ግብፅ ሳዑዲ አረቢያ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ እንዲሁም ለየመን ቀውስ አጠቃላይ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ እንዲገኝ እንደምትሻ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

    ባለፈው ሳምንት ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው የሁቲ አማፂያን የቀይ ባሕርን ምሥራቃዊ ጠረፍ እና የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ቁልፍ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል።

    ባለፉት ሳምንታት በተጠናከረው የየመን ሁቲ ኃይሎች ዘመቻ ሳዑዲ አረቢያ በተደጋጋሚ ዒላማ ሆናለች። ሁቲዎች የሚዋጉት የየመን መንግሥትን የምትረዳው ሳዑዲ በታጣቂዎቹ ላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    ሁቲዎች በቀይ ባሕር የመርከቦች መተላለፊያ በር ላይ ይዞታቸውን በማጠናከር በተለይ የሳዑዲ መርከቦች ላይ የእንቅስቃሴ ዕገዳ መጣላቸው ይታወቃል።

    ይህ የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ እየተጠናከረ የመጣው ተጽእኖ በመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከሳዑዲ ባሻገር ከሱዌዝ ቦይ ከፍተኛ ገቢ የምታገኘውን ግብፅንም የሚነካ ነው።

  19. በኢራን ጦርነት ምክንያት አሜሪካ የወሳኝ ጦር መሣሪያዎች እጥረት እንደገጠማት ተገለጸ

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ ፔንታገን ባወጣው ሪፖርት፣ ከኢራን ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የወሳኝ ጦር መሣሪያዎች እጥረት እንደተፈጠረ ተረጋገጠ። ይህም ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲናገሩ ከነበረው ፈጽሞ የሚቃረን ነው።

    አሜሪካ በጦርነቱ የተጠቀመቻቸውን የጦር መሣሪያዎች በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት በቀረበበት ጊዜ፣ ከየካቲት እስከ ሰኔ ድረስ በኢራን ላይ በተካሄደው ዘመቻ 33.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማስከተሉን የመከላከያ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ከዚህ ውስጥም 22.3 ቢሊዮን ዶላር የወጣው በጥቅም ላይ ለዋሉ ተተኳሾች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ላይ ነው።

    አሁን የወጣው ሪፖርት እንዳለው በኢራን ላይ የተካሄደው ዘመቻ “በወሳኝ የጦር መሣሪያ ክምችቶች ላይ እጥረት አስከትሎ ለተተኳሽ እና ለመሣሪያ አቅርቦት ያለውን የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ውስንነት አጋልጧል” ብሏል።

    የጦር መሣሪያ “እጥረቶችን እና መዘግየቶችን ለመቅረፍ፣ ፔንታገን የግዥ ሂደቶችን ለማፋጠን እንዲሁም ወሳኝ ቁሳቁሶችን፣ መለዋወጫዎችን እና የተመረጡ የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት እና ለማከማቸት የሚወስደውን ጊዜ ለመቀነስ እየሠራ ነው” ተብሏል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን በመካከለኛው ምሥራቅ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት ተመናምኗል መባሉን ደጋግመው ሲያጣጥሉት ነበር። በቅርቡም አሜሪካ “ከሞላ ጎደል ወሰን የሌለው” የጦር መሣሪያ ትጥቅ እንዳላት ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለትም ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ አሜሪካ “በታሪኳ ውስጥ ከማንኛውም ጊዜ በላይ የተራቀቁ እና የላቁ መሣሪያዎችን እያመረተች ነው” ብለዋል።

    ተፈጥሯል የተባለው እጥረት ከአሜሪካ ባሻገር ከአሜሪካ በሚቀርብላቸው ትጥቅ እና ተተኳሽ የሚተማመኑ ዩክሬን እና ታይዋንን በመሳሰሉ አገራት ላይ ስጋትን ፈጥሯል።

  20. የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ተጨማሪ ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ

    ይዞታቸውን እያሰፉ የመጡት የየመን ታጣቂ ኃይሎች ሁቲዎች ከአሥርት ዓመታት በፊት ኤርትራ እና የመን በይገባኛል የተዋጉባቸውን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው ተዘገበ።

    በደቡባዊ ቀይ ባሕር የሚገኙትን እነዚህ ቁልፍ ደሴቶች የሁቲ ኃይሎች ሰኞ ዕለት የያዙት በሳዑዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት ኃይሎችን በማስወጣት መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

    አሁን የሁቲ ታጣቂዎች በደቡባዊ ቀይ ባሕር ከኤርትራ እና ከጂቡቲ ጋር በሚዋሰነው ቦታ ላይ የሚገኙትን ሃኒሽ ደሴቶችን መቆጣጠራቸው በጂቡቲ የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲቀርቡት አድርጓቸዋል።