በካስፒያን ባሕር የኢራን መርከብን የመታችው ዩክሬን ከቴህራን የተሰነዘረባትን የአጸፋ እርምጃ ዛቻ አጣጣለች

ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ሲጓዝ የነበረ የኢራን የጭነት መርከብ ላይ ከፈጸመችው ጥቃት በኋላ ከቴህራን የተሰነዘረባትን የአጸፋ ዛቻ ውድቅ አደረገች።
ድርጊቱ የኢራን እና የዩክሬንን ጦርነቶች በቀጥታ ያገናኘ የመጀመሪያው ክስተት ሆኗል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "የኢራን ዛቻ ምክንያት የለሽ እና መሠረተ ቢስ ነው” ብለዋል።
“ቴህራን ውስጥ ያለው አገዛዝ ከ2022 ጀምሮ ዩክሬናውያን የተገደሉባቸውን የጦር መሳሪያዎች [እያቀረበ] የሞስኮን ወንጀለኛ ጦርነት አጋግሏል፤ [በዚህም] ሩሲያ ዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ወረራ ቀጥተኛ ተባባሪ ነው” ሲሉም ከስሰዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ፤ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች በካስፒያን ባሕር ላይ በፈጸሙት የረጅም ርቀት ጥቃቶች "እጅግ ጥሩ ውጤት" ማስመዝገባቸውን ያስታወቁት ቅዳሜ ዕለት ነበር።
በእነዚህ ጥቃቶች ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ወታደራዊ ጭነቶች ለማጓጓዝ ሲውሉ የነበሩ መርከቦች መመታታቸውንም ገልጸዋል።
የዩክሬን ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ፤ በሰሜናዊ ካስፒያን ባሕር በሚገኝ የነዳጅ መሠረተ ልማት በድሮን መመታቱን አስታውቋል። የሩሲያ ሚሳዔል የታጠቀ ጀልባ እንዲሁም "ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የተጣለባቸው የጭነት መርከቦች" ዒላማ መደረጋቸውንም ገልጿል።
በሩሲያ የኢራን አምባሳደር ካዜም ጃላሊ፣ "አና" የተባለው መርከብ ጥቃት የተፈጸመበት ከቮልጋ ወንዝ 5 ኪሎ ሜትር ቆሞ በነበረበት ወቅት መሆኑን የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በእስራኤል የዩክሬን አምባሳደር የሆኑት ዬቭገን ኮርኒቹክ በበኩላቸው፣ መርከቡ ከኢራን ወደ ሩሲያ ሊደርሱ የነበሩ የተለያዩ የድሮን እና ሚሳዔል ክፍሎችን ጭኖ እንደነበር ገልጸዋል። የሲቪሊያን የጭነት መርከብ አልነበረም ሲሉም ተከራክረዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ዩክሬን እና እስራኤል በተለያዩ ግንባሮች ተመሳሳይ “የክፋት ጥምረትን” እየተጋፈጡ ነው ሲሉም ለእስራኤሉ መገናኛ ብዙኃን ‘ኤን12’ ተናግረዋል።
ኢራን እና ሩሲያ ጥብቅ ወታደራዊ ግንኙት አላቸው። ኢራን ዩክሬን ላይ ወረራ ከተከፈተባት የአውሮፓውያኑ 2022 አንስቶ አገር ውስጥ ያመረተቻቸውን ሻሄድ ድሮኖች ለሩሲያ ማቅረብ ጀምራለች። ሞስኮም እነዚህ ድሮኖች ላይ ማሻሻያ በማድረግ የዩክሬን ከተሞችን አጥቅታባቸዋለች።











