ቀጥታ, ኢራን በጦርነቱ እስካሁን 270 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት እንደደረሰባት ገለጸች

የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋቴሜህ ሞሃጀራኒ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ40ቀናት በዘለቀው ጥቃታቸው ያደረሱት ውድመት "ቅድመ ግምት" 270 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ቁጥር ግን ሊለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ሊወያዩ እንደሚችሉ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ንግግር ሊጀመር እንደሚችል ለኒውዮርክ ፖስት ተናገሩ።

    “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ የሆነ ነገር ሊከሰት ይችላል። እና እኛ የበለጠ ወደዚያ [ፓኪስታን] የመሄድ ዝንባሌ አለን” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

    ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ከደረሱ በኋላ በፓኪስታን ተገናኝተው ለረዥም ሰዓት የተወያዩት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

    በወቅቱ የአሜሪካን ልዑክ የመሩት ምክትል ፕሬዜዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆኑ የኢራን ልዑክ ደግሞ የተመራው በአፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ ነበር።

    ነገር ግን ውይይቱ ያለምንም ስምምነት ተቋጭቷል።

    ዛሬ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በፓኪስታን እና ቴህራን መካከል የመልዕክተት ልውውጥ መኖሩን ዘግበው ከአሜሪካ ጋር ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ስምምነት ስለመደረሱ ግን “ምንም መረጃ የለም” ብለው ነበር።

  2. የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ውይይቱ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን አገራቸው ከእስራኤል ጋር የምታደርገው ውይይት የስቃይዋ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ “ወረራዋን በመቀጠሏ” መረጋጋት “እንደማይመለስ” ጨምረው ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የደህንነት ቀጠና ለመገንባት በሚል ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው።

    ጦርነቱ ካበቃም በኋላ የእስራኤል ጦር መሬቱን በወረራ ይዞ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሯል።

    ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአሜሪካ ተገናኝተው ውይይታቸውን ጀምረዋል።

    ሁለቱ አገራት ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላቸውም።

    ይህ ውይይት እስራኤል የሄዝቦላህ ወታደራዊ ይዞታዎች ናቸው በሚል የምትፈጽመውን ድብደባ ያስቆማል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

    እስራኤል፣ አሜሪካ እና በርካታ ሊባኖሳውያን ሄዝቦላህ ትጥቅ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። ነገር ግን በቤይሩት የሚገኘው መንግሥት ይህንን ያለ ሄዝቦላህ ይሁንታ ማስፈጸም አይችልም።

    ነገር ግን የእስራኤል ጥቃትም ቢሆን ግጭቱን ከማባባስ ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ ስለማምጣቱ ማንም እርግጠኛ አይደለም።

    የሄዝቦላህ ደጋፊዎች የታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች ራሱን ከእስራኤል ጥቃት የሚከላከልበት ነው የሚሉ ሲሆን ቡድኑም ቢሆን በየትኛወም ውሳኔ እንደማይገዛ አስታውቋል።

  3. የእስራኤል እና ሊባኖስ ልዑካን ቡድኖች በዋሺንግተን ዲሲ ውይይታቸውን ጀመሩ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ (መካከል) የውጪ ጉዳይ አማካሪ ሚካኤል ኒድሃም (በስተግራ) እና በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሚሼል ኢሳ (በስተቀኝ)

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ (መካከል) የውጪ ጉዳይ አማካሪ ሚካኤል ኒድሃም (በስተግራ) እና በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሚሼል ኢሳ (በስተቀኝ)

    የእስራኤል እና ሊባኖስ ልዑካን ቡድን ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በመሆን በዝግ ውይይታቸውን ጀምረዋል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ፊት ለፊት ተገናንተው ውይይት ሲያደርጉ ይህ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ከአሜሪካ ወገን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ጋር በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሚሼል ኢሳ እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ዋልዝ ተገኝተዋል።

    በአሜሪካ የሊባኖስ አምባሳደር ናዳ ሃምዴህ እና የእስራኤሉ አምባሳደር ይቼል ሌይተር አገራቸውን በመወከል በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ ነው።

    የሁለቱ አገራት ውይይት ከመጀመሩ በፊት ማርኮ ሩቢዮ ይህ ታሪካዊ ዕድል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    ሩቢዮ አክለውም ውይይቱ ከተኩስ አቁም “በላይ ነው” በማለት የሄዝቦላህ ተጽዕኖ “በቋሚነት እንዲያበቃ የሚያደርግ” ነው ብለውታል።

    አክለውም ለአስርት ዓታት በቀጠለ ውስብሰብ ሁኔታ ውስጥ እየሰሩ መሆናቸውን እንደሚረዱ ገልጸው ቀጥሎ በሚደረገው የስድስት ሰዓታት ንግግር አይፈታም ብለዋል።

    ነገር ግን ቋሚ እና ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ማዕቀፍ ለመንደፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

    የሁለቱ አገራት ውይይት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ለወራት ከተካሄደው ውጊኦያ በኋላ የሚደረግ ሲሆን ጦርነቱን ሊያስቆም እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

    ሄዝቦላህ የኢራን ጦርነት ከተከፈተ ከሳምንታት በኋላ በሰሜናዊ እስራኤል የሮኬት እና የድሮን ጥቃት በመፈፀም ጦርነቱን ተቀላቅሏል።

    እስራኤልም የቡድኑን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም የአየር ጥቃት እና የምድር ላይ ዘመቻ በመጀመሯ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

  4. አሜሪካ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ምንም ዓይነት መርከብ እገዳውን እንዳላለፈ ገለጸች

    ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ከኢራን ወደቦችና የባህር ዳርቻ አካባቢዎች የተጣለውን እገዳ አልፎ ምንም ዓይነት መርከብ አለማለፉን ገለጸች።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንቲኮም) ከ10,000 በላይ ወታደሮች፣ በርካታ የጦር መርከቦችና አውሮፕላኖች እገዳውን ለማስፈጸም መሰማራታቸውን ገልጿል።

    ስድስት የንግድ መርከቦች “ከአሜሪካ ኃይሎች የተሰጠውን መመሪያ ተቀብለው” ወደ ኢራን ወደብ “እንዲመለሱ” ማድረጉን ጨምሮ አስታውቋል።

    ቢቢሲ የክትትል መረጃዎችን በመመልከት አራት ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች እገዳው ከተጀመረ በኋላ የሆርሙዝ ባሕረ ወሽመጥን አቋርጠው መሄዳቸውን አረጋግጧል።

    ሴንቲኮም እገዳው ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ ወይም በሚወጡ በሁሉም አገር መርከቦች ላይ እየተተገበረ መሆኑን ገልጿል።

    አክሎም ወደ ኢራን የማይሄዱ ወይም ከዚያ የማይመጡ መርከቦች “የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መደገፉችንን” እንቀጥላለን ብሏል።

  5. እስራኤል እና ሊባኖስ ለድርድር እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት ውጊያ መቀጠሉ ተሰማ

    እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ ለመነጋገር እየተዘጋጁ ባለበት በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ጦር እና በሄዝቦላህ መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።

    የእስራኤል ጦር በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በደቡብ ሊባኖስ “የሄዝቦላህ የሽብር ድርጅት ዒላማዎች” ያላቸውን 150 ስፍራዎች መደብደቡን አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ እስራኤል ሮኬት ማስወንጨፉን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ የፈጸመችው ጥቃት የሚያሳዩ ምስሎች እነሆ፦

    በቅላሊሌህ ታየር ከተማ የእስራኤል ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ናባቲህ ላይ ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ ጭስ ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሊባኖስ ናባቲህ ላይ ድብደባ ተፈጽሟል
    በሊባኖስ ታየር የአየር ድብደባ ሲፈጸም የዓሣ አጥማጆች ጀልባቸውን ሲቀዝፉ ይታያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በሊባኖስ ታየር የአየር ድብደባ ሲፈጸም የዓሣ አጥማጆች ጀልባቸውን ሲቀዝፉ ይታያሉ
  6. ትራምፕ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር “ድፍረት” ይጎላታል በማለት ተቹ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢራን ጦርነት ላይ “ድፈረት” ይጎላቸዋል አሉ።

    “በእሷ በጣም ደንግጫለሁ። ድፍረት ያላት መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ተሳስቻለሁ” ሲሉ ለጣሊያኑ ጋዜጣ ኮሬሬ ዴላ ሴራ ተናግረዋል።

    አክለውም ሜሎኒ “አሜሪካ እርሷን በመወከል ስራዎችን እንድትሰራ ታስባለች” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሯን የተቹት ሜሎኒ ትራምፕ የካቶሊኩ ጳጳስ ላይ የሰነዘሩትን ትችት “ተቀባይነት የለውም” ካሉ በኋላ ነው።

    ትራምፕ “እርሷ ናት ተቀባይነት የሌላት፤ ምክንያቱም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቢኖራት እና ጣሊያንን እድሉን አግኝታ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ብታጠፋት ግድ አይሰጣትም” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ “ወንጀል ላይ ደካማ፣ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የከፋ” ሲሉ ፖፕ ሊዮን ወቅሰዋል። ቆይተው ደግሞ “አድናቂው አይደለሁም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፤ የትራምፕ አስተዳደርን “እንደማይፈሩ” እንዲሁም የኢራን ጦርነትን በተመለከተ በያዙት አቋም ምክንያት ከፕሬዝዳንቱ ያልተለመደ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ግጭቱን መቃወም እንደሚቀጥሉ መናገራቸው ይታወሳል።

  7. ትንታኔ፡ ቻይና የአሜሪካን እገዳ ብትኮንንም ትራምፕን ግን ከዚህ በላይ መግፋት አትፈልግም

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ዢ ጂንፒንግ እአአ በጥቅምት 2025 በተካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ላይ በተገናኙበት ወቅት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ዢ ጂንፒንግ እአአ በጥቅምት 2025 በተካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ላይ በተገናኙበት ወቅት

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ የኢራንን ወደቦች መዝጋቷን “አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው” በማለት ኮንኗል።

    ይህ አስተያየቷ የተሰማው በየቀኑ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በመወትወት በፓኪስታን የሚደረገውን የሰላም ንግግር ድጋፍ እያደረገች ባለበት ወቅት ነው።

    ቢቢሲ የቻይና ባለሥልጣናት ኢራን ዳግም ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንድትመለስ እየጎተጎቱ መሆኑን መረዳት ችሏል።

    የኢራንን 80 በመቶ ነዳጅ የሚገዛው የቻይና መንግሥት ከኢራን ጋር ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት አለው።

    ነገር ግን ቻይና ከቴህራን ጋር ያላት ወዳጅነት በንግድ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው።

    ቤይጂንግ ለቴህራን የንግድ ስምምነቶችን እንጂ ወታደራዊ ድጋፍ አታቀርብም። ከኢራን ጋርም ምንም ዓይነት ወታደራዊ ስምምነት የላትም።

    ቻይና በኢራን ጦርነት ወቅት ሁለቱም ተፋላሚ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በመጠየቅ የገለልተኝነት ሚና ይዛ መቆየት መርጣለች።

    የቤይጂንግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋሺንግተንን እርምጃ ሊኮንን ቢችልም ዶናልድ ትራምፕን ግን ከዚህ በላይ መግፋት አይፈልግም።

    ቻይና የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት በሚቀጥለው ወር ለመቀበል ሽር ጉድ እያለች ነው። በዚህ የዶናልድ ትራምፕ ጉብኝት ወቅት የተጣሉባትን ታሪፎች ለማስነሳት ትደራደራለች።

    ከዚህ በተጨማሪ ቤይጂንግ ለረዥም ዓመታት በሌሎች አገራት ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲን ስትከተል ቆይታለች። በዚህ ጦርነት ውስጥ መዘፈቅም አትፈልግም።

    ቻይና በፖለቲካው እና ወታደራዊ መስክ ያላት ኃያልነት ቢሆንም ገደቦች አሉበት።

    ስለዚህ ቤይጂንግ ነፍጥ ካነገቡት ፊት ከመሆን ይልቅ ከጎን ሆና ቀውሱን ለማረገብ መስራት ትመርጣለች።

  8. አሜሪካ የኢራን ወደቦችን ለመዝጋት ምን ልትጠቀም ትችላለች?

    ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን በአሁኑ ወቅት በሆርሙዝ ባህር ዳርቻ ከሚገኙት 14 የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦች አንዷ ናት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን በአሁኑ ወቅት በሆርሙዝ ባህር ዳርቻ ከሚገኙት 14 የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦች አንዷ ናት

    አሜሪካ የኢራንን ወደቦች ዘግታ ስለምታቆይበት መንገድ የሚገልጹ ዝርዝር መረጃዎች እምበዛም አይገኝም። ቢቢሲ ቬሪፋይ ግን በዚህ ዘመቻ ወቅት ምን ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ለመመልከት ሞክሯል።

    ቢያንስ 14 የአሜሪካ ጦር መርከቦች በባሕረ ሰላጤው እና በአረብ ባሕር ላይ መሰማራታቸውን የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኢንስቲትዮት መረጃ ያሳያል።

    እነዚህ የጦር መርከቦች ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን እንዲሁም 2500 ባሕረኞችን እና ቀዛፊዎችን የያዙ ጥቃት ፈጻሚዎችን ያካትታሉ።

    በከፊል ሰርጓጅ የሆኑ መርከቦች በቀጣናው ሊሰማሩ የሚችሉ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ግን የሉም።

    የኢራን ወደቦችን ዘግቶ ለማቆት የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገረ ግን የተሰማሩት አውሮፕላኖችን ዓይነት እና የሄዱባቸውን መንገዶች ለማወቅ የሚያስችል የክትትል መረጃ ይፋ አይደለም።

    ሌሎች በቀጣናው ተሰማርተዋል ወይንም በአቅራቢያው ናቸው የተባሉ የጦር መርከቦችም አሉ።

    እነዚህም ወደቦቹን ለመዝጋት ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ ሊደረግላቸው ይችላል።

    አውሮፕላን ተሸካሚ የሆነችው ዩኤስኤስ ጄራልድ ኤች ደብሊው ቡሽ በሦስት አውዳሚ መረከቦች ታጅባ በደቡብ አፍሪካ አካባቢ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየቀዘፈች መሆኑን የባሕር ኃይል ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

    ሌላ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን በአራት አውዳሚ መርከብ ታጅባ እየቀዘፈች ነው።

    ፎርድ በጦርነቱ መጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተች ሲሆን በአሁኑ ወቅት በግሪክ ጥገና ላይ ነች።

  9. የኢራን ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ የዓለም ምጣኔ ኃብት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አይኤምኤፍ አስጠነቀቀ

    በኢራን ጦርነት ወቅት እንደ ኢራቅ ባሉ አገራት የምግብ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ጦርነት ወቅት እንደ ኢራቅ ባሉ አገራት የምግብ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል

    የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው የኢራን ጦርነት ካልቆመ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ከቀጠለ የዓለም ምጣኔ ኃብት የመንኮታኮት አደጋ እንደተጋረጠበት አስጠነቀቀ።

    አይኤምኤፍ የኢራን ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የምግብ ዋጋ ጭማሪ ስለሚታይ የዓለም ምጣኔ ኃብት እድገት ዝቅ እንዲል ያስገድዳል ሲል ገልጿል።

    የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዓለም ምጣኔ ኃብትን በተነበየበት ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው፣ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የምግብ ዋጋ እየጨመረ የሚቀጥል ከሆነ እአአ በ2026 የዓለም ምጣኔ ኃብት እድገት ከ2 በመቶ በታች ሊሆን ይችላል ብሏል።

    "ይህ ማለት ዓለም እአአ ከ1980 ወዲህ አራት ጊዜ ብቻ ወደ ተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ እየሄደች ነው ማለት ነው" ሲል ድርጅቱ ገልጿል።

    ዓለም በቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚ ቀውስ ያጋጠማት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ ነው።

    የኢራን ጦርነት ከጀመረበት ከስድስት ሳምንታት ወዲህ ዋናው የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እንዲሁም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው የሰላም ድርድር ያለውጤት በመጠናቀቁ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

    የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት "በድጋሚ የዓለም ኢኮኖሚ ከመስመሩ ውጪ የመሆን አደጋ ተጋርጦበታል፤ በዚህ ወቅት በየካቲት 2018 ዓ.ም. በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ነው።"

    በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትሉ ከሚችሉት እጅግ አስከፊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የሆነው የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዚህ ኣመት ታይቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ አንድ በርሜል የነዳጅ ዘይት በአማካይ 110 ዶላር ደርሷል።

    እአአ በ2027 ደግሞ 125 ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል።

    በእነዚህ ግምቶች ላይ በመመስረት አይኤምኤፍ በሚቀጥለው ዓመት የዋጋ ግሽበት እስከ 6 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል። ይህ ደግሞ ብሔራዊ ባንኮች የዋጋ ጭማሪን ፍጥነት ለመቀነስ የወለድ ተመኖችን ከፍ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል።

    በኢራን ግጭት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ወደ 120 ዶላር ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም ማክሰኞ ዕለት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ 98.85 ዶላር ተሸጧል።

    ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግጭቱ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከተፈታ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚወጣው የነዳጅ ምርት እና የውጭ ንግድ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ መደበኛ መሆን ከጀመረ በ2026 የዓለም እድገት በ3.1 በመቶ ብቻ እንደሚቀንስ ግምቱን አስቀምጧል።

  10. ኢራን በጦርነቱ እስካሁን 270 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት እንደደረሰባት ገለጸች

    እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን ከተሞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን በጦርነቱ ምክንያት የደረሰባትን ውድመት ግምት ውስጥ በማስገባት የካሳ ክፍያን የድርድሩ አካል ለማድረግ በማሰብ የጉዳቱን መጠን ማስላት መጀመሯን ከአብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘገበ።

    የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋቴሜህ ሞሃጀራኒ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ40ቀናት በዘለቀው ጥቃታቸው ያደረሱት ውድመት "ቅድመ ግምት" 270 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ቁጥር ግን ሊለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

    በኢራን የሚገኙ ባለሥልጣናት የደረሰውን ውድመት እያሰሉ መሆኑን የተናገሩት ባለሥልጣኗ ይህም በሕንፃዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና ኢንዱስትሪዎች ሥራ በማቆማቸው ምክንያት የሚደርሰውን ኪሳራ ያካትታል ማለታቸውን ታስኒም ዘግቧል።

    ሞሃጀራኒ ለኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ ኢርና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ውይይት ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ ካሳ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ቀደም ሲል በፓኪስታን በተካሄደው ውይይት ላይ "ጠቃሚ ውይይቶች" እንደተደረጉ ቢናገሩም ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ግን አልተደረሰም።

    በቴህራን በተፈጸመ የአየር ድብደባ ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን በተፈጸመ የአየር ድብደባ ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንጻ
  11. የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከአሜሪካ ጋር ቀጣይ ንግግር ስለመኖሩ “መረጃ የለም“ አሉ

    የአሜሪካ እና የኢራን ባንዲራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ኢርና፣ በአሜሪካ እና በቴህራን መካከል አደራዳሪ በመሆን እያገለገለች ካለችው ፓኪስታን ጋር የመልዕክት ልውውጦች ቢኖሩም ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ግን የተደረሰ ስምምነት ስለመኖሩ “መረጃ የለም” አለ።

    የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሰው የዘገቡት የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያለውጤት ከተጠናቀቀው ድርድር ወዲህ ከፓከሲታን ጋር ያለው የመልዕክት ልውውጥ “አሁን ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ” መሆኑን ገልጸዋል።

    ቀደም ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል አሜሪካ እና ኢራን በዚህ ሳምንት ዳግም በኢዝላማባድ ተገናኝተው ውይይታቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

    ሮይተርስ የጠቀሳቸው ምንጮች ሁለቱ አገራት መቼ ወደ ድርድሩ እንደሚመለሱ በግልጽ ባይናገሩም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ግን ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

    አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን “ቁርጥ ያለ ቀን አልተቀመጠም። ልዑካኑ ከአርብ እስከ እሁድ ያለውን ቀን ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢዝላማባድ የተደረገው የሁለቱ አገራት ውይይት የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው።

    ንግግር ዳግም እንደሚጀመር ለሮይተርስ የተናገሩት የመጀመርያው ምንጭ ለሁለቱም አገራት ምክረሃሳቦች የያዘ ሰነድ መሰጠቱን እና ልዑካኖቻቸውን ዳግም ልከው ውይይቱ እንዲቀጥል ተነግሯቸዋል ብለዋል።

    ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው የፓኪስታን ምንጮች ደግሞ ኢዝላማባድ ከሁለቱም አገራት ጋር ቀጣዩ ውይይት መቼ መደረግ እንዳለበት እየተነጋገረች መሆኑን ገልጸዋል።

    አክለውም በሳምንቱ መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ከፍተኛ የፓኪስታን ባለሥልጣን “ኢራንን አነጋግረናል እናም ሁለተኛው ዙር ንግግር ሊደረግበት ስለሚችልበት ሁኔታ በጎ ምላሽ አግኝተናል”

    በፓኪስታን የሚገኘው የኢራን ኤምባሲም ስለ ሁለተኛ ዙር ድርድር ውይይቶች መደረጋቸውን ለሮይተርስ አረጋግጧል።

    ዋይት ሐውስ ግን በጉዳዮ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

  12. ጣሊያን ከእስራኤል ጋር ያላትን ወታደራዊ ስምምነት አቋረጠች

    የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጆርጂያ ሜሎኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጣሊያን ከእስራኤል ጋር የገባችውን ወታደራዊ ስምምነት እንደማታድስ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጆርጂያ ሜሎኒ ተናገሩ።

    ሜሎኒ በየአምስት ዓመቱ ይታደስ የነበረውን የሁለቱን አገራት ወታደራዊ ስምምነት ለማዘግየት የወሰኑት “አሁን ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት” እንደሆነ ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስለጉዳዩ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

    ነገር ግን ሮም እና ቴል አቪቭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ንፋስ ገብቶታል።

    በሊባኖስ የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ጣሊያናውያን ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከተተኮሰባቸው እና አንድ መኪና ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ባለፈው ሳምንት ጣሊያን በሮም የሚገኙትን የእስራኤል አምባሳደርን ጠርታ አነጋግራለች።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እስራኤል በሊባኖስ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “ተቀባይነት የሌለው” ካሉ በኋላ “እንደ ጋዛ ያለ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ ቢሆን መቆም አለበት” ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ እስራኤል የጣሊያን አምባሳደርን በመጥራት አነጋግራለች።

    ሌሎች የአውሮፓ አገራት በተመሳሳይ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የጦር መሣሪያ ውጭ ንግድ ገድበዋል ወይንም ለጊዜው አቁመዋል።

    የጣሊያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለረዠም ጊዜ አገራቸው ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ ሲወተውቱ ነበር።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጣሊያናውያን እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    ሠልፈኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ የፍልስጤም ነጻ አገርነትን እንደ ሌሎች ለመቀበል ዳተኛ በመሆን ተችተዋቸዋል።

    ጣሊያን ከእስራኤል ጦር መሣሪያ ከሚገዙ ሦስት ቀዳሚ አገራት መካከል አንዷ ናት።

    ከፊት ያሉት ሁለት አገራት አሜሪካ እና ጀርመን ናቸው።

  13. የኢራን ፕሬዝዳንት ወታደራዊ እርምጃ አሜሪካ “ራሷ የፈጠረችውን ችግር” ያባብሳል አሉ

    ፕሬዝዳንት መሱድ ፐዝሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, IRANIAN PRESIDENCY

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዝሽኪያን ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ቴህራን የሰላም ንግግሮችን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን እና ግጭቶችን ለመፍታት የምትመርጠው ዲፕሎማሲያዊ መንገድን እንደሆነ መናገራቸውን የኢራን የዜና አውታሮች ዘገቡ።

    ፕሬዝዳንቱ ለማክሮን ዛቻዎች፣ ጫናዎች እና ወታደራዊ እርምጃዎች ችግሮችን ለመፍታት “አያግዙም” በማለት ተናግረዋል። አሜሪካ “ራሷ የፈጠረችውን ችግር” የሚያባብስ እንደሚሆንም አሳስበዋል

    ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን አሜሪካ ለዓለም አቀፍ ሕግ እና መመሪያ ተገዢ እንድትሆን አውሮፓ ማበረታታት አለበት ሲሉም አክለዋል።

  14. ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት መርከቦች ከአሜሪካ እገዳ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ አለፉ

    በሆርሙዝ የሚጓዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በሆርሙዝ ላይ የጣለችው እገዳ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ቢነገረም ከኢራን ጋር ግንኙነተ ያላቸው አራት መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፋቸውን ቢቢሲ ቬሪፋይ የተነተነው የመርከቦች ጉዞ የትክክል መረጃ አሳየ።

    ‘ማሪን ትራፊክ’ የተሰኘው መርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚመለክተው ከአራቱ ውስጥ ሁለቱ መርከቦች የኢራን ወደቦችን ጎብኝተው ነበር።

    'ክርስቲያና' የተሰኘችው የጭነት መርከብ ወደ ኢራን ባንዳር ኢማን ኮሜኒ ወደብ ተጉዛ የነበረ ሲሆን ሰኞ ዕለት አሜሪካ እገዳ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ደግሞ በወሽመጡ በኩል ማለፏን መረጃው ያሳያል።

    ከኢራን ጋር በሚያደርገው የንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ‘ሪች ስቴሪ’ የተባለ ሌላ መርከብ ደግሞ ትናንት ሌሊት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሻርጃ በመነሳት በሆርሙዝ በኩል ተጉዟል። መርከቡ መዳረሻው ቻይና እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።

    በወሽመጡ በኩል ያለፈው ሌላኛው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ‘ሙርሊኪሻን’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው። ይህም መርከብ ከኢራን ጋር ባለው ንግድ ምክንያት አሜሪካ ማዕቀብ ጥላበታለች።

    መርከቡ ከቻይና ላንሻን እንደተነሳ እና ሌሊቱን በሆርሙዝ በኩል እንዳለፈ መረጃው አሳይቷል። እንደ ማሪን ትራፊክ ከሆነ፤ መርከቡ የታየበት የመጨረሻው ስፍራ ከኢራን ቃሽም ደሴት በስተምስራቅ ያለ አካባቢ ነው።

    ‘ኤልፒስ’ የተባለ ሌላ ነዳጅ ጫኝ መርከብም ማክሰኞ ዕለት ከኢራኑ ቡሼህር ወደብ ተነስቶ በወሽመጡ በኩል ማለፉን የጉዞ መከታተያው ድረ ገጽ መረጃ ይጠቁማል። መዳረሻው ያልታወቀው ይህ መርከብም በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎበታል።

    እነዚህ መርከቦች አድራሻቸውን ለመደበቅ ሲሉ የሚገኙበትን ቦታ በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

    የአሜሪካ ጦር ከትናንት ሰኞ 11 ሰዓት ጀምሮ “ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን በሙሉ” እንደሚያግድ አስታውቆ ነበር።

    "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን" ግን እንደማያስቆም ገልጾ ነበር።

  15. ቻይና “አደገኛው እና ኃላፊነት የጎደለው” የአሜሪካ እገዳ “ውጥረቱን ያባብሳል” ስትል አስጠነቀቀች

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/Shutterstock

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረችውን ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ የጉዞ እገዳ “አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው” በማለት አወገዘ።

    ውጤት ያልተገኘበት የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር ፓኪስታን ውስጥ ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ኢራን ወደቦች ጉዞ እንዳይደረግ ዘግቷል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን፤ እገዳው “ውጥረቱን ከማባባስ እና ቀድሞውንም ደካማ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመሸርሸር” ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው አስጠንቅቀዋል።

    “ይሄ አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ባሕሪ ነው” ሲሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም ቻይና ለኢራን አዲስ የአየር መከላከያ ስርዓት እያዘጋጀች ነው የሚሉ ዘገባዎች “ሙሉ በሙሉ ፈጠራ ናቸው” ሲሉ አስተባብለዋል።

    ይህ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቻይና ለኢራን ወታደራዊ እገዛ የምታደርግ ከሆነ በምርቶቿ ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።

    “አሜሪካ በቻይና ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ለመጣል ይህንን እንደ ምክንያት የምትጠቀም ከሆነ፤ ቻይና በእርግጠኝነት ቆራጥ የአጸፋ እርምጃዎችን ትወስዳለች” ብለዋል።

  16. የተባበሩት መንግሥታት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም አለ

    የህንድ መርከብ በሆርሙዝ በኩል እየተጓዘ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት፤ ማንም አገር ለዓለም አቀፍ ትራንዚት ጥቅም ላይ በሚውለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን የማገድ ሕጋዊ መብት እንደሌለው ገለጹ።

    የዓለም አቀፉ የባሕር ጉዞ ተቋም ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ ከቢቢሲ ራዲዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ ጉዞ መታገዱ አደገኛ ምሳሌን የሚያስቀምጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

    “ግጭት እየተካሄደ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለዓለም አቀፍ ጉዞ ጥቅም ላይ የሚውልን ማንኛውም ወሽመጥ ለማገድ የሚወሰድ እርምጃ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕጋዊ መሠረት የለውም” ብለዋል።

    ዋና ጸሐፊው ዶሚንጌዝ፤ “ተጨማሪ የአጸፋ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር፤ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ ያጡት 20 ሺህ ባሕርተኞች እና በዓለም ዙሪያ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የበረታባቸው ሰዎች ስጋት ይጨምራል” ሲሉም ተናግረዋል።

    “ለረጅም ጊዜ በቆየ ቁጥር ተጽዕኖው በሁላችንም ላይ ለተራዘመ ጊዜ ይቆያል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ 20 በመቶው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋት የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    ለእዚህ የኢራን እርምጃ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞን ከትናንት ጀምሮ አግደዋል።

  17. ሆርሙዝ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተዘጋ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት የቻይና መርከብ ማለፉ ተዘገበ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Ian Forsyth/Getty Images

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ በሆርሙዝ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን ካገደ በኋላ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት አንድ የቻይና ነዳጅ ጫኝ መርከብ በወሽመጡ በኩል ማለፉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    መዳረሻው ቻይና የሆነው ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የበረው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ ላይ እንደነበረ ቢቢሲ የተመለከታቸው መረጃዎች አሳይተዋል።

    “ሪች ስቴሪ” የተሰኘው ይህ ነዳጅ ጫኝ የአሜሪካ እገዳ ትናንት 11 ሰዓት ላይ ከተጀመረ በኋላ በወሽመጡ በኩል በማለፍ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ቀዝፎ የሄደ መርከብ መሆኑን የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጾች አሳይተዋል ተብሏል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ የመርከቡ ባለቤት “ሻንዳይ ዡአንረን ሺፒንግ” የተባለ እና ከኢራን ጋር በሚፈጽመው ንግድ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ኩባንያ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት “ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት ወይም ከዚያ ለመውጣት የሚሞክር ማንኛውም እና ሁሉም መርከቦች” በአሜሪካ ባሕር ኃይል እንደሚታገዱ ገልጸው ነበር።

    ሰኞ ዕለት ደግሞ እገዳው የሚተገበረው “ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ” መርከቦች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝም በተመሳሳይ “ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚደረጉ ሁሉም የባሕር ላይ ጉዞዎች” እንደሚታገዱ አስታውቋል።

    ይሁን እንጂ "እገዳው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወይም ከ[ኢራን] ወዳልሆኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ ገለልተኛ የትራንዚት ጉዞዎችን አያስቆምም" ብሏል።

    ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እገዳው ሰኞ 11 ሰዓት ላይ ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ አስቀድሞ ባሉት ሰዓታት አራት መርከቦች በወሽመጡ በኩል አልፈዋል።

    ‘ማሪን ትራፊክ’ የተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያሳየው አራቱም የጭነት መርከቦች ናቸው። ምናልባትም ነዳጅ፣ ጋዝ ወይም ኬሚካል ጭነው እንደሚሆን ተገምቷል።

    ማክሰኞ ዕለት ጉዞ ያደረገው ብቸኛ መርከብ ‘ሪች ስቴሪ’ ነው። ይህ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የነበረው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ እንደሆነ እና መዳረሻውን ቻይና እንዳደረገ የ‘ማሪን ትራፊክ’ መረጃ ያሳያል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ በዚህ መርከብ ላይ ያሉት የቻይና የባሕር ሠራተኞች ናቸው።

    በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ሌላ መርከብም ወደ ወሽመጡ ማምራቱን የዜና ወኪሉ ‘ኤልኤስኢጂ’ ከተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ መመልከቱን ጠቅሷል።

    ከዚህ ቀደም የሩሲያ እና የኢራን ነዳጅን በማጓጓዝ የሚታወቀው ይህ ሁለተኛ መርከብ፤ ሐሙስ ዕለት ኢራቅ ደርሶ ነዳጅ እንደሚጭን ይጠበቃል ተብሏል።

  18. የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷ "ከባድ" የሉዓዊነት “ጥሰት” ነው አሉ

    የመርከብ ትራፊክ እንቅስቃሴ

    የፎቶው ባለመብት, MarineTraffic

    የምስሉ መግለጫ, የመርከብ ትራፊክ የክትትል መረጃዎች በሆርሙዝ ወሽመጥ በጣም ጥቂት መርከቦች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያሳያሉ

    በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሜሪካ የኢራን ወደቦችን መዝጋቷን የቴህራን ሉዓላዊነት ላይ የተፈፀመ “ከባድ ጥሰት” ሲሉ አወገዙ።

    አምባሳደር አሚር ሳይድ ኦራቫኒ ለተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፃፉት ደብዳቤ “ሕገ ወጥ” የሆነው እግድ “የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረታዊ መርህዎች ላይ ከባድ ጥሰት የሚፈፅም” ነው ብለዋል።

    ጉቴሬዝ “ሁሉም ወገኖች” ለዓለም የነዳጅ ዝውውር ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የመርከቦችን ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በፓኪስታን የተደረገው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ከትናንት ሠኞ ጀምሮ የኢራን ወደቦችን ዘግቷል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እግዱ “ያለ ልዩነት” ወደ ኢራን ወደቦች ወይም የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በሚገቡ እና በሚወጡ የሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቋል።

    ሆኖም ጦሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንደማይከለክል ገልጿል።

  19. እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ በአሜሪካ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ

    ሊባኖስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል እና የሊባኖስ አምባሳደሮች ልዩ የተባለ የሰላም ንግግር በዛሬው ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ ያደርጋሉ።

    ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለሥልጣናት ለቀጥታ ንግግር ፊት ለፊት ሲገናኙ በአስርት ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ልዩ በሆነው የቀጥታ ንግግር እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    የሁለቱ ጎረቤት አገራት ንግግር አሜሪካ እና ኢራን የመካከለናውን ምሥራቅ ቶርነት ለመቋጨት ያደረጉት ስምምነት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሚደረግ ነው።

    መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአገራቱ መካከል የከፍተኛ ባለሥልጣናት የቀጥታ ንግግር ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይም ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የሊባኖስ ሹማምንት በመጀመሪያ እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የከፈተችው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የማስማማት ፍላጎት አላቸው።

    ይሁን እንጂ እስራኤል በኢራን የሚደገፈው ቡድን ትጥቁን መፍታት አለበት በሚል ሀሳቡን ውድቅ አድርጋዋለች።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ የሁለቱ አገራትን ንግግር ውድቅ በማድረግ ስምምነት ለሚደረስበት ማንኛውም ጉዳይ እንደማይገዛ አስታውቋል።

    የአሁኑ የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ግጭት ለሊባኖስ አውዳሚ ሆኗል። 500 ሴቶችን፣ ሕፃናትን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ2,000 ሠዎች በላይ ሠዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

  20. የተመድ ዋና ጸሐፊ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ እንደሚቋጭ ተስፋ በማድረግ በድጋሚ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ።

    ጉቴሬዝ፤ ጦርነቱን ለማብቃት የሚያስችል “ወታደራዊ አማራጭ እንደሌለ ግልጽ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ሁለቱ አገራት ለሁለት ሳምንት የደረሱበት የተኩስ አቁም “ፍጹም መጠበቅ እንዳለበት” ያሳሰቡት ዋና ጸሐፊው፤ “ሁሉም” የስምምነቱ “ጥሰቶች ሊቆሙ እንደሚገባ” ገልጸዋል።

    “ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አክለውም ሁሉም አገራት “በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገውን ጨምሮ የመርከቦች የጉዞ ነጻነትን ማክበር እንዳለባቸው” አስታውሰዋል።

    ጉቴሬዝ ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የወሰደችውን እርምጃ በመድገም ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን ካገዱ በኋላ ነው። ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ለማስገደድ መሆኑን ተናግረዋል።