በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ ጉዞ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ “ሁሉም የንግድ መርከቦች ሚያደርጉት ጉዞ ለቀሪው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን መታወጁን” በኤክስ ገጻቸው አስታውቀው ነበር።
የኢራን መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ “ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣንን” ጠቅሶ ባስተላለፈው ዘገባ፤ የመርከቦቹ ጉዞ የሚከናወነው “በተለየ መስመር” እንደሆነ ገልጿል። መርከቦቹ ለማለፍ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸውም ጠቅሷል።
ባለሥልጣኑ ለቴሌቪዥን ጣቢያው እንደተናገሩት፤ ይህ የተለየ የጉዞ መስመር የተወሰነው በኢራን የወደቦች እና ማሪታይም ድርጅት ነው።
ጣቢያው ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የወታደራዊ መርከቦች ጉዞ አሁንም ቢሆን "የተከለከለ" ነው።
በሌላ በኩል የመርከብ ጉዞ ኩባንያዎች የሆርሙዝ ደኅንነት እስከሚረጋገጥ ድረስ ወሽመጡን እንደማይጠቀሙ ተናግረዋል። ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የነዳጅ እና የጋዝ ጫኝ መርከቦች ኦፕሬተር፤ ለጊዜው የኢራን መግለጫ “ምንም የሚቀይረው ነገር የለም” ብሏል።
“አላስፈላጊ አደጋ ውስጥ መግባት አለብን ብለን አናስብም፤ የኩባንያችን በወሽመጡ በኩል ቀድሞ የሚያልፍ ተቋም እንሆናለን የሚል አቋም የለውም” ሲል ገልጿል።
በቀጣናው የሚገኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ኦፕሬተር የሆነው ‘ስቴና በልክ’ የተሰኘው ኩባንያ በበኩሉ “ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ” መሆኑን አስታውቋል።
“የእያንዳንዱ ጉዟችን ውሳኔ የሚመሠረተው የሠራተኞቻችን እና የመርከቦቻችን ደኅንነት ላይ ነው፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እስካላረካን ድረስ ጉዞ አንጀምርም” ብሏል።






















