ቀጥታ, ኢራን ከአሜሪካ ጋር መግባባት እንደተደረሰ የታገደባት ግማሽ ሀብቷ እንዲለቀቅ ጠየቀች

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው ድርድር መግባባት ላይ ሲደርስ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከታገደባት ሀብት ግማሽ ያህሉ እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነገረ። ድርድሩ ገና ከመቋጫው ያልደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን የታገደ ሀብት የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው ነበር። ይህ ጉዳይ በሁለቱ አገራት መካከል ከስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት እንዳይሆን ተሰግቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሞቃዲሾ ለሁለት ቀናት የቆየው ግጭት ጋብ ማለቱ ተዘገበ

    የመንግሥት ወደታሮች እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደጋፊ ሚሊሻዎች ሞቃዲሾ ውስጥ ለሁለት ቀናት ከተጋጩ በኋላ የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገለጸ።

    "የተቃዋሚ ቡድን ሚሊሻዎች ትጥቅ ፈትተው ከነበሩባቸው ቦታዎች እንዲወጡ ተደርገዋል።” ያለው ሚኒስቴሩ ግጭቱን ፈርተው የሸሹ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ኑሯቸው ተመልሰዋል ብሏል።

    ነገር ግን ነዋሪዎች ሚሊሻዎች ትጥቃቸውን አለመፍታታቸውን እና ግጭቱም የቆመው በጎሳ መሪዎች በተደረገ የሽምግልና ጥረት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃ በኋላ ቦታቸውን ያላስረከቡትን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድን የሚቃወም ሰልፍ ለማካሄድ የተያዘው ዕቅድ ከመተግበሩ በፊት ነው።

    ባለፈው መጋቢት ወር የአገሪቱ ፓርላማ የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ቆይታ በአንድ ዓመት የሚያራዝመውን ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ በመደገፍ የምርጫ ጊዜውን በአንድ ዓመት ገፍቶታል።

    ሐሙስ ዕለት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼክ አህመድ የመንግሥት ኃይሎች ቤታቸውን ዒላማ ማድረጋቸውን እና መንግሥት “በሕገ- ወጥነት ሕገ መንግሥቱን አሻሽሏል” ሲሉ ከስሰዋል።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሳን አሊ ካሂር በተመሳሳይ የመንግሥት ወታደሮች ፀረ ታንክ መሳሪያ እና ድሮኖችን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ተጠቅመዋል ሲሉ ክስ አሰምተዋል።

    የማስታወቂያ ሚኒስቴር ግን ሁለቱን የቀድሞ ባለሥልጣናት ታጣቂዎቻቸውን ወደ መኖሪያ አካባቢዎች በማሰማራት እና ፖሊሶችን እንዲያጠቁ በማድረግ የሰላማዊውን ሕዝብ ሕይወት ለአደጋ አጋልጠዋል ሲል ወቅሷል።

    የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ማኅበር በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

  2. በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ሚሊዮኖችን ለረሃብ አደጋ ማጋለጡ ተነገረ

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን ለረሃብ አደጋ እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።

    ድርጅቱ እንዳለው እየጨመረ ያለው የነዳጅ እና የትራንስፖርት ዋጋ በአንድ በኩል ምግብን ውድ ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የገንዘብ እጥረት ድርጅቱ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ እንዲቀንስ አስገድዶታል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ቀጣናዊ ጦርነት ከመቀስቀሱ በተጨማሪ ወደ ሊባኖስ ተስፋፍቶ ሆርሙዝ ወሽመጥን ጨምሮ በወሳኝ የባሕር ማጓጓዣ መስመሮች በመዘጋታቸው እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል።

    ይህ ሁኔታም የጭነት መርከቦች የጉዞ መስመሮቻቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ሰንሰለትን አደናቅፏል።

    በአፍጋኒስታን፣ በሶማሊያ እና በሲሪ ላንካ ያሉ ቤተሰቦች ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ሲሆኑ፣ በነዳጅ እና በምግብ ዋጋ መናር እንዲሁም በገቢ ማሽቆልቆል እና በንግድ እንቅስቃሴ መቋረጥ ምክንያት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑ ተገልጿል።

    የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት 6.5 ሶማሊያውያን ወይም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ከባድ የረሃብ አደጋ ይገጥመዋል።

    በአፍጋኒስታን ደግሞ 17.4 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት ችግር ገጥሞታል።

    መስተጓጎሉ የሚቀጥል ከሆነ ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ ከፍ በማለት በሶማሊያ እና በአፍጋኒስታን ተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ የምግብ እጥረት እና ረሃብ እንደሚያጋጥማቸው ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

    ሁለቱም አገራት ከውጭ በሚገቡ የኃይል አቅርቦት እና የምግብ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናቸው።

  3. የሰሀራ በረሃን ሲያቋርጡ ከነበሩ ተጓዦች መካከል ቢያንስ 50 ሰዎች በውሃ ጥም ሞቱ

    በሰሀራ በረሃ ውስጥ እየተጓዙ ሳሉ መኪናቸው የተበላሸባቸው ቢያንስ 50 ሰዎች በውሃ ጥም መሞታቸው ተዘገበ።

    ተጓዦቹ በማሊ የሙስሊሞች ፌስቲቫል ላይ ታድመው እየተመለሱ ነበር።

    መንገደኞቹ በኒጀር እና በአልጄሪያ መካከል ከምትገኘው ቁልፍ ሥፍራ አሳማካ በ80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሳሉ ውሃ እንዳለቀባቸው ተገልጿል።

    የአግዴዝ አገረ ገዢ ባወጡት መግለጫ “በጣም ሞቃታማ በሆነው ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ ገጠማቸው። የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ስላላገኙ በሕይወት መቆየት ከባድ ነው” ብለዋል።

    አብረው በመጓዝ ላይ ከነበሩት መካከል ሁለቱ ብቻ ተርፈዋል።

    መኪናቸው ከማሊዋ ቴለሀንደክ ከተማ ከተነሳ በኋላ መንገዱን እንደሳተ ተገልጿል።

    ለቀናት ያህል አሽከርካሪው እና ተሳፋሪዎች መኪናውን ለመጠገን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

    “መኪናውን መሥራት አልቻሉም፤ ውሃም አልቆባቸው ነበር። በከባድ ሙቀት ውስጥ ታፍነው ነበር። መኪናው አጠገብ ብዙ አስከሬኖች ተገኝተዋል” ይላል መግለጫው።

    ሟቾቹ በጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል።

    መኪናው ከተበላሸበት ሥፍራ በቅርብ ርቀትም ሌላ 60 ሰዎች የጫነ ተሽከርካሪ ብልሽት ገጥሞት ተገኝቷል። ተሳፋሪዎች መኪናውን ለመሥራት ለሦስት ቀናት ሞክረው አልተሳካላቸውም።

  4. ኢራን ከአሜሪካ ጋር መግባባት እንደተደረሰ የታገደባት ግማሽ ሀብቷ እንዲለቀቅ ጠየቀች

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው ድርድር መግባባት ላይ ሲደርስ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከታገደባት ሀብት ግማሽ ያህሉ እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነገረ።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ እና የአገራቸው ተደራዳሪ ቡድን አባላት እንዳሉት ከአሜሪካ ጋር “የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈረመ ወዲያውኑ ከታገደባት 50 በመቶው ሀብት እንዲለቀቅላት የኢራን እስላማዊ ረፐብሊክ ጠይቃለች” ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ማቅረባቸውን አመለክተዋል።

    መጀመሪያ ግማሹ ሀብት ከተለቀቀ በኋላ “ቀሪው በተወሰነ ጊዜው ውስጥ፤ በእኛ ግምት ከአንድ ወይም ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲለቀቅ” እንደሚፈልጉ መጠየቃቸውን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መህር ለተባለው የኢራን ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም የታገደውን የኢራን ሀብት ማስለቀቅ ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ወሳኝ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ምን ያህሉ ገንዘብ መጀመሪያ ላይ እንደሚለቀቅ እና ቀሪው በምን ያህል ጊዜ እንደሚለቀቅ በድርድር የሚወሰን ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ ግን ሊደረስ በሚችለው ስምምነት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ምንም ዓይነት ገንዘብ ለኢራን እንደማይለቀቅ ከዚህ ቀደም አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም "ከኢራን ጋር ስምምነት የሚደረስ ከሆነ፣ ባራክ ኦባማ እንዳደረገው የኒውክሌር ስምምነት ተፈርሞ ለኢራን ክምር ገንዘብ የሚያስገኝ ሳይሆን ጥሩ ስምምነት ነው የሚሆነው” በማለት ኢራን የታገደባትን ሀብቷን በምትፈልገው መጠን የማግኘት ፍላጎቷን ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል።

  5. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱበትን የሰላም ስምምነት ሄዝቦላህ እንደማይቀበል ማስታወቁን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።

    የዛሬው የዋጋ ንረት የታየው የኦማን ነዳጅ መጫኛ አካባቢ ፍንዳታ በመነሳቱ የነዳጅ ጭነት ከመቋረጡ ጋር በተያያዘም ጭምር ነው።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ከዚህ ቀደም የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያድሱ ከማስታወቃቸው በተጨማሪ በሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላህ እንቅስቃሴ የሚገደብበት የደኅንነት ቀጣና ለመፍጠርም ተስማምተዋል።

    ሄዝቦላህ ግን ስምምነቱን “ለሊባኖስ አሳፋሪ እና እርባና ቢስ” በሚል እንደማይቀበለው አስታውቋል።

    የሄዝቦላህ መሪ “ሄዝቦላህ ተኩስ አቁሞ ተዋጊዎቹን ከደቡብ ሊባኖስ የሚያስወጣበት ስምምነት የመሸነፍ ያህል ነው፤ የእስራኤልንም ዓላማ ያሳካል” ማለታቸውም ተዘግቧል።

  6. እስራኤል ጋዛ ውስጥ በርካታ የሐማስ የደኅንነት ባለሥልጣናትን መግደሏን አስታወቀች

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት እና የአገር ውስጥ ደኅንነት ተቋም የሆነው ሺን ቤት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሌሊቱን በተካሄዱ ዘመቻዎች የሐማስ “ጠቅላላ የደኅንነት አገልግሎት” የሚባለው ኃይል በርካታ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን አስታወቁ።

    “የጋዛ ጠቅላላ ደኅንነት አገልግሎት” የሚባለው ኃይል በሐማስ ውስጥ ያለ ምሥጢራዊ ቡድን ሲሆን ኃላፊነቱም የሐማስን መሪዎች መጠበቅ እና ድጋፍ መስጠት መሆኑን እስራኤል ገልጻለች።

    የዚህ ኃይል ዋነኛ ኃላፊነቶች በሐማስ መሪዎች መካከል ግንኙነት እና ቅንጅት እንዲኖር ማድረግ፣ ጥበቃ ማድረግ እና ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ማጓጓዝ፣ መረጃ ማሰባሰብ እንዲሁም የሐማስ መሪዎች ለሚሰጡት ውሳኔ የደኅንነት መረጃ መስጠትም ይካተቱበታል።

    ከእስራኤል ጦር እና ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሺን ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የጠቅላላ ደኅንነት ቡድኑ ምክትል አዛዥ የሆነው ሐሳን ራባህ ሐሳን ላባዳ በተፈጸሙት ጥቃቶች ተገድሏል።

    በተጨማሪም አሲም አሚን ሻላሽ ሻቢር፣ አብዱላህ አታ ዩኒስ አቡ ኩሉብ እና ሞሐማድ ኖማን ዛኪ አቡ ማርቅ በጥቃቶቹ ተገድለዋል ከተባሉት የቡድኑ ባለሥልጣናት መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

    ከዚህ በፊት በተካሄደው ጦርነት ወቅት እና ከዚያም በኋላ በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ በእስራኤል ኢላማ ተደርገው የተገደሉበት ሐማስ አሁን የእስራኤል ጦር እና የደኅንነት ተቋም ከፍተኛ አመራሮቹን ስለመግደላቸው ስላወጡት መግለጫ እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።

  7. ሄዝቦላህ የእስራኤል እና ሊባኖስን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበል አስታወቀ

    በአሜሪካ አሸማጋይነት ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበል ሄዝቦላህ አስታወቀ።

    ሄዝቦላህ ባወጣው ጠንካራ ይዘት ያለው መግለጫ ላይ መሪው ናይም ቃሲም “ድርድሮች ለሊባኖስ አሳፋሪ እና ውጤት አልባ ሆነዋል” ብለዋል።

    ስምምነቱን “በሊባኖች ሕዝብ ስም” እንደማይቀበለውም ታጣቂ ቡድኑ አስታውቋል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ከዚህ ቀደም የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያድሱ አስታውቀዋል። በሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላህ እንቅስቃሴ የሚገደብበት የደኅንነት ቀጣና ለመፍጠርም ተስማምተዋል።

    የእስራኤል እና ሊባኖስ ስምምነት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም የሚያግድ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሄዝቦላህ እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ የተወሰነ መሻሻል መስተዋሉን አስታውቀዋል።

    “ሊባኖስ ሰላም ብታገኝ መልካም ነው። ለዓመታት ጥቃት ሲደርስባት ነበር። ጥቃቱ ቢገታ ጥሩ ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው በፊት በውይይቱ ያልተሳተፉ የሄዝቦላህ መሪ “ሄዝቦላህ ተኩስ አቁሞ ተዋጊዎቹን ከደቡብ ሊባኖስ የሚያስወጣበት ስምምነት የመሸነፍ ያህል ነው፤ የእስራኤልንም ዓላማ ያሳካል” ብለዋል።

    የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆነው የቤሩት ደቡባዊ ክፍል የተስተዋለውም ተመሳሳይ ስሜት ነው።

    ቢቢሲ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ሳሚ “ይሄ የሰላም ስምምነት ሳይሆን መረታት ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣናቸው በምክር ቤት በመገደቡ ቁጣቸውን ገለጹ

    የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢራን ላይ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣናቸውን የሚገድብ ውሳኔ በማሳለፉቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምክር ቤቱን አባላት አጥብቀው ተቹ።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማብቃት የሚያስችለው ድርድር “ከመጨረሻ ደረጃ” ላይ በደረሰበት ጊዜ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጦርነት በማካሄድ ሥልጣናቸው ላይ ገደብ መጣሉን “አገር ወዳድነት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ውሳኔውን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተቀናቃኞቸቻውን ዲሞክራቶች እና እነሱን ደግፈው ድምጽ የሰጡ የፓርቲያቸው ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላትን ወቅሰዋል።

    ". . .ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማብቃት በመጨረሻው ድርድር መካከል ላይ እያለሁ አራት የሪፐብሊካን እና ሁሉም የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የምክር ቤት እንደራሴዎች ጦርነት የማካሄድ ሥልጣኔን የሚገድብ ትርጉም የለሽ ውሳኔ አሳልፈዋል” ብለዋል።

    "ድርድሩ ከምን ደረጃ ላይ እንዳለ እያወቁ እንዴት እንዲህ ያለ ከአርበኝነት የራቀ ውሳኔ ይሰጣሉ?” ሲሉ በተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

    ከዚህ ቀደም ብዙም ባልታየ ሁኔታ የአሜሪካ ምር ቤት ረቡዕ ዕለት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ያቀረቡትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጦርነት የሚገድብ የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ ድምጽ ሰጥተዋል።

    ይህ ውሳኔ በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ ዲሞክራቶች የ211 አባላት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ አራት የትራምፕ ፓርቲ አባላትም ደፈግወውት በ215 ለ208 በሆነ የድምጽ ብልጫ ነው ተቀባይነት ያገኘው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የትራምፕን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ በተደጋጋሚ ድምጽ ቢሰጥም ተቀባይነት ሳያገን ቀርቶ ነበር። አሁን ግን አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች ውሳኔውን ቢቃወሙትም በአብላጭ ድምጽ አልፏል።

  9. የአሜሪካ ቪዛ የዘገየበት በዓለም ዋንጫ የሚሳተፈው የኢራን ቡድን ወደ ሜክሲኮ ሊጓዝ ነው

    ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ውስጥ የቆየችው የኢራን ብሔራዊ ቡድን አሜሪካ ከሜክሲኮ እና ከካናዳ ጋር በጥምረት በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የአሜሪካ ቪዛ ቢዘገይበትም ወደ ሜክሲኮ እንደሚጓዝ ተገለጸ።

    ኢራን ዜና አገልግሎት ኢርና ብሔራዊ ቡድኑን ጠቅሶ እንደዘገበው ሁሉም ተጫዋቾች እና የቡድኑ አባላት የሜክሲኮ ቪዛ ስላገኙ ቅዳሜ ዕለት ከቱርክ ተነስተው ወደዚያው ይጓዛሉ።

    በምድብ ጂ ከቤልጂየም፣ ከግብፅ እና ከኒው ዚላንድ ጋር የተደለደለው የኢራን ብሔራዊ ቡድን ከሜክሲኮ በተጨማሪ አሜሪካ ውስጥ ስለሚጫወት የአሜሪካ ቪዛ ያስፈልገዋል።

    ኢራን ከኒው ዚላንድ እና ከቤልጂየም ጋር የምታደርጋቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሎስ አንጀለስ ውስጥ የምታካሂድ ሲሆን ከግብፅ ጋር ደግሞ ሲያትል ውስጥ ትጋጠማለች።

    ምንም እንኳን የብሔራዊ ቡድኑ ቀዳሚ ጨዋታዎች በአሜሪካ ከተሞች ውስጥ የሚካሄዱ ቢሆንም የቡድኑ አባላት አስካሁን የአሜሪካ ቪዛ አላገኙም።

  10. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ‘ጠላት በጦር ሜዳ ተሸንፏል’ ካሉ በኋላ መከፋፈል እንዳይኖር አሳሰቡ

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ኖጅታባ ኻሜኒ ሐሙስ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት ‘ጠላቶቻችን በጦር ሜዳ ተሸንፈዋል’ ካሉ በኋላ አሁን ደግሞ የሕዝቡን ጥንካሬ ለማፍረክረክ እና መከፋፈል ለመፍጠር እየሞከሩ ነው አሉ።

    ኻሜኒ ኢራናውያን አገሪቱ በተጋፈጠችው ስጋት ፊት ብሔራዊ አንድነት እንዲያሳዩ ጥሪ አስተላልፈው በሕዝብ መካከል ተስፋ መቁረጥን ወይም መከፋፈልን መፍጠር ጠላትን መርዳት ነው ብለዋል።

    የጠቅላይ መሪው መልዕክት የተነበበው የእስላማዊ ሪፐብሊክ መስራች የሆኑትን ሩሆላህ ኻሜኒን የሚዘክረው ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ነው።

    ሞጅታባ ኻሜኒ ሥልጣን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በአደባባይ ታይተው አያውቁም።

    ከዚህ በፊት የሰጧቸው የተለያዩ መግለጫዎች በጽሑፍ የቀረቡ ሲሆን ስላሉበት ሁኔታ ወይንም በአገሪቱ አስተዳደር ውስጥ ስላላቸው የዕለት ተዕለት ቁጥጥር በተመለከተ ቀጥተኛ ማስረጃ የለም።

  11. ቻይና ታይዋንን የጎበኙ አራት የኒው ዚላንድ የሕዝብ እንደራሴዎች ላይ እገዳ ጣለች

    ቻይና አራት የኒው ዚላንድ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ታይዋንን በመጎብኘታቸው ለአንድ ዓመት እገዳ እንደጣለችባቸው የኒውዚላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የሕዝብ እንደራሴዎቹ እገዳው እንደተጣለባቸው ያወቁት የቻይና ኤምባሲ በግንቦት ወር ከጉብኝታቸው ሲመለሱ ይቅርታ ከጠየቁ ሊቀነስ ወይንም ሊነሳላቸው እንደሚችል ከገለጸላቸው በኋላ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ቻይና ታይዋን ደሴትን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥር ሲሆን ከየትኛውም አገር ጋር የውጭ ግንኙነት እንድታደርግ አትፈቅድም።

    ቻይና በኒው ዚላንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላይ እገዳ ስትጥል ይህ የመጀመርያዋ ነው።

    የኒው ዚላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዊንስተን ፒተርስ በቻይና ውሳኔ “መደነቃቸውን” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ “የኒው ዚላንድ የፓርላማ አባላት ታይዋንን ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጎብኝተዋል፤ እናም እንደዚህ ያሉ ጉብኝቶች ከኒው ዚላንድ አንድ ቻይና ፖሊሲ ጋር የሚቃረኑ አይደሉም” ብለዋል።

    በኒው ዚላንድ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ እገዳው የፓርላማ አባላቱ “የቻይናን አሳሳቢ ጉዳዮች ችላ በማለታቸው” እና እንደ ፓርላማ አባልነታቸው ታይዋንን ለመጎብኘት ፍላጎት በማሳየታቸው የተወሰደ እርምጃ ነው ብሏል።

    ጉብኝቱ ለታይዋን ገዥው ዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ እና የታይዋን የነጻነት ኃይሎች “የተሳሳቱ ምልክቶችን ልኳል” ሲል ኮንኖ “በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት” ነው ብሏል።

  12. እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ዘመቻዋን እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናገሩ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ ጦራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያካሄደውን ዘመቻ ለጊዜው እንደሚቀጥል አስታወቁ።

    ሚኒስትሩ አክለውም ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን መመለስ አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።

    የሚኒስቴሩ አስተያየት የተሰማው ሊባኖስ እና እስራኤል በዋሺንግተን የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

    ስምምነቱ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ እና ጥቃት መፈጸም ከማቆሙ ጋር የተገናኘ ነው።

    ካትዝ በመግለጫቸው ላይ ወታደሮቻቸው በደቡባዊ ሊባኖስ የደህንነት ቀጣና በሚባሉት እና 900 ዓመት እድሜ አለው በተባለው እና እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በተቆጣጠረችው ቤውፎርት አምባ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ ”እስራኤል “በአካባቢው የሚገኘውን የሽብርተኛ መሠረተ ልማት ማፈራረስ” እንደምትቀትል ተናግረው “በእስራኤል ማኅበረሰቦች እና ግዛት ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመ ምላሽ የመስጠት መብት እንዳለን አሜሪካም ትደግፈዋለች” ብለዋል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል ረቡዕ ዕለት በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል።

    ሁለቱ አገራት በሚያዚያ ወር ግጭት የማቆም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በግንቦት ወር የተራዘመ ቢሆንም ግጭቶች ግን ቀጥለዋል።

  13. እስራኤል እና ሊባኖስ ሄዝቦላህ ጥቃቱን የሚያቆም ከሆነ የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማሙ

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁሙ ተግባራዊነት ላይ መስማማታቸውን አስታወቀ።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ ስምምነቱ በኢራን ከሚደገፈው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ የሚሰነዘረውን ጥቃት እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን "በፍፁም ማቆም ላይ የተመሠረተ" ነው ብሏል።

    ረቡዕ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሄዝቦላህም ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶችን ተኩሷል።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመገለጫው አክሎም “ሁሉም አገራት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ያለው የወደፊት ግንኙነት በሁለት ሉዓላዊ መንግሥታት መካከል መወሰን እንዳለበት ተስማምተዋል። በመንግሥታዊ ወይንም መንግሥታዊ ባልሆኑ ማንኛውም አካላት ሊባኖስን እንደማስያዣ ለመጠቀም የሚደረግን ጥረት ውድቅ አድርገዋል” ብሏል።

    ስምምነቱ እስራኤል በምትቆጣጣረው ደቡባዊ ሊባኖስ ከሊታኒ ወንዝ እስከ ድንበሩ ካለው አካባቢ “ሁሉም የሄዝበላህ ተዋጊዎች እንዲወጡ” ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል።

    አሜሪካ “የሊባኖስ መከላከያ የሚቆጣጠረው እና ማንኛውም ከመንግሥት ውጪ የሆነን ታጣቂ የሚያስወገድበትን የሙከራ ዞኖች” እንዲመሠረት ድጋፍ እንደምታደርግም መግለጫው ጠቅሷል።

    በሁለቱ አገራት መካከል ይህ ስምምነት የተደረሰው ሰኞ ዕለት ሄዝቦላህ እስራኤልን የማያጠቃ ከሆነ በምላሹ ቴል አቪቭ ቤይሩትን እንደማትደበድብ ዋስትና መስጠቷን እና ከፊል ተኩስ አቁም መታወጁን ሊባኖስ ካሳወቀች በኋላ ነው።

    ሁለቱ አገራት ዳግም ሰኔ 15፣2018 ዓ.ም. ተገናኝተው “አጠቃላይ ሰምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት” ቀጠሮ ይዘዋል።

    ሄዝቦላህ ስለ ስምምነቱ እስካሁን ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም።

  14. ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር የተወዛገቡት ጠ/ሚኒስትር ኔታኒያሁ ኢራን “በእሳት እየተጫወተች ነው” አሉ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በእሳት እየተጫወተች ነው ያሏት ኢራን ያላትን የዩራኒየም ክምችት ለማስወገድ እንዳልተስማማች ነገር ግን የሚደርስባት ጫና እየበረታ መሆኑን ተናገሩ።

    ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር መወዛገባቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትራምፕ ጋር በኢራን ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም እንዳቸላው ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሲኤንቢሲ በሰጡት ቃለ ምለልስ ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ድርድር ካለስኬት ቢቋጭ ብዙም እንደማያሳስባቸው እና የኢራን ጉዳይ ያላበቃ ቢሆንም ግን በከፍተኛ ሁኔታ መዳከሟን ገልጸዋል።

    ከኢራን ጋር ዳግም ወደ ሙሉ ጦርነት የመግባቱ ጉዳይ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚወሰን መሆኑን እና ”የአሜሪካ እና የእስራኤል ኃይሎች ዝግጁ ናቸው። ኢራንም ይህንን ማወቅ አለባት፤ እነሱም ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን በግልጽ እንደሚታየው በእሳት እየተጫወቱ ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደችው ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለፉት ቀናት ሲዘገብ እንደነበረው በሁለቱ መሪዎች መካከል ጠንከር ለያ ንግግር መደረጉ ተገልጿል።

    ፕሬዝዳን ትራምፕ “ፖድ ዋን ፎርስ” ከተባለ ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኔታኒያሁ ጋር የጋለ ምልልስ ማድረቸጋውን አረጋግጠዋል።

    “አዎ [ጠንካራ ውይይት] አድርገናል። በጣም ተናድጄ ነበር፤ ሊባኖስ ውስጥ [ኔታኒያሁ] እያካሄደው ባለው ያልተቋረጠ ጦርነት ተረብሼ ነበር” በማለት ውይይታቸው ጠንከር ያለበትን ምክንያት አስረድተዋል።

    የኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ስለተደረገው የስልክ ምልልስ በይፋ ከመናገር ቢቆጠብም ጠቅላይ ሚኒስረሩ ግን “እንደ ጥሩ ቤተሰብ አንዳንድ ጊዜ ስልታዊ ልዩነቶች አሉን” በማለት ጉዳዩን በማጣጣል የጋራ ዘላቂ አላማ እንዳላቸው አመልክተዋል።

    ኔታኒያሁ ጨምረውም ከኢራን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ዘወትር ስመምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

  15. ኢራን በኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽማ አንድ ሰው መገደሉ ተነገረ

    በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተፈጸመ የኢራን የድሮን ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን እና 60 ሰዎች መቁሰላቸውን አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን ተናገሩ።

    የኩዌት የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥቃቱን “የኢራን የወንጀል ድርጊት” ሲሉ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ በጥቃቱ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጥቃቱ አሜሪካ ዛሬ ጠዋት በኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከብ እና በቄሽም ደሴት ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ መሆኑን ገልጿል። ኢራን ቀደም ብላ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ወደታራዊ ሰፈሮችን ዒላማ ማድረጓን አሳውቃ ነበር።

    አሜሪካ ጠዋት ላይ “ራስን የመከላከል” እርምጃ በኢራን ላይ መውሰዷን እና ወደ ኩዌት እና ባህሬን የተወነጨፉ የኢራን ሚሳኤሎችን መትታ ማክሸፏን ገልለጻች።

    በኩዌት አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመው የኢራን የድሮን ጥቃት የተገደለው ግለሰብ ሕንዳዊ ዜግንት ያለው መሆኑ ታውቋል።

    የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን በማውገዝ በተጨማሪም ሌሎች በርካታ ዜጎቹ በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

    ዛሬ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተካሄደው የአጸፋ ጥቃት መቋጫ ያላገኘው የሁለቱን አገራት ድርድር እንዲቋረጥ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

  16. ሩሲያ በምትቆጣጠረው የዩክሬን ግዛት በአውቶብስ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገደሉ

    ሩሲያ በምትቆጣጠረው የዩክሬን ግዛት አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን እና አስራ አንድ መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

    ክሬምሊን በዩክሬን ምሥራቃዊ ዶኔትስክ ክልል የሾመቻቸው ዴኒስ ፑሺሊን ጥቃቱ ከሞስኮ ወደ ክሬሚያ ሲምፎሮፖል ይጓዝ በነበረ አውቶቡስ ላይ ረቡዕ ማለዳ መድረሱን ገልጸዋል።

    በተያያዘ ዜና ረቡዕ ማለዳ በሴይንት ፒተርስበርግ ጭስ የታየ ሲሆን፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የከተማዋ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።

    ጥቃቱ የተፈጸመው ሩሲያ ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚክ ፎረም በምታዘጋጅት ወቅት ነው።

    ሩሲያ ትናንት ማክሰኞ በዩክሬን ከተሞች ላይ በርካታ የድሮን ጥቃቶች ፈጽማ ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 22 ሰዎች ተገድለዋል።

    ፑሽሊን በድሮን ጥቃት በደረሰበት አውቶብስ ሰባት ሰዎች መግደላቸውን ገልጸው ጉዳት የደረሰባቸው 11 ሰዎች የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

    ዩክሬን በአውቶቡስ ላይ ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

    ሩሲያ ሌሊቱን ከዩክሬን የተነሱ 350 ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።

  17. ኢራን በኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት በርካቶች መጎዳታቸው ተገለጸ

    የኢራን ድሮኖች የኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ረቡዕ ማለዳ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በረራዎች መቋረጣቸው ተገለጸ።

    በኩዌት የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ቴህራን እና ዋሺንግተን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ሲሆን በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውም ተገልጿል።

    ሁለት የኢራን ዜና ወኪሎች ቴህራን የተኩስ አቁሙን ለማራዘም ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ንግግር ማቋረጧን ማክሰኞ ዕለት ዘግበዋል።

    ትራምፕ ግን ዘገባውን አጣጥለው ንግግሮች እየተካሄዱ ናቸው ብለዋል።

    የኩዌት መከላከያ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ሳዑድ አብዱላዚዝ አል ኦታእቢ “በርካታ ጥቃት ፈጻሚ ድሮኖች” የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃን ዒላማ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

    በጥቃቱ የመንገደኞች ማስተናገጃው ክፉኛ መጎዳቱን የገለጹ ሲሆን “በርካታ ሰዎችን” አቁስሏል ብለዋል።

    የአውሮፕላን ማረፊያው በኢራን ጦርነት ምክንያት ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ከሁለት ቀናት በፊት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. ነበር።

    ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የአሜሪካ ጦር ኢራን በኩዌት እና ባህሬን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ጠቅሶ በወታደራዊ ተቋማቷ ላይ የአጸፋ ምላሽ ድብደባ ማካሄዱን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር አክሎም በኩዌት የሚገኙ የጦር ሰፈሮቹን ዒላማ ያደረጉ “በርካታ ድሮኖችን መትተን ጥለናል” ሲል አስታውቋል።

    የኢራን ፈጥኖ ደራሽ አብዮታዊ ዘብ በባህሬን የሚገኝ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ዋና ማዘዣ እና ኩዌትን በስም ሳይጠቅስ ሌላ አገር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    አክሎም ጥቃቱን የፈጸመው የአሜሪካ ጦር የጣለውን እገዳ ለማለፍ እየተንቀሳቀሰች የነበረች ነዳጅ ጫን መርከብ ሞተር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎመሆኑን ጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው “ከዚህ በፊት ለማንኛውም ጥቃት የምንሰጠው ምላሽ የተለየ እና የከፋ እንደሚሆን ተናግረን በነበረው መሠረተ እረምጃውን ወስደናል” ብሏል።

  18. አሜሪካ የኢራን ግዙፍ የክሪፕቶ መገበያያ ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ማዕቀብ ጣለች

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት የኢራን ግዙፍ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ የቴህራን መንግሥት እና ስማቸው በጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈሩ ኩባንያዎች የምዕራባውያንን ማዕቀብ ለማለፍ ያገለግላል በሚል ማዕቀብ ጣለች።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል በግንቦት ወር ኖቢቴክስ (Nobitex) የሚባለው የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ከአገሪቱ ሕጋዊ የገንዘብ ሥርዓት ጋር በትይዩነት ለማዕከላዊ ባንኩ እና ለአብዮታዊ ዘቡ እያገለገለ መሆኑን በመጥቀስ ዘግቦ ነበር።

    ዘገባው አክሎም ኖቢቴክስ ኢንተርኔት በተዘጋበት ወቅትም አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አመልክቶ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠሩ ግብይቶችን ማካሄዱን አሳይቷል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ “የኢራን ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ ባለበት ወቅት አገዛዙ ለራሱ እኩይ አጀንዳው የዲጂታል መገበያያዎችን ማዕቀብ ለማምለጥ እና ሃብት ከአገር ውጭ ለማሻገር መጠቀም መርጧል” ብለዋል።

    የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው ኖቢቴክስ ከኢራናውያን ቤተሰቦች በተገኙ ወንድማማቾች የተመሠረተ ሲሆን፣ ከአዲሱ ጠቅላይ መሪ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ማዕቀብ መጣሉን ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል።

    ኖቢቴክስ ለኢራን መንግሥት “ጠንካራ ድጋፍ” እየሰጠ ነው፤ እንዲሁም ለአብዮታዊ ዘቡ እና ለአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ “በርካታ ቁጥር ያለው” የዲጂታል ግብይቶችን አመቻችቷል ብሏል።

    "በኢራን ውስጥ አሜሪካ ጦርነት መክፈቷን ተከትሎ ኖቢቴክስ የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቋረጥም የአገዛዙን ሀብት ለመከላከል በኢራን ውስጥ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ለማንቀሳቀስ ሚና ተጫውቷል።"

  19. እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ከፊል ተኩስ አቁም ከተስማማች በኋላ በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃቶችን ፈጸመች

    ኢራን ማክሰኞ ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽመውን ጥቃት የቀጠለች ቢሆንም በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላህ ጋር የደረሰችውን ከፊል ተኩስ አቁም ተከትሎ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ላይ ጥቃት አለመፈጸሟን ተገለጸ።

    ሊባኖስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሰኞ አመሻሽ ላይ ይፋ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት የማይፈጽም ከሆነ ጦሯ ቤይሩትን እንደማያጠቃ በማሳወቃቸው ድብዳው አልተፈጸመም ብላለች።

    ኢራን በበኩሏ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ምትፈጽመው ጥቃት ከአሜሪካ ጋር ጦርነቱን ለማቆም የምታደርገውን ድርድር አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስታውቃለች።

    የተኩስ አቁሙ ይፋ ከሆነ በኋላ የእስራኤል ጦር ወደ አገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተተኮሱ ተወንጫፊዎችን ማክሸፉን አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የእስራኤል ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፣ እስራኤል በበኩሏ ከባድ ጥቃት ማድረሷን አስታውቃለች።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እስራኤል በጃባል አመል ሆስፒታል አጠገብ የሚገን ሕንጻ ላይ ሰኞ ከሰዓት ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አራት ሰዎች መገደላቸወን እና 127 መጎዳታቸውን አስታውቋል።

    ከተጎዱት መካከል 39 የሆስፒታል ሠራተኞች የሚገኙበት ሲሆን፣ አራቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ተብሏል።

    የእስራኤል ጦር በአካባቢው የሚገኝ “የአሸባሪው ሄዝቦላህን መሠረተ ልማት” ማጥቃቱን ገልጾ፤ በሆስፒታሉ ላይ ጉዳት ቢደርስም “ዒላማ አልነበረም” ሲል አስተባብሏል።

    ሄዝቦላህ ሰላማዊ ሰዎች መሠረተ ልማቶች እና ሕዝብ በሚኖርባቸው ቦታዎች ላይ ይሸሸጋል ሲል ማስረጃ ሳያቀርብ ይወነጅላል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 128 የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እና የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን በአምቡላንሶች እና በሕክምና ተቋማት ላይ ደግሞ 159 ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።

    ሚኒስትሩ አክሎም ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 3,468 ሰዎች መገደላቸውነ የገለጸ ሲሆን፣ ቁጥሩን ግን ሰላማዊ ሰዎችን እና ተዋጊዎች አልለየም።

    የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የእስራኤል ጦር ከአገሪቱ አንድ ስምንተኛ አካባቢ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ለቅቀው እንዲወጡ ካስጠነቀቀ ወዲህ 1 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል።

    እስራኤል 25 ወታደሮቿ እና አራት ሰላማዊ ሰዎች በዚህ ጦርነት ወቅት መገደላቸውን አስታውቃለች።

  20. የተኩስ አቁም ድርድሩ በተደናቀፈበት ሁኔታ አሜሪካ እና ኢራን ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ

    የአሜሪካ ጦር በኢራን ደሴት ላይ ‘ራስን የመከላከል’ ጥቃት መፈጸሙን እና ወደ መርከቦች እና የባሕረ ሰላጤው አገራት የተተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን መትቶ መጣሉን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) በሆርሙዝ ወሽመጥ እና ኣለይ በቄሸም ደሴት ላይ “ኢራን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ልትፈጽም የነበረውን የጥቃት ሙከራ ተከትሎ” ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል።

    ኢራን ወደ ኩዌት ሁለት ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ነገር ግን የታለመላቸውን ስፍራ ሳይደርሱ መውደቃቸውን እንዲሁም ሦስት ወደ ባሕሬን የተወነጨፉ ደግሞ በአየር ላይ እንዲከሽፉ መደረጋቸውን ገልጿል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በቄሸም ደሴት በሚገኝ የግንኙነት ማማ ላይ ለተፈጸመ ጥቃት በሰጠው ምላሽ በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን እና ሂሊኮፕተሮችን ማጥቃቱን በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በኩል አስታውቋል።

    ሴንትኮም በቄሸም ደሴት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የኢራን ጦር የምድር መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ ኢራን “በቀጣናው ውሃዎች ላይ የማለፍ መብት ያላቸው ሰላማዊ ባሕረተኞች” ላይ የተኮሰቻቸውን ሦስት ድሮኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

    አብዮታዊ ዘቡ “የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ማወክ ጠብ አጫሪውን የአሜሪካ ጦር ከባድ ዋጋ ያስከፍለዋል” ሲል በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

    ኢራን በተደጋጋሚ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው ባሕሬን እና ኩዌት ላይ ጥቃቶቸን ፈጽማለች።

    ቀደም ሲል ሴንቲኮም አሜሪካ የጣለችውን እገዳ ተከትሎ ወደ ኢራን እየቀዘፈ የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ማጥቃቱን እና እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉን አስታውቋል።

    የአሜሪካ አየር ኃይል የቦትስዋናን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በተደጋጋሚ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ማለቱን ተከትሎ በሞተሩ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተገልጿል።

    ሴንቲኮም ማክሰኞ ዕለት መርከቦ ላይ ጥቃት ሲፈጽም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ያሠራጨ ሲሆን የኢራን ጦር በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።

    ዕዙ በመግለጫው ከአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 13 ጀምሮ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማገዷን አስታውሶ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 122 መርከቦች አቅጣጫቸውን አንዲቀይሩ እና እንዲመለሱ መደረጋቸውን አሻፈረኝ ያሉትም ሞተራቸው እነዳይሠራ መደረጉን አስታውቋል።

    ቢቢሲ የቦትስዋናን መንግሥት አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም አልተሳካም።

    አሜሪካ ይህንን ጥቃት የፈጸመችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በአገሪቱ ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርበው ስለ ኢራን ጦርነት ከተጠየቁ በኋላ ነው።