በምዕራብ አፍሪካ 58 የሳይበር ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከኮምፒውተር ፊት ለፊት የተቀመጠ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢንተርፖል ጃካል IV የተባለው ዘመቻ የዓለም አቀፍ ትብብርን ያሳያል ብሏል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በ22 አገሮችና ስድስት አህጉራት በተካሄደ ዘመቻ ከምዕራብ አፍሪካ የተደራጁ የሳይበር ወንጀል ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው 58 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

"ኦፕሬሽን ጃካል አይቪ (IV)" ተብሎ የተሰየመው ይህ ዘመቻ በዓለም አቀፍ የፖሊስ ኤጀንሲ፣ ኢንተርፖል የተመራ ሲሆን በፍቅር እና ኢንቨስትመንት ስም የሚያጭበረብሩ ግለሰቦችን ዒላማ አድርጓል።

በተጨማሪም 263 ተጠርጣሪዎችን መለየቱን አስታውቋል።

ኢንተርፖል ዘመቻውን ያካሄደው ናይጄሪያ ውስጥ ከፍተኛ ስም እና ዝና ያፈሩት 'ብላክ አክስ' የተሰኙ የወንጀል መረብ አባላት ለሳይበር ተኮር የፋይናንስ ማጭበርበር "ከፍተኛ ድርሻ" እንዳላቸው ስለታመነ እና እየጨመረ ላለው ዓለም አቀፍ ስጋት ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተናግሯል።

ዘመቻው እነዚህ ቡድኖች ታዳጊዎችን ዒላማ ለማድረግ እድሜያቸው 14 የሆኑ ታዳጊዎችን ጨምሮ ወሲብ ነክ መልዕክቶችን በመላክ እንዴት እንደሚያማልሉ የሚያሳይ አዳዲስ መንገዶችን መለየት መቻሉን ጠቅሷል።

ኦፕሬሽን ጃካል IV የተካሄደው እአአ ከኀዳር 2025 እስከ ሰኔ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ቡድኖቹ ሕጋዊ ያልሆነን ገንዘብን እንዴት ወደ ሕጋዊ መስመር እንደሚያስገቡ፣ እንደ የክሪፕቶ ምንዛሬ እና የኢሜይል ማጭበርበር ያሉ የሳይበር ወንጀሎችን እንዴት እንደሚፈጸሙ መርምሯል።

ኢንተርፖል እንደገለጸው አጭበርባሪዎቹ ብዙውን ጊዜ ዒላማ የሚያደርጉት "እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ጡረተኞችን ነው።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ድንበር ተሻግሮ የሚገኙ ሕገ ወጥ የገንዘብ ፍሰቶችን በመከተል፣ የተደራጁ ወንጀሎችን መስመር እና የወንጀል መረቦች ከእንቅስቃሴያቸው ትርፍ ለማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው እያደረግን ነው" ሲሉ የኢንተርፖል የፋይናንስ ወንጀል ማዕከል ዳይሬክተር ቶሞኖቡ ካያ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

"ኦፕሬሽን ጃካል IV የዓለም አቀፍ ትብብርን አቅም ያሳያል።"

በዘመቻው ወቅት ኢንተርፖል ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን እና የመረጃ ልውውጥን በማገዝ ድጋፍ አድርጓል።

በተጨማሪም ከተሳታፊ አገሮች ጋር የገንዘብ ዝውውር ምርመራዎችን ለመደገፍ የሚያስችል ልዩ ስልጠና ሰጥቷል።

ኢንተርፖል እንደገለጸው የኦፕሬሽን ጃካል IV ጉዳይ በርካታ ገጽታዎች በምርመራ ላይ ያለ ቢሆንም የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶቹ በአርጀንቲና፣ በጣሊያን፣ በሮማኒያ እና በደቡብ አፍሪካ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።

በደቡብ አፍሪካ፣ በፍቅር እና በኢንቨስትመንት ስም ከሚፈጸም ማጭበርበር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰባት ድረ ገጾችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ኢንተርፖል በዘመቻው ወቅት የአካባቢውን ባለሥልጣናት ለመደገፍ በጆሃንስበርግ ተገኝቷል።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ 39 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ 2.67 ሚሊዮን ዶላር ሲይዝ 257 የባንክ ሂሳቦችን ዘግቷል።

ኢንተርፖል አክሎም ከሳይበር ማጭበርበር በተጨማሪ የምዕራብ አፍሪካ የወንጀል መረቦች በሌሎች ከባድ እና የአመጽ ወንጀሎችም ተሳትፈዋል ሲል አስታውቋል።

የኦፕሬሽን ጃካል IV እአአ ከ2022 ጀምሮ ከተከናወኑ በርካታ ዘመቻዎች መካከል አንዱ ነው።

እአአ በ2024 ጃካል ሳልሳዊ ከብላክ አክስ እና ከሌሎች ተባባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው 300 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

ብላክ አክስ በዓለም ዙሪያ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የወሲብ ንግድ እና የግድያ ተግባራት ላይ የተሰማራ የወንጀል መረብ ነው።

ናይጄሪያ ዋና የመመልመያ አገር ስትሆን ብዙዎቹ አባላቱ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የተማሩና በትምህርት ቤት ሳሉ የተመለመሉ ናቸው።