በትግራይ ክልል በረዶ የቀላቀለ ዝናብ አንድ ታዳጊን ገድሎ፤ 10 ሺህ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን ቀይሕ ተኽሊ ወረዳ በረዶ እና ኃይለኛ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ምክንያት የአንድ ታዳጊ ሕይወት እንዳለፈ እና 10 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በበረዶው ምክንያት እንስሳት መሞታቸውን፣ ቤቶች መፍረሳቸውን እና ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል መውደሙን ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢኮኖሚ ልማት ኃላፊው ሀብቶም ዘነበ ገልጸዋል።

በሰዎች፣ እንስሳት፣ ሰብል እና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው ኃይለኛ ዝናብ የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ዕለት ቢሆንም እስካሁን ድረስ "በረዶው እንዳልቀለጠ" አስረድተዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት በረዶው የዘነበው አመሻሽ ከ12 ሰዓት ተኩል ገደማ ላይ ነው። "በጣም ኃይለኛ፣ ታይቶ የማይታወቅ በረዶ ነው ያጋጠመን" የሚሉት አቶ ሀብቶም፣ በወረዳው የሚገኙ "አምስት ቀበሌዎች እና ሰባት ጎጥ" ውስጥ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሀብቶም ገለጻ፣ በዕለቱ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሌሎች ወረዳዎች ውስጥም ተመሳሳይ ክስተት ቢያጋጥምም የከፋ ጉዳት የደረሰው በቀይሕ ተኽሊ ወረዳ ነው።

"እስካሁን በሌላ ወረዳ የሞተ ሰው አልሰማሁም" ሲሉም በወረዳው ያጋጠመው ክስተት "በመጠኑ እና በክብደቱ" እንደሚበልጥ አስረድተዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት ሕይወቱ ያለፈው ከብቶችን በመጠበቅ ላይ የነበረ የ12 ዓመት ታዳጊ ነው። ታዳጊው በረዶ የቀላቀለውን ዝናብ ተከትሎ በመጣ ጎርፍ መወሰዱንም አክለዋል።

"በበረሀ እያለ ገና ቤት ሳይገባ ነው በበረዶውም፣ በጎርፉም አደጋ የደረሰበት" ብለዋል። "ሰዓቱ አመሻሽ ስለነበረ ነው እንጂ ብዙ ሰው አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር" ሲሉም የበለጠ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበት ዕድል እንደነበር አመልክተዋል።

በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ፍየሎች እና ከብቶችን ጨምሮ 201 እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል። በዝናቡ ምክንያት 12 ቤቶች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸውን የሚናገሩት አቶ ሀብቶም፤ 625 ቤቶች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።

ይህን ክስተት ተከትሎ "2,134 አባወራዎች" ወይም "10,556 ሰዎች" ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። አብዛኛዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች "ቤተሰቦቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው" ጋር መጠለላቸው እንዲሁም ሌሎች ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ እንዳሉም ጠቅሰዋል።

በረዶው በማደግ ላይ የነበረ እንዲሁም የተዘራ አዝዕርትን "ሙሉ በሙሉ" ማውደሙንም ገልጸዋል። "በዚህ አደጋ ወደ 1059.5 ሄክታር የተለያዩ አዝርዕት መቶ ፐርሰንት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በመስኖም 115.6 ሄክታር በተመሳሳይ መቶ ፐርሰንት ጉዳት ደርሷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው እንደሚያስረዱት ከወደመው አዝዕርት ውስጥ አብዛኛው ሚያዝያ ላይ በተገኘ "ትንሽ ዝናብ" ተዘርቶ "በእድገት ደረጃ ላይ" የነበረ ነው።

እንደ ምክትል አስተዳዳሪው ገለጻ፣ ይህ አደጋ የደረሰው ወረዳው የክረምት ዝናብ ሳያገኝ "46 ደረቃማ ቀናትን" ካሳለፈ በኋላ ነው። ዝናብ "ዘግይቶ እንደሚገባ፣ መሃል ላይ እንደሚቋረጥ [እና] ቶሎ ብሎ እንደሚወጣ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ይዘን ነበር" ሲሉም አስረድተዋል።

በበረዶ በተቀላቀለው ዝናብ እና ጎርፍ አዝርዕታቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች "በትልቅ ጭንቀት ውስጥ" እንደሚገኙ የሚያነሱት አቶ ሀብቶም፤ እርዳታ ካልቀረበላቸው ለበለጠ ለአደጋ እንደሚጋለጡ አስጠንቅቀዋል።

"እስካሁን የደረሰ ድጋፍ የለም። ግን የወረዳ፣ የክልል፣ የዞን የተለያዩ አመራሮች እና ባለሙያዎች መጥተው በረዶውን ስላዩት መፍትሔ ሊመጣ ነው ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ኤል ኒኖ የተባለው ከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከመደበኛወወ ውጪ ከባድ የአየር ሁኔታ እንደሚያጋጥም ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አስታውቋል።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች በዝናብ ማጠር የተነሳ ከፍተኛ ድርቅ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ከመደበኛ ከፍ ያለ በረዶና የጎርፍ መጥለቅለቅን የሚያስከትል ዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል።