ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ መንግሥት የትራምፕን ፊት የያዘ የ250 ዶላር ኖት ለማተም እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ፈቃድ የሚሰጡ ከሆነ የፕሬዝዳንቱን ምስል የሚይዝ የ250 ዶላር የገንዘብ ኖት ለማተም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የፌደራል ሕግ በሕይወት ያለ ሰው ምስል በአሜሪካ ገንዘብ ላይ እንዳይታተም ይከለክላል። ኮንግረስ ውስጥ የሚገኙ የትራምፕ አጋሮች ግን ለፕሬዝዳንቱ ልዩ ፈቃድ የሚሰጥ ሕግ አስተዋውቀዋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ለዚህ ሕግ ምላሽ ለመስጠት "ተገቢውን ዕቅድ እና ቅድመ ግምገማ እያካሄደ" መሆኑን የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ረቂቅ ሕጉን ያቀረቡት የኮንግረስ አባላት ይህ እርምጃ ዘንድሮ ለሚከበረው የአሜሪካ 250ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ተምሳሌት እንደሚሆን ይናገራሉ። ረቂቁ የሚጸድቅ ከሆነ፤ ፕሬዝዳንቱ እና አጋሮቻቸው በብሔራዊ ተቋማት እና ምልክቶች ላይ የትራምፕን ምስል፣ ስም እና አምሳያ ያሳፈሩበት አዲስ እርምጃ ይሆናል።
የ250 ዶላር የገንዘብ ኖቱ ምን አይነት ገጽታ እንደሚኖረው እስካሁን ይፋ አልተደረገም። በግምጃ ቤቱ ስር የሚገኘው እንዲሁም የአሜሪካን ገንዘብ የሚያዘጋጀው እና የሚያትመው ቢሮ ግን ንድፉ እንዲሰራ ጠይቋል።
የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ባወጡት መግለጫ "ይሕ ረቂቅ ሕግ እንዲሆን የሚፈረም ከሆነ፤ የህትመት ቢሮው ለታላቋ አገራችን 250ኛ ዓመት በዓል በአግባቡ እውቅና የሚሰጥ የ250 ዶላር መታሰቢያ ኖት ለማተም በንቃት እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የአገሪቱን 250 ዓመት በዓል በማስመልከት የትራምፕ ፊርማ በአሜሪካ ገንዘብ ላይ እንዲያርፍ መወሰኑ ይፋ ተደርጓል። በሕይወት ያለ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፊርማ በአገሪቱ ገንዘብ ላይ ሲታተም ይህ የመጀመሪያው ነው።
ባለፈው ዓመት የተዘጋጀው አዲሱ ረቂቅ ሕግ ለመሆን በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሴኔት ቀርቦ መጽደቅ አለበት።
ሐሙስ ዕለት በተካሄደ መግለጫ ላይ ሊጸድቅ ስለሚችለው አዲሱ የገንዘብ ኖት ጥያቄ የቀረበላቸው የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቤሴንት "ሁሉም ነገር" በኮንግረስ "እጅ ነው" ብለዋል። መሥሪያ ቤቱ ሕጉ የሚጸድቅ ከሆነ በሚል እየተዘጋጀ ቢሆንም የሚሰራው ሕጉን ተከትሎ መሆኑን ገልጸዋል።
የአገሪቱን 250ኛ ዓመት የነጻነት በዓል በማስመልከት በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰብን ምሥል የሚይዝ ገንዘብ ማተም "አላግበብ የሆነ ነገር ነው" ብለው እንደማያስቡም ተናግረዋል።
በአሜሪካ ሴኔት የባንክ ሥራ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሴናተር ማርክ ዋርነር ግን እቅዱን ተችተዋል።
"አሜሪካውን በነዳጅ፣ አስቤዛ፣ መኖሪያ ቤት እና የጤና አገልግሎት ዋጋ መጨመር እየታገሉ ባሉበት በዚህ ሰዓት፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የግብር ከፋዩን ገንዘብ ለማዋል ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ቤተሰቦች በየቀኑ ከሚጋፈጧቸው ተግዳሮቶች ፈጽሞ የተራራቀ ነው" ብለዋል።
"ዋይት ሀውስ የፕሬዝዳንቱን ኢጎ ለማስጠበቅ ከሚያወጣው ኃይል ውስጥ ግማሹን እንኳ ዋጋ ለማስቀነስ አውሎት ቢሆን ኖሮ አሜሪካውያን ቤተሰቦች ነዳጅ ለመሙላት የ250 ዶላር ኖት አያስፈልጋቸውም ነበር" ሲሉም ተችተዋል።
የ250 ዶላር ገንዘብ ኖት ለማተም የሚደረገው ጥረት የሚታተሙ የገንዘብ ኖቶችን ከሚዘረዝረው ሌላ የፌደራል ሕግ ጋር ሊቃረን ይችላል። ሕጉ ዝርዝሩ ውስጥ የ250 ዶላር ኖትን አላካተተም።
በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ውስጥ ትልቁ የገንዘብ ኖት በሆነው 100 ዶላር ላይ የሚታዩት ከአሜሪካ መስራቾች አንዱ የሆኑት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ናቸው።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም እንደ 500፣ 1,000 እና 10,000 ዶላር ያሉ ትላልቅ የገንዘብ ኖቶችን አሳትማ ነበር። ይሁን ከአውሮፓውያኑ 1969 በኋላ ሕትመታቸው ተቋርጧል።