የመከላከያ ክትባት ያለው የቲቢ በሽታ ለምን ዛሬም ድረስ በርካቶችን ለሞት ይዳርጋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የንጉሥ ሉዊ 15ኛ አማካሪ እና ውሽማ የነበረችው ማዳም ደ ፖምፓዶር የሞተችው በአውሮፓውያኑ 1764 ነበር። በ1830 ደግሞ በደቡብ አሜሪካ "የነጻ ታጋይ" በሚል የሚታወቀው ሳይመን ቦልቬር ኮሎምቢያ ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።
ሁለቱም የሞቱት በሳምባ ነቀርሳ (ቲቢ) ተይዘው ነው። ሳምባ ነቀርሳ በተለያዩ ዘመናት ለፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች፣ ሙዚቀኞች ኅልፈት ምክንያት ሆኗል።
ታዋቂዎቹ ደራሲዎች ኤምሊ ብሮንቴ እና አን ብሮንቴ፣ ዝነኛው አቀናባሪ ፍሬድሪክ ቾፒን እና ተጽዕኖ ፈጣሪው ጸሐፌ ተውኔት አንቶን ቼኮቭ የሞቱት በሳምባ ነቀርሳ ነው።
በ18ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን በሽታው በርካቶችን ለሞት ዳርጓል።
በ1839 ጀርመናዊው የሕክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ጆሀን ሉካስ ሾንሊን፤ በዚህ ሕመም የሞቱ ሰዎች 'ቲውበርሴልስ' የተባለ አነስተኛ ጠባሳ በሰውነታቸው በመታየቱ በሽታው ቲውበርክሎሲስ እንዲባል ሐሳብ አቅርቧል።
በዘመኑ በሽታው የሚከሰተው አንዳች መንፈስ የሰዎችን ሰውነት ሲዋሀድ እንደሆነ ይታመን ነበር።
ሰውነት ሲነጣ፣ የአካል መጠን ሲቀንስ እና ዐይን ብሩህ ሲሆን እንደ ውበት መገለጫ ይቆጠርም ነበር። የፈጠራ ሰዎች የሚገጥማቸው አሳዛኝ የሆነ የውበት መገለጫ እና የነፍስ ንጹህነት ማሳያ ተደርጎም ይወሰድ ነበር።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች የሚገጥማቸው እክል ነው ይባል እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል።
በአውሮፓውያኑ 1882 ግን አፈ ታሪኩ እውነተኛ እንዳልሆነ ይነገር ጀመር። ጀርመናዊው የማይክሮባዮሎጂ ተመራማሪ ሮበርስ ኮች በሽታው በመንፈስ የሚከሰት ወይም የጥበብ ሰዎችን የሚከሰት አለመሆኑን ተናገረ።
የሳምባ ነቀርሳ ማይኮባክቴርየም ቲዩበርክሎሲስ በተባለ ተላላፊ ዝርያ ምክንያት የሚፈጠር ሕመም መሆኑን ተመራማሪው ይፋ አደረገ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቲቢ መንስዔ ይፋ መደረጉ በዘናዊ የሰው ልጆች ታሪክ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል። በሽታው ይታይበት የነበረውን መንገድ ቀይሯል።
ረዥም ቀሚስ ወይም ረዥም ጺም ጀርሞች ሊራቡበት እንደሚችል ሐኪሞች አስጠነቀቁ። በርካቶችም የሐኪሞችን ምክር መስማት ጀመሩ።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ሕክምና የሚወሰደው እረፍት ማግኘት፣ ፀሐይ መሞቅ እና ንጹሕ አየር ላይ መናፈስ ነበር።
በወቅቱ በተራራማ አካባቢዎች ሕክምናው ይሰጣል። ሰዎች ንጽሕናቸውን መጠበቅ እና ፀሐይ ማግኘትን እንደ አማራጭ ወስደውም ነበር።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን በረንዳዎች ክፍት ሆነው የተሠሩት ወይም መስኮት ረዘም ተደርጎ የተገነባውም እንደ ተፈጥሯዊ መድኃኒት ማግኛ ስለሚቆጠሩ ነው።
ቆሻሻ ወደ ቤት ውስጥ እንዳይገባ በመከላከል ጀርሞች እንዳይራቡ ለማድረግ ይሞከር ነበር።
የአኗኗር ለውጥ ቢደረግም ለበሽታው ሳይንሳዊ ሕክምና አልተገኘም።
በ1921 በፓሪስ በሚገኝ ሆስፒታል የሙከራ ክትባት ለጨቅላ ሕጻን ተሰጠ። የሕጻኑ እናት በሳምባ ነቀርሳ ሕይወቷን አጥታለች።
ፈረንሳውያኑ ሳይንቲስቶች አልበርት ካልሜት እና ካሜል ጉሪን ባክቴርያውን በመጠቀም ከአሥርት ዓመታት በላይ ክትባት ለማግኘት ተመራምረዋል።
በምርምራቸው 'ባሲለስ ካልሜት ጉይሪን' ወይም ቢሲጂ የተባለው ክትባት ተገኘ። ክትባቱ እስከሚገኝ ድረስ የባክቴርያው ቅንጣት ላይ 230 ጊዜ ለውጦች ተደርገዋል።
በዚህ መንገድ በጨቅላዎች ሰውነት ላይ በሽታውን የመከላከል አቅምን ማዳበር ቢቻልም ባክቴርያውን መግደል አልተቻለም ነበር።
ቢሲጂ ጨቅላዎችን ከሳምባ ነቀርሳ ለመታደግ ነው የተሠራው። ሕጻናት በዚህ በሽታ ምክንያት በቀላሉ ለኅልፈት ይዳረጋሉ።
ባክቴርያው በሰውነታቸው ከተስፋፋ በኋላ ቲውበርክሎሲስ ሜንጃይተስ እና ሚሊተሪ ቲውበርክሎሲስ የተባሉ የኢንፌክሽን ዓይነቶች ያስከትላል። እነዚህም በከፍተኛ መጠን ለሞት ያጋልጣሉ።
ክትባቱ በተሠራበት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት በፈረንሳይ ለተወሰኑ ሕጻናት ብቻ ነበር የተሰጠው።
የሳይንሱ ማኅበረሰብ ክትባት ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው የሚለውን ለመወሰን ለዓመታት ሙከራ መደረግ እንዳለበት ስለሚያምን ክትባቱ ስለመሠራቱ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም።
በወቅቱ የባክቴርያውን አካል በክትባት አማካኝነት ወደ ሰውነት ማስገባት የሚለውን ሐሳብ ሳይንቲስቶች ብዙም አልተቀበሉትም።
ከ1929 እስከ 1930 በጀርመን፣ ሉቤክ ከተማ ለ251 ሕጻናት ክትባቱ ተሰጠ። በቤተ ሙከራ ውስጥ በተሠራ ስህተት ምክንያት ክትባቱ ከአደገኛው የሳምባ ነቀርሳ ዝርያ ጋር ተደባልቆ ነበር።
በዚህም ምክንያት 72 ሕጻናት ሲሞቱ 173 የሚሆኑት ክፉኛ ታመሙ። ይህ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ክስተት ክትባቱ በአውሮፓ ያለውን ስም አጉድፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ቢሲጂ ክትባት በስፋት ጥቅም ላይ አልዋለም።
በወቅቱ በአውሮፓ የሳምባ ነቀርሳ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነበር። ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ክትባት ለመስጠትም ወሰኑ።
በፈረንሳይ ብሔራዊ የጤና ምርምር ማዕከል የሚሠሩት የታሪክ ባለሙያ ካላስ ኪቼል "ቢሲጂ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ለቲቢ በስተመጨረሻ ክትባት አግኝተናል" ይላሉ።
ነገር ግን ክትባቱ "በምን ያህል መጠን ከበሽታው እንደሚከላከል" በግልጽ አለመታወቁን ይጠቅሳሉ።
በለንደን የፍራንሲስ ከርክ ተቋም ኃላፊ የሆኑት ማክሲሚላኖ ጉቴሬዝ "ቲቢ በዋነኛነት የሚጎዳው ሳምባን ነው። ባክቴርያው በመተንፈሻ አካላት በኩል ወደ ሰውነት ገብቶ ሳምባ ጋር ይደርሳል" ይላሉ።
ባክቴርያው ሳምባ ውስጥ ከገባ በኋላ በሕዋሳት ውስጥ በመስረግ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማል።
"ባክቴርያው ከሕዋሳት ጋር ሲደባለቅ ሰውነት ወይ ባክቴርያውን መግደል ይችላል አልያም ደግሞ ባክቴርያው ይራባል። ባክቴርያው ሲራባ የሳምባ ነቀርሳ ይከሰታል" በማለት ባለሙያው ያስረዳሉ።
ክትባቱ ሰውነት ባክቴርያውን እንዲገድል የሚያደርግ ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች በሳምባ ነቀርሳ እንዳይያዙ የሚያደርገው ክትባት አዋቂዎችን ከበሽታው የመከላከል አቅሙ ደካማ መሆኔ የታወቀው ከዓመታት በኋላ ነበር።
ማክሲሚላኖ "በሕጻንነታቸው የተከተቡ ሰዎች ከበሽታው ራሳቸውን መከላከል ቢችሉም የመከላከል አቅሙ በጊዜ ሒደት ይቀንሳል" ሲሉ ያብራራሉ።
በዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የሚያሳየው ክትባቱ በረዥም ጊዜ ሒደት ውስጥ ከሳምባ ነቀርሳ የመከላከል አቅሙ ደካማ መሆኑን እንደሚያሳይ ይናገራሉ።
ከክትባቱ በተጨማሪ 'ስቴርፕቶሚኪን' የተባለው ውጤታማ ፀረ ባክቴርያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው በአውሮፓውያኑ 1943 ነበር።
የሳምባ ነቀርሳን የተለያዩ የመድኃኒት ዓይነቶች በማዋሀድ ለመከላከል የሚደረገው ጥረትም ቀጠለ።
አሁን ላይ የሳምባ ነቀርሳ ሕክምና የሚሰጠው የተለያዩ ፀረ ባክቴርያዎችን በማዋሀድ ሲሆን፤ እስከ ስድስት ወራት የሚወስድ ሒደት ነው።
በአውሮፓ ትልቁ የሆነው ክሪክ ቤተ ሙከራ ውስጥ ምርምሩ ቀጥሏል።
ማክሲሚላኖ እንደሚሉት፤ በሽታውን ለማከም ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ፀረ ባክቴርያዎች እና ስድስት ወራት ለምን እንደሚያስፈልግ ምርምር ይደረጋል።
"ሰዎችን ማዳን የሚቻልበት ጊዜ እንዲያጥር እና በተሻለ መጠን ውጤታማ የሚሆኑ ፀረ ባክቴርያዎችን ለማግኘት ሙከራ እየተደረገ ነው" ይላሉ።
ኢንፌክሽኑ በሚፈጠርበት የመጀመሪያው ወቅት ምን እንደሚከሰት ማወቅ ሌላው የምርምሩ ዓላማ ነው።
"የመጀመሪያውን ደረጃ ማወቅ አንድ ሰው በሽታውን ያስወግዳል ወይስ በሽታው ይጸናበታል የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል" ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።
የሳምባ ነቀርሳ "ውስብስብ" እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው ስለ በሽታው እስካሁን ድረስ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸውን ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሱሪይ መምህር የሆኑት ዳኒ ቤትስ እንደሚናገሩት፤ የሳምባ ነቀርሳን የሚያስከትለው 'ማይክሮባክቴርየም ቲውበርክሎሲስ' እጅግ ከባድ ሲሆን፤ እድገቱም በጣም ዘገምተኛ ነው።
"እድገቱ በጣም ዘገምተኛ ስለሆነ በዘርፉ የሚደረገውም ጥናት የተጓተተ ሆኗል። እጅግ አደገኛ ተህዋሲ ነው" ይላሉ።
የባክቴርያው ባህሪ ሙሉ በሙሉ ሰውነት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ እና እንዲደበቅ የሚያስችለው ነው። ሰውነትን የሚከላከሉ ሕዋሳት ውስጥ መግባቱ ደግሞ የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል።
"ሰውነት ውስጥ የገባን ባክቴርያ እና ቫይረስ ለይቶ የማጥፋት ሚና ያለው ማክሮፋገስ የተባለው ሰውነትን ከበሽታ የሚከላከል ሕዋስ ነው። የሳምባ ነቀርሳ ግን በሕዋሳቱ ውስጥ የመኖር እና የመራባት ችሎታ አለው" ሲሉ መምህሩ ይገልጻሉ።
የሳምባ ነቀርሳ በሌሎች የሰውነት ሕዋሳት ውስጥም መኖር ይችላል።
በመላው ዓለም ከአራት ሰዎች አንዳቸው የሳምባ ነቀርሳ የሚያስከትለው ባክቴርያ በሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል። በበሽታው ሳይያዙ ነገር ግን ባክቴርያው በሰውነታቸው ውስጥ ይኖራል ማለት ነው።
ባክቴርያው ጉዳት ሳያደርስ በሰውነት ውስጥ የሚቀመጥበትን ምክንያት የሚያጠናው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት ዳኒ "የባክቴርያውን መሠረታዊ ውቅር መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ።
ባክቴርያው እንዴት እንደሚሠራ ማወቅን ጨምሮ ሌሎችም መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች አሉ። የተሻለ የሕክምና መንገድ ለማግኘትም እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል።
አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን ክትባት ለማሻሻል ወይም አዲስ ክትባት ሠርቶ ባክቴርያውን ለማጥፋት በተለያዩ አገራት ጥናት እና ምርምር እየተደረገ እንደሆነ ማክሲሚላኖ ይናገራሉ።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ቢደረጉም እንኳን የሳምባ ነቀርሳ ዋነኛ ገዳይ ከሆኑ ሽታዎች አንዱ ነው።
ሰዎችን ለሞት ከሚዳርጉ 10 ቀዳሚ ሕመሞች አንዱ የሳምባ ነቀርሳ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በሽታው በሁሉም አገራት በየትኛውም ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሊይች ይችላል።
የደቡብ ምሥራቅ እስያ እና የአፍሪካ አገራት በሽታው የሚከሰትበትን መጠን ይመዘግባሉ። በላቲን አሜሪካ አገራት ግን በስፋት ምዝገባ አይከናወንም።
በአውሮፓውያኑ ከ2015 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት በመላው ዓለም ያለው የበሽታው ስርጭት 12.3% ሲቀንስ፤ በላቲን አሜሪካ ግን 13% እንደጨመረ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ለዚህም በከተማ ውስጥ የሚስተዋለው የተጨናነቀ ኑሮ፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ጫና ዋነኛ ምክንያት ተብለው ተጠቅሰዋል።
የሳምባ ነቀርሳን ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶች ቢቀጥሉም አሁንም ድረስ ፈተናዎች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፀረ ባክቴርያውን ለማግኘት አለመቻል፣ የጤና ተቋማት መዳከም እና ድህነት ተጠቃሽ መሰናክሎች ናቸው።
በዘርፉ አዲስ መድኃኒት ወይም ሕክምና ለማግኘት ለሚደረጉ ጥናት እና ምርምሮች በቂ ገንዘብ እንደማይገኝም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ንጹሕ መኖሪያ ቤት እና ንጹሕ ውሃን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ማድረግ አለመቻሉ ሌላው መሰናክል ነው።




































