የመንግሥታቱ ድርጅት ሁሉም ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሕፃናትን ደህንነት የሚጠብቁ እንዲሆኑ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁሉም ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሕፃናትን ደህንነት ለመጠበቅ መስራት እንዳለባቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ አሳሰቡ።
ኃላፊው ይህንን ያሉት ሜታ በአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በልጆች የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት የቀረቡበትን ክሶች በስምምነት ለመፍታት እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ከተስማማ በኋላ ነው።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች ጋር የገባው ስምምነት የሕፃናትን ደህንነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነው።
ነገር ግን ሜታ እነዚህ ገደቦች ስናፕቻት፣ ቲክ ቶክ እና ዩቲዩብ ተመሳሳይ የሕጻናት ጥበቃ እርምጃዎችን ከወሰዱ የበለጠ ሊጠናከሩ እንደሚችሉ ተናግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ እንዳሉት መንግሥታት "ፍርድ ቤቶችና ኩባንያዎች እርምጃ እስኪወስዱ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።
አክለውም "ሕጻናት በኦንላየን ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ፍርድ ቤቶችን መጠበቅ የለባቸውም" ሲሉ አብራርተዋል።
"ልጆች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ክስ እስኪመሰረት መጠበቅ የለባቸውም" ብለዋል።
ተርክ በተጨማሪም ሜታ ያቀረባቸውን የጊዜ ገደቦች እና የወላጆች ቁጥጥር እርሳቸው ሲጠይቋቸው ከነበሩ ለውጦች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን አስታውሰው፤ "ግን እስካሁን እዚያ አልደረስንም" ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
በግንቦት ወር የተርክ ቢሮ ማኅበራዊ ሚዲያን ለመቆጣጠር የሚያስችል 10 ነጥብ ያለው ማዕቀፍ ይፋ አድርጓል።
ይህም የመረጃን ግላዊነት መጠበቅ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲኖር ማድረግ፣ የተጠቃሚን ዕድሜ ማረጋገጥ እና ተጠቃሚዎችን ሱስ የሚያስይዙ ንድፎችን ማስቀረት ያካትታል።
ይሁን እንጂ ማዕቀፉ ሕጻናት የማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ በቀጥታ መከልከል የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የካሊፎርኒያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሮብ ቦንታ፣ ቲክ ቶክ ከሜታ ጋር ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንዲወስድ "ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ" ተናግረዋል።
ሜታ ረቡዕ ዕለት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ወጣቶች ሱስ እንዲይዙ አድርጎ ነድፏል በሚል ከቀረቡበት ክሶች ጋር በተያያዘ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።
በስምምነቱ መሠረት ሜታ ታዳጊዎች ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን የሚጠቀሙበትን ጊዜ እና መንገድ ይገድባል።
ስምምነቱ ኩባንያው የልጆችን ደህንነት አስመልክቶ ሕዝብን አሳስቷል እና ምርቶቹም በሕጻናት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የቀጠለውን የፌዴራል ፍርድ ሂደት ያቋርጠዋል ተብሏል።
ሜታ ከዚህ ውሳኔ በኋላ የሚደረጉት የተለያዩ ለውጦች ውጤታማ የሚሆኑት "ሁሉም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከተቀላቀሉን ነው" ብሏል።
ቦንታ ለሲኤንቢሲ ከቲክ ቶክ እና ከዩቲዩብ ጋር ለመነጋገር "እንደሚፈልጉ" እንዲሁም ቲክ ቶክ "ከእኛ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት አለው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱም ኩባንያዎች አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ቦንታ አክለውም በርካታ ወጣቶች ከሚጠቀሙት ከስናፕ ጋር ግንኙነት መጀመራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ነገር ግን ሜታ ለውጦችን ለማድረግ በተስማማባቸው መንገዶች መሠረት ለመስራት ካልተስማሙ "ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈቃደኛ" እንደሆኑ አስጠንቅቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ሜታ እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክፍያ ለ47 የአሜሪካ ግዛቶች፣ ለዋሺንግተን ዲሲ፣ ለፖርቶ ሪኮ፣ ለአሜሪካን ሳሞአ እና ለኖርዘርን ማሪያና ደሴቶች በአጠቃላይ እስከ 16.7 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክፍያ ለመፈጸም ተስማምቷል።
ሜታ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ታዳጊዎች ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ገደብ ይጥላል። የወላጅ ፈቃድ ከሌለ ደግሞ ከእኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት ድረስ አጠቃቀም ይታገዳል።
በተጨማሪም ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት ባለው የትምህርት ጊዜ አብዛኛዎቹ ገፋፊ የሆኑ መልዕክቶች ለታዳጊዎች እንዳይላኩ ይደረጋል። ህጻናት የእድሜ ገደብ ያላቸው ይዘቶችን እንዳያገኙም ተጨማሪ የደህንነት እርምጃዎች ይጠናከራሉ።
ሜታ በክሱ ላይ ከስምምነት ላይ ቢደርስም ጥፋት መፈጸሙን ግን አልተቀበለም።















