በሳምንታት ኢራንን ያንበረክካል ተብሎ ስድስተኛ ወሩን በደፈነው ጦርነት ማን ከፍተኛውን ዋጋ ከፈለ?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ ከስድስት ወራት በኋላ፣ አጭር ይሆናል ተብሎ የተጠበቀው ጦርነት፣ መጨረሻው ግልጽ ያልሆነ እና የተራዘመ ግጭት ሆኗል።

የካቲት 21/2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ ጦርነቱን የጀመሩት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲሁም ቁልፍ የአመራር እና ወታደራዊ ማዕከላትን ዒላማ በማድረግ ነበር።

በመጀመሪያው ዕለት በኢራን ላይ በተፈጸሙት የተቀናጁ የአውሮፕላን እና የሚሳዔል ጥቃቶች የእስላማዊቷን አብዮታዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

ይህንን ተከትሎም ለወራት በሕዝባዊ ተቃውሞ ሲናጥ የነበረው የኢራን መንግሥት እንዳበቃለት በስፋት የተነገረ ቢሆንም፣ እጇን ያልሰጠችው ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው ወዲያው ነበረ።

ለዘመናት የገነባቻቸው ዘመናዊ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎቿን በመጠቀም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ለቀናት አዝንባለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን ጋር የሚካሄደው ጦርነት ከሳምንታት የማያልፍ አጭር ጦርነት እንደሆነ እና ኢራንም በቶሎ እጅ እንድትሰጥ በመጠየቅ ሠራዊታቸው ለድል መቃረቡን አሳውቀው ነበር።

ነገር ግን በጦርነት እና በድርድር ውስጥ ሳትበገር የቆየችው ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት እንዲሁም በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከባድ ተጽዕኖን ማሳደር ችላለች።

ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን ተክተው ጠቅላይ መሪ ሆነው ተመርጠዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንታት

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ የያዙት ዋነኛ ግብ ኢራን ኒውክሌር መሳሪያ ለማምረት የሚያስችል አቅም እንዳይኖራት ማድረግ ነው።

ኢራን ከጅምሩም ይህንን ዓይነቱን መሣሪያ የመታጠቅ ዕቅድ እንደሌላት ስትገልጽ ቆይታለች።

የኢራንን የኒውክሌር መሳሪያ የማምረት አቅም ለማስቀረት በሚል የተጀመረው ይህ ጦርነት በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ብቻ በቴህራን ወታደራዊ አቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

አሜሪካ እና እስራኤል በመቀናጀት በፈጸሙት ጥቃት የቴህራንን የሚሳዔል ተቋማት፣ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች፣ የመከላከያ ተቋማት እና የመከላከያ ኢንዲስትሪዎችን መትተዋል።

የኢራን መደበኛ ወታደራዊ ተቋማት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል፤ የአየር እና የባሕር ኃይሏ እንዳያንሰራራ ተደርጎ ተመትቷል። ነገር ግን ቴህራን ሚሳዔሎቿን እና ድሮኖቿን ደብቃ ማቆየት ችላለች።

ኢራን እነዚሀን መሳሪያዎቿን በመጠቀምም በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች እንዲሁም አጋሮች ላይ የአጸፋ ምላሽ ሰጥታለች።

እነዚህ ጥቃቶችም የኢራን ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው የተራዘመ ጦርነት ከመቀስቀስ እንደማያስቆማት ያሳየ ነው።

በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል ያለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ ኪሳራ የማድረስ አቅም ያለው ወገን የተሳተፉበት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ የመጣ ግጭት ተፈጥሯል።

አሜሪካ እና እስራኤል ወደ ጦርነቱ ሲገቡ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እርምጃ ኢራን በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ በቀጣናው የምትፈጥረውን ስጋት እንደሚያዳክም ተስፋ በማድረግ ነበር።

ይሁን እንጂ ከስድስት ወራት በኋላም ኢራን ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን የማስወንጨፍ አቅሟን ጠብቃ የቆየች ሲሆን፣ ሰፋ ያለው ግጭትም ከኢራን ድንበር ባሻገር ከፍተኛ መዘዞችን አስከትሏል።

የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሆርሙዝ ወሽመጥ የጦርነቱ ማዕከል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ግጭት ውስጥ የታየው ትልቁ ለውጥ የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ የግጭቱ ማዕከል መሆን ነው።

ይህ ጠባብ የመርከቦች መተላለፊያ ወሽመጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የዓለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ይተላለፍበታል።

የዓለም 20 በመቶ የሚሆነው የኤነርጂ አቅርቦት የሚጓጓዝበት ይህ መስመር አሜሪካ እና የኢራን ጦርነት ማዕከል የሆነው ግጭቱ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።

ቴህራን አሜሪካ እና እስራኤል ለከፈቱባት ጦርነት አጸፋ ወሽመጡን ሙሉ በሙሉ በመዝጋቷ በዓለም የነዳጅ እና የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል።

በነሐሴ ወር ብቻ በወሽመጡ በኩል ያለፉ መርከቦች ቁጥር ከተለመደው በእጅጉ ያነሰ መሆኑን በአካባቢው የሚደረገውን የመርከቦች እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም. ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን አስተዳደር በተመለከተ መነጋገር ጀምረዋል።

ይህም የመርከብ እንቅስቃሴ ዳግም ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋን ፈንጥቋል።

ድርድሩ ኢራን እና ኦማን በጋራ የሚያስተዳድሩት በባሕረ ሰላጤው ውስጥ አዲስ የመተላለፊያ መስመር መክፈት ላይ ያተኮረ ነበር።

ነገር ግን ስምምነቱ ሊፈረም ይችላል የሚል ተስፋ እየጨመረ በመጣበት ጊዜ ኢራን ወሳኝ የሆነው የባሕር መስመር እንደገና ከመከፈቱ በፊት አሜሪካ ማሟላት አለባት ያለቻቸውን ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝራለች።

ኳታር በበኩሏ ከፓኪስታን ጋር በመሆን ቴህራን እና ዋሺንግተን መግባባት ላይ እንዲደርሱ ማሸማገል ጀምራለች።

ነገር ግን የነዳጅ መተላለፊያው መዘጋት ያስከተለው ውስብስብ ጫና ከመካከለኛው ምሥራቅ ያለፈ ሆኗል።

ሮይተርስ የዓለም ግማሽ የነዳጅ ምርት የሚገኘው አሁን በግጭቱ ከተጎዱ አገራት መሆኑን ሲዘግብ፣ በጦነርቱም 10 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ማጣሪያ አቅም ከአገልግሎት ውጪ ተደርጓል ብሏል።

በዋጋ ግሽበት እና በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ የተጎዱ መንግሥታት የወሽመጡ መዘጋት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ፈተና እና የደኅንነት ቀውስ ደቅኖባቸዋል።

በቴህራን ጎዳና ላይ የሚንቀሳቀሱ ኢራናውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ያለው የዋጋ ግሽበት ወደ 70 በመቶ አካባቢ እንደሚደርስ ሲተነበይ፣ ኢኮኖሚውም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሽቆለቁል ይጠበቃል

ሰላም ማምጣት ያልቻለው ዲፕሎማሲ

ጦርነቱን ለማስቆም በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተደርገዋል።

ፓኪስታን በተናጠል ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ለማስማማት ካደረገችው ጥረት ባሻገር፣ ከኳታር ጋር በመሆን በሰኔ ወር ጦርነቱን በተኩስ አቁም ጋብ ለማድረግ ያስችላል የተባለ የመግባቢያ ስምምነት እንዲፈራረሙ ማድረግ ተችሎ ነበር።

ነገር ግን በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም፣ በማዕቀቦች መነሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስለሚኖር ቋሚ ቁጥጥር መግባባት ባለመቻሉ ስምምነቱ ፈርሷል።

በሁለቱ አገራት መካከል ዳግም ያገረሸው ግጭት ኳታር፣ ፓኪስታን እና ኦማን የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል።

ጥረታቸው ግን ዋሺንግተንም ሆነ ቴህራን ከግጭቱ ለመውጣት የሚያስችል የመፍትሔ ሃሳብ ላይ መድረስ አለመቻላቸውን እንደሚያሳይ ቀጣናውን የሚከታተሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

ስምምነት አለመድረሱ በቀጣናው ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል።

የታገደውን የኢራን ሀብት አጠቃላይ ዋጋ ከ27 እስከ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
የምስሉ መግለጫ, የታገደውን የኢራን ሀብት አጠቃላይ ዋጋ ከ27 እስከ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በምጣኔ ሀብት ጫና በኢራን ላይ

ለስድስት ወር የተካሄደው ጦርነት ቴህራን ላይ ያደረሱት ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ከባድ ነው።

ወታደራዊ ጥቃቶቹ ወሳኝ የሆኑ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶችን ያወደሙ ሲሆን፣ ማዕቀቦች እና በነዳጅ ኤክስፖርት ላይ የተጣሉ ገደቦች ደግሞ ቀድሞውኑም ችግር ላይ የነበረው ምጣኔ ሀብት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥረዋል።

አሜሪካ ከ27 እስከ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል የኢራንን ሃብት ለዓመታት እንዳይንቀሳቀስ አግዳ ቆይታለች።

ሀብቱ የሚገኘው በአንድ፣ ማንቀሳቀስ በሚቻል አካውንት ውስጥ አይደለም። የኢራን ሀብት ሲባል የነዳጅ ሽያጭ ገቢዎችን እንዲሁም የነዳጅ፣ የጋዝ እና የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ገንዘብን ያካትታል።

የኢራን መገበያያ ገንዘብ አቅሙ የተዳከመ ሲሆን በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፣ እንዲሁም የነዳጅ እጥረት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

ኢራናውያን ከዕለት ወደ ዕለት የኢኮኖሚው ጫና እየተሰማቸው መሆኑን ሮይተርስ እና የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግበዋል።

ከኢራን የሚወጡ ዘገባዎች በነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚታየውን ረጅም ሰልፍ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ያሳያሉ።

በኢራን ያለው የዋጋ ግሽበት ወደ 70 በመቶ አካባቢ እንደሚደርስ ሲተነበይ፣ ኢኮኖሚውም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሽቆለቁል ይጠበቃል።

ሆኖም፣ ይህ የኢኮኖሚ ጫና ቴህራን የዋሽንግተንን ጥያቄዎች እንድትቀበል አላስገደዳትም።

ከዚያ ይልቅ የኢራን አመራር ማዕቀቦቹን እንደ ኢኮኖሚ ጦርነት በመፈረጅ በአሜሪካ ጫና ላይ ተቃውሞውን ቀጥሏል።

ካርታ

የአሜሪካ የአቋም ለውጥ

አሜሪካ በስድስት ወር ያህል በዘለቀው ግጭት ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች።

ኢራን ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 20 የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ማውደሟን እና የደረሰው ጉዳት በይፋ ከታወቀው ከፍተኛ መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

ኢራን ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ስምንት አገራት ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላትን ዒላማ አድርጋ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ዘመናዊ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ በአየር ላይ ነዳጅ የሚሞሉ አውሮፕላኖችን እና ራዳሮችን በመምታት በሚሊዮኖች ዶላር የሚያስወጣ ውድመት አድርሳለች።

ጦርነቱ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ወታደራዊ መሳሪያዎች እና ተተኳሾች ጥቅም ላይ የዋሉበት ከመሆኑም በላይ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።

ግጭቱ መራዘሙን ተከትሎ፣ የትራምፕ አስተዳደር ትኩረቱን ከወታደራዊ ጥቃቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጫና የማሳደር አዝማሚያ አዘንብሏል። ይህም ከኢራን ባሻገር ሌሎችንም አገራት የሚነካ መሆኑ ተነግሯል።

ዋሽንግተን፣ ኢራንን በኢኮኖሚ መደገፋቸውን በሚቀጥሉ አገራት እና ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠሩ እርምጃዎችን ጨምሮ፣ "በታሪክ እጅግ ጠንካራ ማዕቀቦች" ስትል የገለጸቻቸውን እርምጃዎችን ወስዳለች።

ይህ ለውጥ፣ ወታደራዊ ኃይል ብቻውን ዋሽንግተን የፈለገችውን የፖለቲካ ውጤት እንዳላመጣ ያሳያል።

አሸናፊው ያልለየ ጦርነት

ስድስት ወር ሙሉ በጦርነት ውስጥ የቆዩት አሜሪካ እና ኢራን አሸናፊነታቸውን ማወጅ አልቻሉም።

የኢራን ወታደራዊ አቅም በእጅጉ የተዳከመ ቢሆንም፣ የሚሳዔል እና የድሮን አቅሟ ግን አሁንም አለ። የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ጉዳት ቢደርስበትም ምን ያህሉ እንደተረፈ እና የደረሰውን ውድመት ለመገምገም የሚችል ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን አልቻለም።

ለአሜሪካ፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደገና መከፈት እና ኢራን የኒውክሌር አቅሟን እንዳትገነባ መከላከል ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ሆነዋል። ይሁን እንጂ፣ ወደ ሙሉ ወታደራዊ ግጭት ሳያመለሱ እነዚህን ግቦች ማሳካት አሁንም አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

ስለሆነም ጦርነቱ አደገኛ ወደሆነ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፤ ይህም ሙሉ በሙሉ ሰላም ያልሰፈነበት ግን በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት ወቅት እንደነበረው ውጥረት የሚስተዋልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

አሁን ያለው ዋና ጥያቄ፣ በጦርነቱ ማን አሸነፈ የሚለው ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ወታደራዊ ዘመቻዎች ማሳካት ያልቻሉትን ዲፕሎማሲ ለውጥ ያመጣል ወይ የሚለው ነው።

ከስድስት ወራት በኋላ፣ ጦርነቱ ኢራንን ቀይሯል፣ የአሜሪካን ወታደራዊ አቅም ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። የዓለምን የኤነርጂ ገበያ አዛብቷል፤ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የኃይል አሰላለፍ ለውጧል።

አጠቃላይ የመፍትሄ እርምጃ በቅርብ ርቀት በማይታይበት በዚህ ወቅት፣ ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ይቆያል ተብሎ የተገመተው ይህ ጦርነት፣ በቀጣዮቹ ወራት ወይም ዓመታትም ቀጣናውን እና የዓለምን ኢኮኖሚ በአዲስ መልክ መቅረጹ አይቀርም።