ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ የተደጋጋሚ ግጭቶች መነሻ የሆነው የሞያሌ ችግር

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በሞያሌ ከተማ በሶማሌ እና በኦሮሞ ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ለሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የተከሰተው ይህ ግጭት በሶማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀል ውዝግብ የተነሳ መሆኑን የሁለቱም ክልል ከንቲባዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከባድ መሳሪያዎችን ጨምሮ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን አብራርተዋል።

እንደ ኬንያ ቀይ መስቀል መረጃ ከሆነ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ኬንያ የሸሹ ግለሰቦች ቁጥር ከ40,000 በላይ ይደርሳል።

የሞያሌ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢቆይም፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በከተማው ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስ በቂ የፀጥታ ኃይል አላሰማሩም።

ወደ ኬንያ ከተሰደዱት መካከል 15,000 ያህሉ በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ደግሞ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ቤት ማረፋቸው ተሰምቷል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች እንደሚገልጹት፣ የተፈናቀሉት ሰዎች ምግብ፣ መጠለያ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች በአስቸኳይ ያስፈልጓቸዋል።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው እንዴት ነው?

ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በሚዋሰኑባት ሞያሌ ከተማ ከቀናት በፊት ግጭት የተቀሰቀሰው የኦሮሚያ ክልል ይገባኛል በሚለው አካባቢ የሶማሌ ክልል ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ነው።

የሞያሌ ነዋሪ የሆነው ሞሉ፣ ጃታኒ አጋ የተባለች ታዳጊ የባንዲራው መሰቀል በመቃወሟ እንደተገደለች ተናግሯል። ይህም በአካባቢው ነዋሪዎችና በኦሮሞ ወጣቶች መካከል ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።

ሞሉ እንዳለው ከሆነ ነዋሪዎች በዚያን ዕለት ጠዋት ባንዲራ መሰቀሉን እስኪሰሙ ድረስ ስለተፈጠረው አለመግባባት አያውቁም ነበር።

ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ የሰጡ ሌሎች ሦስት ነዋሪዎችም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ገልማ ኮሮፊቻ፣ ግጭቱን አሳዛኝ ሲሉ ገልጸው፣ ከሶማሌ ክልል የመጡ የፀጥታ ኃይሎች ውጥረቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

ከንቲባው ግጭቱ የተከሰተው ለረጅም ጊዜ አብረው ሲኖሩ እና የቅርብ ማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ግንኙነቶች ባሏቸው የኦሮሞ እና የሶማሌ ማኅበረሰቦች መካከል መሆኑን ይናገራሉ።

በሶማሌ ክልል የሚገኘው የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ኩላ አሊ አብዲራህማን ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሶማሌ ክልል ባንዲራ ከመሰቀሉ ጋር በተያያዘ መሆኑን ይስማማሉ።

"ሰላም እያለን እና ምንም ዓይነት ግጭት ሳይኖር፣ ከእንቅልፋችን ነቅተን ራሳችንን በጦርነት መሃል አገኘን። ግጭቱ የተጀመረው በቅርቡ በከተማው ውስጥ በከፈትነው የአስተዳደር ቢሮ ምክንያት ነው" ብለዋል።

አክለውም "በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ አዲስ የከተሞች እና ወረዳዎች አስተዳደራዊ መዋቅር ከአንድ ዓመት በፊት ተዋቅሯል። ከዚያ ወዲህ ሞያሌ ሁለት አስተዳደሮች እንዲኖሯት መደረጉን በመቃወም ቅስቀሳ የሚያደርጉ ነበሩ" ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ ቀደም ሲልም በአካባቢው ባሉ መንግሥታዊ ቢሮዎች ላይ የሶማሌ ክልል ባንዲራዎች ሲሰቀሉ የነበረ ቢሆንም ተቃውሞውም ባንዲራውን ሳይሆን አዲሱን የአስተዳደር ቢሮ መከፈቱን የሚመለከት ነበር።

"ባንዲራችን እዚያ የተሰቀለው ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም" ካሉ በኋላም "ከዚህ በፊትም ብዙ ቢሮዎች ተከፍተዋል፣ በእያንዳንዱም ቢሮ ባንዲራ ይሰቀላል። የተቃወሙትም ይህንኑ [አዲሱን ቢሮ] ነው" ሲሉ የግጭቱ መንስዔ ያሉትን አስረድተዋል።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የሞያሌ ነዋሪዎች፣ ከባድ ውጊያዎች ለቀናት ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው በግጭቱ ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሣሪያዎች ከአካባቢው አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በላይ ያሉ ኃይሎች በግጭቱ ውስጥ ተሳትፈዋል የሚል ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ነዋሪዎች፣ በግጭቱ ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆን የተሳተፉ ግለሰቦችም የላቀ ወታደራዊ ሥልጠና ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

በተጨማሪ ከሌላ አካባቢ የመጡ ተዋጊዎች በዚህ ግጭት መሳተፋቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሏቸው ገልጿል።

እንደ ሞሉ ገለጻ ከርቀት የሚተኮሱ ከባድ መሣሪያዎች የሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።

ቢቢሲ ከሞሉ ጋር ቃለ መጠይቅ ባደረገበት ወቅትም ከበስተጀርባ የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበር።

ነዋሪዎች በተጨማሪም መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ግጭቱ እንዲቆም ባለማድረጉ ቅሬታቸውን ገልጸው፣ የአካባቢውን ለማረጋጋት የፀጥታ ኃይሎች እስከ ማክሰኞ ከሰዓት ድረስ አለመሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

ሞሉ እንዳለው፣ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል፤ ብዙ ሰዎች አካባቢውን እየለቀቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ያለ ምግብ ቀርተዋል።

"ሰዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ወደ ኬንያ ጋምቦ እየሸሹ ነው። ብዙ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ነው። የቆሰሉት ሕክምና አላገኙም፤ የሟቾችም ቁጥር ከፍተኛ ነው" ብሏል።

የሶማሌ ክልል ምን አለ?

በሶማሌ በኩል የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ኩላ አሊ አብዲራህማን ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ለወረዳዎችና ቀበሌዎች አዲስ የአስተዳደር መዋቅር ማስተዋወቁን አስታውሰዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በዚህ ሂደት አዲስ የአስተዳደር ቢሮ ከተከፈተ በኋላ ተቃውሞዎች በርትተዋል።

እንደ ኩላ አሊ ገለጻ፣ ሞያሌ ለረጅም ጊዜ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በጋራ ስትተዳደር የነበረች ሲሆን፣ በከተማዋ መሃል የሚያልፈው ዋና መንገድ ግራ እና ቀኝን በመያዝ ክልሎቹ የራሳቸውን አስተዳደር መሥርተዋል።

ከተማዋን ለሁለት ሰንጥቆ የሚያልፈው ዋናው መንገድ ሁለቱን ክልላዊ መንግሥታት የሚለይ ድንበር ተደርጎ ይወሰዳል።

የሶማሌ አስተዳደር የከተማዋን ምሥራቃዊ ክፍል እንደሚያስተዳድር የሚናገሩት ከንቲባው፣ የኦሮሚያ አስተዳደር ደግሞ ምዕራባዊውን ክፍል እንደሚያስተዳድር ከንቲባው ተናግረዋል።

ከንቲባው እንዳሉት፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሞያሌ በሁለት ክልላዊ መንግሥታት እንድትተዳደር የሚለውን ሃሳብ የማይቀበሉ ሲሆን፣ መላው ከተማ በኦሮሚያ ሥር መሆን አለበት በሚል አቋም ያንጸባርቃሉ ሲሉ ይወቅሷቸዋል።

ኩላ አሊ እንደተናገሩት ሁለቱ ክልሎች ከተማዋን በዚህ መልክ ማስተዳደር ከጀመሩ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የኖረ መሆኑን ገልጸው፣ አዲሱ አስተዳደር ከተደራጀ በኋላም ውጥረቱ እንደተባባሰ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተፈጸሙ ጥቃቶች የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎቶች እንዲቋረጥ መደረጉንም በመጥቀስ ከስሰዋል።

አዲሱ የአስተዳደር አወቃቀር

የሶማሌ ክልል መንግሥት አዲስ 14 ወረዳዎችን፣ ሁለት የዞን አስተዳደሮችን እና 25 ማዘጋጃ ቤቶችን አስተዳደራዊ መዋቅር የጸደቀው ሐምሌ 19/ 2017 ዓ.ም. ነበር።

በ2017 ዓ.ም. የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት 14 አዳዲስ ወረዳዎችን መፍጠሩን በማስታወቅ፣ በአስተዳደሩ ሥር ያሉትን ወረዳዎች ቁጥር ከ95 ወደ 109 አሳድጓል።

አስተዳደራዊ መዋቅሩ የጸደቀው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነበር።

በወቅቱ የክልሉ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት፣ ለውጡ የተደረገው የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማሻሻል እና ወደ ወረዳ እንዲያድጉ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ ማኅበረሰቦችን ፍላጎት ለማሟላት ነበር።

ሆኖም ይህ አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ በተለይም በሞያሌ እና በያቤሎ አካባቢዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እና ተቃዋሚዎች የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ይፋ ያደረገውን እና የሞያሌ ከተማን የሚመለከቱ ለውጦችን ያካተተውን የአስተዳደር መልሶ ማዋቀር ዕቅድን በጽኑ አውግዘውታል።

የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ግን እነዚህን ክሶች በመቃወም፣ አዳዲሶቹ ወረዳዎች የተቋቋሙት በአካባቢው ያሉ አስተዳደራዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እንጂ ከኦሮሚያ ክልል መሬት ለመንጠቅ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል አዲሱን አስተዳደራዊ መዋቅር ይፋ ባደረገበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በጉዳዩ ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ይህ ጉዳይ እንደገና ተቀስቅሶ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት መንስዔ ሆኗል።

ዘላቂ መፍትሄ ያጣው የሞያሌ ችግር

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በአርሲ ሺርካ በተፈጸሙ ግድያዎች ላይ መግለጫ ቢያወጣም ስለ ሞያሌ ግን እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ ለቀናት የቀጠለ ግጭት ባስተናገደችው ሞያሌ ከተማ ጉዳይ የፌደራል መንግሥት "ዝምታ መምረጡን" ተችቷል።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ በሞያሌ ከተማ እና ቦረና ዞን ውስጥ "እየተባባሰ የመጣውን ጥቃት፣ የታጠቁ ኃይሎችን ሰርጎ መግባት እና ኢ-ሕገመንግሥታዊ የአስተዳደር ለውጦችን" በጥብቅ አውግዟል።

የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር መሐመድ በበኩሉ በሞያሌ የተቀሰቀሰው ግጭት ከሌሎች የአካባቢ ድንበር ውዝግቦች የተለየ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጃዋር ስለ ቀውሱ ሲናገር ግጭቱ በቀላሉ በቦረናና በገሪ ማኅበረሰቦች መካከል ያለ ውዝግብ ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ያስረዳል።

"ገሪ እና ቦረና አንድ ሕዝብ ናቸው። ወንድማማቾች ናቸው። በወንድማማቾች መካከል አለመግባባት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ይህ በተደጋጋሚ ወደ ትጥቅ ግጭት መሸጋገሩ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የተፈጠረ ክስተት ነው" ብሏል።

ጃዋር አክሎም በደርግ ዘመን ባለሥልጣናት ከአንዱ ማኅበረሰብ ጋር በመወገን በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ክፍፍል ለማስፋት እንደሞከሩ ገልጾ፣ ይህም ለረዥም ጊዜ የቆየ ውጥረት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል።

ሁለቱ ማኅበረሰቦች ምንም እንኳን ጥብቅ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ትስስር ቢኖራቸውም በተከታታይ የተለያዩ አካላት በማኅበረሰቡ መካከል ያሉ ቅሬታዎችን ለራሳቸው ጥቅም ሲጠቀሙበት ቆይተዋል ብሏል።

በ1997 ዓ.ም. በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ሥር በሚገኙ አካባቢዎች በቦረናና በገሪ ማኅበረሰቦች መካከል የነበረውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ነበር።

ሆኖም ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት የሚዳርጉ ግጭቶች በየጊዜው ሲከሰቱ ቆይተዋል።

ጃዋር አክሎም "ከእንዲህ ዓይነቱ ግጭት ትልቁን ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉት የመንግሥት የጸጥታ ተቋማት ወይም በኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩ አካላት ናቸው" ብሏል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ ሰፋፊ የሕገወጥ የሰው ዝውውር እና የንግድ መረቦች መስመሮች መኖራቸውን ጠቅሷል።

ጃዋር መንግሥት ለሰባት ቀናት የቀጠለውን ይህንን ግጭት ለመቆጣጠር በፍጥነት ጣልቃ መግባት ነበረባቸው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ቢቢሲ ከሰላም ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ከአዲስ አበባ በ775 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሞያሌ በ1909 ዓ.ም. ነበር ሕጋዊ ዕውቅና አግኝታ ከተማ የሆነችው።

እንደ የድንበር እና የንግድ ከተማነቷ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች በጋራ ይኖሩባታል።

ሆኖም ፌደራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት ይፋ ከተደረገ በኋላ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እየተነሳ በሞያሌ እና በአካባቢው በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭቶች መፈጠር ጀምረዋል።

የነበረውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት 11 ቀበሌዎችን ለሶማሌ ክልል ሲሰጥ 17 ቀበሌዎችን ደግሞ ለኦሮሚያ ክልል ሰጥቷል።

ይህ ውሳኔ ግን በሞያሌ ከተማ ያለውን ችግር የፈታው በጥቂቱ ብቻ ነበር።

በ2004 ዓ.ም. የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በሽግግር መንግሥቱ ምላሽ ያልተሰጣቸውን ጉዳዮች እንደሚፈታ ታምኖበት የነበረ ቢሆንም ችግሩ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።