አሜሪካ የሞት ቅጣት በጥይት ድብደባ፣ በጋዝ እና በኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲፈጸም ልትፈቅድ ነው

ሞት ቅጣት የሚፈጸምበት አልጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት የአገሪቱ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሞት ቅጣትን የሚፈጸምባቸው ዘዴዎች ዝርዝር ውስጥ በጥይት መደብደብ፣ በጋዝ ማፈን እና የኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲያካትቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

አርብ ዕለት ይፋ በሆነው ባለ 48 ገጽ ሰነድ መስሪያ ቤቱ የሞት ቅጣት "እንደሚጠናከር" ገልጿል። ይህ እርምጃ "እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለተጎጂዎች ፍትሕ ለመስጠት እና ለሟች ቤተሰቦች ለረጅም ጊዜ የዘገየ መጽናኛን ለመስጠት" እንደሚረዳም በሰነዱ አብራርቷል።

የቀድሞው የአሜሪካ አስተዳደር በአብዛኛዎቹ የፌደራል የሞት ቅጣቶች ላይ እገዳ ጥሎ ነበር። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በፊት የሞት ቅጣት ከተፈረደባቸው 40 የፌዴራል እስረኞች መካከል ለ37ቱ ምህረት አድርገዋል።

ፕሬዝዳንትነቱን የተረከቡት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ወደ ቤተ መንግሥት በገቡ የመጀመሪያው ቀን ፍትሕ መስሪያ ቤቱ የሞት ቅጣትን እንዲያስጀምር ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

መስሪያ ቤቱ አሁን ለማረሚያ ቤቶች በላከው መልዕክት 'ፔንቶባርቢታል' የተባለውን መድኃኒት በመርፌ በመውጋት ለሚፈጸም የሞት ቅጣትን ያለው ድጋፍ ገልጿል።

አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 1993 ጀምሮ የፌደራል የሞት ቅጣቶችን ለማስፈጸም የምትጠቀመው ይህንን ዘዴ ሲሆን ተሟጋቾች ግን ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ዘዴ ነው በማለት ተቃውሞ ያቀርቡበታል። ቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ መድኃኒቱን ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

ቅጣቱ የሚፈጸምበት አማራጩን መስፋቱ "ይህ መድኃኒት ባይገኝም እንኳ ሕጋዊ የሞት ቅጣቶችን መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ" የፍትሕ መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሞት ቅጣት ያላቸውን ድጋፍ ለረጅም ጊዜ ሲገልጹ ቆይተዋል። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ለ20 ዓመታት ተጥሎ የነበረውን የሞት ቅጣት እገዳ ያነሱ አድርገዋል። በዚሁ የሥልጣን ዘመናቸውም 13 ሰዎች የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።

በጥር 2025 በድጋሚ ወደ ሥልጣን በተመለሱበት የመጀመሪያ ዕለት "የወንጀሉ ክብደት እንዲፈጸም በሚያደርግባቸው ሁሉም ወንጀሎች" እንዲሁም ሕገ ወጥ ስደተኛ የሕግ አስከባሪ አካልን በሚገድልበት ወቅት የሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።