የተበሳጩ ነዋሪዎች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ሆስፒታል ድንኳኖችን አቃጠሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቫይረሱ ምክንያት እንደሞተ የሚገመት ወጣት ቤተሰቦች እና ጓደኞች አስከሬኑን ለቀብር እንዳይወስዱ በመከልከላቸው የተበሳጩ ሰዎች በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ማዕከል ሆስፒታልን የተወሰነ ክፍል አቃጠሉ።
"በሆስፒታሉ ላይ ቁሳቁስ መወርወር ጀመሩ። ለለይቶ ማቆያ ክፍሎች የሚያገለግሉ ድንኳኖችንም እንኳን አቃጠሉ" ሲሉ የአካባቢው ፖለቲከኛ ሉክ ማሌምቤ በሩዋምፓራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስለተመለከቱት ጉዳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሁከቱ ውስጥ ፖሊስ ሕዝቡን ለመበተን የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን ተኩሷል።
በኢቦላ ምክንያት የሞተ ሰው አስከሬን በሽታውን በከፍተኛ ደረጃ አስተላላፊ በመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መቀበር ይኖርበታል።
በኢቱሪ ግዛት ቡኒያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሩዋምፓራ ሆስፒታል የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ፖሊስ ስርዓት ለማስከበር በሚንቀሳቀስበት ወቅት በወታደራዊ ጥበቃ ስር እንዲቆዩ ተደርገዋል።
የሕግ አስከባሪዎች ጣልቃ ከመግባታቸው በፊት አንድ የጤና ባለሙያ ድንጋይ በሚወረውሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶበታል ሲሉ የሆስፒታሉ ባልደረባ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የሞተው ግለሰብ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ስለነበር በሞቱ የተበሳጩ ሰዎች "የበሽታውን እውነታ አልተረዱም" ሲሉ በኢቱሪ የኢቦላ ምላሽ አስተባባሪ የሆኑት ዣን ክላውድ ሙኬንዲ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
የዓይን እማኞች በበኩላቸው ወጣቱ ከብዙ የአካባቢ ቡድኖች ጋር የተጫወተ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበር ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል። እናቱ ለዜና ማሰራጫው ልጇ በኢቦላ ሳይሆን በታይፎይድ ህይወቱ ማለፉን እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
ማሌምቤ እንዳሉት ህዝቡ እስካሁን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ130 በላይ ሰዎችን የገደለው ቫይረስ እውነተኛ መሆኑን አላመነም።
"ሕዝቡ ስለተከሰተው ነገር በትክክል አልተረዳም ወይም አላወቀም። ለተወሰነው የሕዝቡ ክፍል በተለይም በሩቅ አካባቢዎች ለሚገኙት ኢቦላ በውጭ ሰዎች የተፈጠረ የሌለ ነገር ነው" ብለዋል ፖለቲከኛው።
"መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሆስፒታሎች ናቸው ይህንን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የፈጠሩት ብለው ያምናሉ። ይህ ደግሞ አሳዛኝ ነው።"
ሁለት ድንኳኖች እና ሊቀበር የተዘጋጀ አስከሬን ተቃጥሏል ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢቦላ ሰለባዎች "ደህንነቱ የተጠበቀ እና ክብር ያለው የቀብር ሥነ ሥርዓት" እንዲደረግ ይመክራል። ይህም የሰለጠኑ ባለሙያዎች አስከሬኑን ለመቅበር የመከላከያ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙም ይመክራል።
ስድስት ታካሚዎች በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ በሚገኙ ድንኳኖች ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን በሁከቱ ምክንያት ሸሽተው ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል።
ድንኳኖቹን የሚያስተዳድረው አሊማ የተባለው የሕክምና በጎ አድራጎት ድርጅት ሁሉም ታካሚዎች መኖራቸውን እና "በአሁኑ ጊዜ በሆስፒታሉ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ የተገለጸው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የነበረውን የዓለም ዋንጫ ቅድመ-ዝግጅት በወረርሽኙ ምክንያት መሰረዙ ከተነገረ በኋላ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት "የዓለም አቀፍ ስጋት የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ" ብሎ ቢጠራውም በወረርሽኙ ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ገልጿል።
ተቋሙ ረቡዕ ዕለት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ600 ተጠርጣሪዎች መካከል 139 ሰዎች በኢቦላ እንደሞቱ ተናግሯል።
በተመሳሳይ ቀን የኮንጎ የጤና ሚኒስትር ሳሙኤል ሮጀር ካምባ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን 159 ሰዎች ሞተዋል ብለዋል።
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጎረቤት በሆነችው ኡጋንዳ ሁለት የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል።















