የኢቦላ ክትባት ለማዘጋጀት ዘጠኝ ወራት ሊፈጅ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

የኢቦላ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን ለመለየት የሰውነት ሙቀቱ የሚለካ ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተረጋገጡ 51 ኬዞች ተመዝግበዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ዝርያ የሚከላከል ክትባት ለማግኘት እስከ ዘጠኝ ወራት ድረስ ሊፈጅ እንደሚችል ተናገረ፡፡

'ቡንዲቡጊዮ' የተባለውን የኢቦላ ዝርያ ለመቆጣጠር ሁለት ክትባቶች በእጩነት የቀረቡ ቢሆንም እስካሁን የትኛውም ክትባት የክሊኒካል ሙከራ እንዳልተካሄደበት የድርጅቱ አማካሪ ዶ/ር ቫሴ ሙርቲ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳስታወቁት 600 የሚጠሩ የኢቦላ ኬዞች አሉ።139 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል።

ለቫይረሱን ክትባት ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ ረጅም በመሆኑም እነዚህ አሃዞች እንደሚጨምሩ ይጠበቃል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተያዘ ሰው በተገኘበት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስከአሁን 51 የተረጋገጡ ኬዞች የተገኙ ሲሆን በጎረቤት ኡጋንዳ ደግሞ ሁለት ሰዎች እንደተገኙ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዕሑድ የዓለም የጤና ድርጅት ኢቦላን ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ሲል የበየነው ሲሆን፤ ሆኖም የወረርሽኝ ደረጃ ላይ አለመድረሱን አስታውቋል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተረጋገጡት 51 ኬዞች የተገኙት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ኢቱሪ ግዛት እና ሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የተገኙት ሁለቱም ሰዎች ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጡ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ የአንደኛው ሕይወት አልፏል።

"በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው የበሽታው መጠን ከዚህ በላይ እንደሆነ እናውቃለን" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል። ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት በመጥቀስ፤ ይህ ክስተት በተለይ አሳሳቢ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

በአካባቢው ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የመከላከያ ግብዓቶች መድረስ ቢጀምሩም፣ አሁንም በቂ ግብዓቶች እንደሌላቸው ይገልፃሉ፡፡

የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የአደጋ ፕሮግራም ኃላፊ ትሪሽ ኒውፖርት የጤና ተቋማት በተጠረጠሩ ኢቦላ ታካሚዎች እንደተሞሉ እና በቂ አልጋዎች እንደሌሏቸው እንደሚገልፁ ተናግረዋል፡፡

"ይህ አሁን ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያሳያል" ሲሉ ለኤኤፍፒ ገልፀዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች ቫይረሱ ከመቼ ጀምሮ እንደተስፋፋ ለማወቅ ምርመራ እንደጀመሩ ተናግረው፤ ነገር ግን ዋና ትኩረታቸው ስርጭቱን መቆጣጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመጀመሪያው የታወቀ ኬዝ በኢቱሪ ዋና ከተማ ቡኒያ ነርስ የሆነች ታማሚ ስትሆን፤ ምልክቶቹን ካሳየች በኋላ በሚያዚያ አጋማሽ ሕይወቷ አልፏል።

ኢቦላ እ.አ.አ በ1976 በዛሬዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ከሌሊት ወፎች እንደመጣ ይታመናል፡፡

ለሰዎች በሽታ የሚያመጡ አራት የኢቦላ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተደጋጋሚ የተከሰተው ዝርያ የተለመደው ነው።

አገሪቱ አሁን 17ኛውን የኢቦላ ወረርሽኝ እየተጋፈጠች ሲሆን የቡንዲቡጊዮ ዝርያ በአስርት ዓመታት ውስጥ ያልታየ እና የራሱን ልዩ ችግሮችን ያመጣ በሽታ ሆኗል።

ይህ ዝርያ ቀደም ሲል እ.አ.አ በ2007 በኡጋንዳ እና በ2012 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሁለት ጊዜ ብቻ ተከሰቶ ነበር። በበሽታው ከተያዙት ሰዎች አንድ ሦስተኛዎቹን ገድሏል።