የ90 ዓመቷ አዛውንት በደቡብ ኮሪያ የልጃቸውን የወንጀል ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለዋል በሚል ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ ኮሪያ ልጃቸው ከአደገኛ ዕፅ ዝውውር ያገኘውን ትርፍ ሕጋዊ በማስመሰል ያጠቡ የ90 ዓመት አዛውንት የአንድ ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ስማቸው ያልተጠቀሱት ሴት እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2022 በዘጠኝ የተለያዩ ጊዜያት ከ260 ሺህ ዶላር በላይ በመቀበል የልጃቸውን መመሪያ ይዘው በባንክ አካውንት ውስጥ ማስገባታቸው ተነግሯል።
ሶንግ የሚል መጠሪያ በዘገባዎች የተሰጠው ልጃቸው ሜታፌኔሚን በተባለ የአደገኛ ፅፅ ዝውውር ወንጀል ተፈርዶበት ከ2020 ጀምሮ በካምቦዲያ በእስር ላይ ይገኛል።
ሠኞ ዕለት በዋለው ችሎት የሶንግ እናት በ2019 ብቻ ካምቦዲያን አምስት ጊዜ የጎበኙ ሲሆን፤ ልጃቸውም የታሰረበትን ቦታ ማወቃቸው ገንዘቡ ሕገ ወጥ መሆኑን መረዳት ይችላሉ ተብሏል።
ብይኑን ያስተላለፉት ዳኛ የ90 ዓመቷ ሴት እርምጃ ከአደገኛ ዕፅ የተገኘ ሕገ ወጥ ትርፍን ለመከታተል ከባድ እንዳደረገ እና አዛውንቷ የዕፅ ዝውውር እንዲስፋፋ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሲሰጥ የተከሳሿን እድሜ እና ከዚህ ቀደም ከአደገኛ ዕፅ ጋር የተያያዘ ወንጀል አለመስራታቸውን ከግምት ውስጥ አስገብቷል።
የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ሶንግ የተባለውን ልጃቸውን ከካምቦዲያ ተላልፎ እንዲሰጣቸው ለማድረግ እየመኮሩ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በ60ዎቹ እድሜ ውስጥ ነው የተባለው ሶንግ ልጁንም የወንጀሉ ተባባሪ እንዳደረገ መቀመጫውን ሶል ያደረገ ጋዜጣ ዘግቧል።
ልጁ 600 ሚሊዮን ወን ሕገ ወጥ ገንዘብ በመቀበል እና 274 ሚሊዮን የሚሆነውን በማስተላለፍ ፍርድ ቤት መቅረቧ ታውቋል።
በኋላ ላይ ፍርድ ቤቱ ገንዘቡ ከዕፅ ዝውውር የመጣ መሆኑን ስለማወቋ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ባለማግኘቱ ክሱን ሰርዞላታል።












