ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመተከል ዞን ዋና ከተማ በተፈጸመ ጥቃት "ሰባት የቄራ ሠራተኞች" መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ግልገል በለስ የሚገኝ "ማረሚያ ቤትን ሰብረው ለመግባት" የሞከሩ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው የፓርላማ ተመራጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የፓርላማ አባሉ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እንደሚያስረዱት ታጣቂዎቹ በግልገል ከተማ ተኩስ የከፈቱት ለአርብ ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም. አጥቢያ 11 ሰዓት ገደማ ላይ ነው።
ታጣቂዎቹ "ግልገል በለስ ከተማን ከብበው፤ ከፍተኛ ጥቃት" መክፈታቸውን የሚገልጹት ዶ/ር መብራቱ፤ ዋና ዒላማ የነበረው ግን በከተማው የሚገኘው ማረሚያ ቤት "መቆጣጠር" እንደነበረ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም ማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት መከፈቱን ጠቅሰዋል። አንድ ነዋሪ፤ "የጉሙዝ ታጣቂዎች ናቸው ለመግባት የሞከሩት። ማረሚያ አካባቢ የራሳቸውን አባላት ለማስፈታት ነው" ብለዋል። ሌላ ነዋሪም ጥቃቱ የተከፈተው "በጉሙዝ ታጣቂዎች" መሆኑን ጠቅሷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አለሙ በበኩላቸው "ከጉሙዝ ሰላም ተመላሽ ውስጥ ያልተስማሙ፣ በሰላም አንመለስም ካሉት ወገኖች ውስጥ እንደሆነ ነው ያለኝ መረጃ የሚያሳየው። ግን ከሌሎችም የታጠቁ ቡድኖች ጋር አብረው እንደመጡ ነው ያለኝ መረጃ" ብለዋል።
አንድ ነዋሪ እንደገለጸው፤ ታጣቂዎቹ ተኩስ መለዋወጥ የጀመሩት ከማረሚያ ቤት ፖሊስ ጋር ሲሆን ኋላ ላይ "ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ፌደራል ፖሊስ" ለተከፈተው ጥቃት ምላሽ ሰጥተዋል።
ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት በአካባቢው ሥራ ላይ የነበሩ "ሰባት የቄራ ሠራተኞች" መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል። አንድ ነዋሪ ደግሞ የተገደሉት ሰዎች ብዛት "አምስት" እንደሆነ ጠቅሷል።
ማረሚያ ቤቱ እና የከተማው ቄራ የሚገኙበት ስፍራ ተቀራራቢ መሆኑን የሚያስረዳው አንድ ነዋሪ፤ "በአጋጣሚ በመሃል የተገኙ የቄራ ሠራተኞች፣ ሰባት አካባቢ ተገድለዋል። እዛ ለእርድ የሄዱ ናቸው" ብሏል።
ዶ/ር መብራቱም በተመሳሳይ "ትልቅ ተኩስ ነበር የፈጠሩት። በዚህ ሂደት ውስጥ ልኳንዳ፣ ቄራ የሚሠሩ አራጆች ነበሩ። ምንም ስለማያውቁ፣ ሌሊት ስለሚወጡ እነርሱ በጣም ተጎድተዋል። ሰባት የሚደርሱ የቄራ ሠራተኞች ነው ያለኝ መረጃ" ሲሉ በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል።
ከታጣቂዎቹ በኩል ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አክለዋል። አንድ ነዋሪም "በመሃል የተወሰነ ኃይል እየተጨመረባቸው ሲመጣ ወደ ኋላ [አፈገፈጉ]፤ ሁለቱ [ታጣቂዎች] ስቴዲየም አካባቢ ወደቁ። ከሚሊሻም ደግሞ አንድ ሰው ተመታ" ሲል ተጨማሪ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን አብራርቷል።
ታጣቂዎቹ ማረሚያ ቤቱ ላይ በከፈቱት ጥቃት እስረኞችን እንዳላስለቀቁ ነዋሪዎች እና የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል። ዶ/ር መብራቱ "ሊሳካቸው አልቻለም። የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ትልቅ ተጋድሎ አድርገው ያንን ነገር ማስቀረት ችለዋል" ሲሉ ያሰባሰቡትን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።
ከ2011 ዓ.ም. አንስቶ ተከታታይ ጥቃቶች ካስተናገደ በኋላ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበት የነበረው መተከል ዞን ካለፈው ዓመት አንስቶ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በጉሙዝ ታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተፈተነ ነው። በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት በዞኑ ቡለን ወረዳ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት "20 ሰዎች" እንደተገደሉ አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፓርላማ አባሉ ዶ/ር መብራቱም በተመሳሳይ "ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ በድባጤ ወረዳ፣ ቡለን ወረዳ፣ በተለይም ወንበራ ወረዳ በተለይ በሸኔ ታጣቂዎች፤ ድባጤም በጉሙዝ ታጣቂዎች ብዙ ንጹኃን ዜጎች በዚህ 10 ቀን ውስጥ የሞቱበት ሂደት አለ" ሲሉ የደረሱ ጥቃቶችን ዘርዝረዋል።
ቢቢሲ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከመተከል ዞን አስተዳደር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።