መነጋገሪያ የሆነው ሕንዳዊቷ ዳኛ ለተደፈረች ሕጻን የጻፉት ደብዳቤ

ታዳጊ ሴት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሕንዳዊውቷ ዳኛ ለተደፈረችው ሕጻን የጻፉት ልብ የሚነካ ደብዳቤ መነጋገሪያ ሆኗል።

ዳኛዋ ለታዳጊዋ በጻፉት ደብዳቤ ላይ የደፈራት ግለሰብ "ቀሪ ዕድሜውን እስር ቤት እንደሚኖር" ነግረዋታል። የተደፈረችውን ሕጻን "በብርቱነቷም" አሞግሰዋል።

ዳኛዋ ራጃኒ ራንጋ ለ10 ዓመቷ ሕጻን የላኩትን ደብዳቤ የጀመሩት "ውዲቷ ልጅ" ብለው ነው።

ሕጻኗ በአውሮፓውያኑ 2023 ስትደፈር ሰባት ዓመቷ ነበር።

ዳኛዋ "በዚህ ፍርድ ቤት ካየሁዋቸው ሁሉ ደፋሯ አንቺ ነሽ" ብለዋታል።

ሕጻኗን የደፈራት ግለሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ ፍርደኛው "ቀሪ ዕድሜውን በእስር ቤት እንደሚያሳልፍ" ተገልጿል።

ለሕጻኗ የ10,941 ዶላር (1.05 ሚሊዮን ሩፒ) ካሳም ተሰጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዳኛዋ ውሳኔያቸውን ካሳወቁ በኋላ "ጥቃት ለደረሰባት ልጅ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ዳኛዋ ሕጻኗን ማነጋገር የሚፈልጉት እንደ ዳኛ ሳይሆን "የልጅቷን ድምጽ እንደሰማች ዳኛ" መሆኑን ተናግረዋል።

ከሕጻኗ የሰሙት ነገር እና ደፋርነቷ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።

"ይሄን ሰውዬ እስከሚያረጅ ድረስ እስር ቤት አቆዩት ብለሽ ስትጠይቂ ፍርድ ቤቱ አዳምጦሻል፤ ፍርድ ቤቱ ለጥያቄሽ ምላሽም ሰጥተዋል" ሲሉም ለሕጻኗ ደብዳቤ ጽፈዋል።

በሕንድ ውስጥ ጎልማሳ ወንዶችን 'አጎት' ብሎ የመጥራት ልማድ አለ።

ሕጻኗ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበችው ተማጽኖ "ይሄ አጎት ከእስር እንዳይለቀቅ" ማለቷን ዳኛዋ አስታውሰዋል።

"ይሄ 'አጎት' ያልሽው ሰው መቼም ቢሆን ነጻ አይወጣም" ሲሉ ዳኛዋ በደብዳቤያቸው ለሕጻኗ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

"ቀሪ ሕይወቱን ከብረት ፍርግርግ ጀርባ ታስሮ ያሳልፋል። እዚያው እያለ ያረጃል፤ እዚያው ይሞታል" ብለዋል።

በደብዳቤያቸው "መቼም ቢሆን ሊጎዳሽ አይችልም። መቼም መቼም ቢሆን አንቺንም፣ ታናሽ እህትሽንም፣ ወይም ሌላ ልጅንም ሊጎዳ አይችልም" ሲሉ ጽፈዋል።

ዳኛዋ ሕጻኗን "እጅግ ደፋሯ ልጅ" ሲሉ አሞግሰዋታል።

ወደ ፍርድ ቤት በመሄዷ፣ የጎዳትን ሰው በማጋለጧ እና እውነቱን በመናገሯ "ደፋር" መሆኗን ዳኛዋ ገልጸዋል።

"ይሄ 'አጎት' ያልሽው ሰው በጣም ክፉ ድርጊት ፈጽሞብሻል። አንቺ ግን ዝም አላልሽም። ለእናትሽ ተናገርሽ። ለመናገር ድፍረቱን ስላገኘሽ ከዚህ በኋላ የትኛዋንም ልጅ ሊጎዳ አይችልም። ነጻ ሰው ሆኖ እንደማይለቀቅ ፍርድ ቤቱ ቃል ይገባልሻል።"

ዳኛዋ የጻፉትን ደብዳቤ ያጠናቀቁት እንደሚከተለው ነው።

"ፍርድ ቤቱ ልጅነትሽን መልሶ ሊሰጥሽ አይችልም። አሁን ሕይወትሽን ኑሪ፣ ትምህር ቤት ሂጂ፣ ጓደኞች አፍሪ፣ ሳቂ፣ ተጫወቺ፣ አልሚ። ፍርድ ቤቱ ጀግንነትሽን እስከወዲያኛውን ያስታውሰዋል።"

ዳኛዋ ራጃኒ ራንጋ ደብዳቤውን የጻፉት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው።

በሕንድ ሕጻናት ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃት የሚዳኘው በልዩ ፍርድ ቤት ነው። 'ፕሮቴክሽን ኦፍ ችልድረን ፍሮም ሴክሽዋል ኦፌንስስ' የተባለው ይህ ፍርድ ቤት የተጎጂዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ውሳኔዎቹን ይፋ አያደርገም።

ፍርደኛው በደልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ውድቅ ተደርጎበታል። በዋስ ለመውጣት እና የእስሩ ጊዜም እንዲቀነስለት አቤቱታ አቅርቦ ነበር።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍርደኛውን ስም ይፋ ከማድረግ በዘለለ ስለ ግለሰቡ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

ፍርድ ቤቱ ዳኛዋ ለሕጻኗ የጻፉትን ደብዳቤ "አበረታች መልዕክት" ብሎታል።

የደልሂ ዐቃቤ ሕግ የዳኛዋን ደብዳቤ እና የካሳ ገንዘብ ለሕጻኗ እንዲያደርስም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የዳኛዋ ደብዳቤ በርካታ ሕንዳውያንን ስሜታዊ አድርጓል።

"በብዛት የማይታይ" እና "የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ" ሲሉ ደብዳቤውን አሞካሽተዋል።

ሕጻኗ በሰባት ዓመቷ መደፈሯ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በመግለጽ በርካቶች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

በእርግጥ ዳኛዋ የጻፉት ደብዳቤ እምብዛም የተለመደ አይደለም።

በሕንድ የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃቶችን በሚዳኘው ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ 69,000 ክሶች መቅረባቸውን የመንግሥት መረጃ ይጠቁማል።

አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ተጎጂዎች በሚያውቋቸው ሰዎች መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

ተጎጂዎች በሚያምኗቸው ወይም እንክብካቤ በሚሰጧቸው ሰዎች ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። ስለ አብዛኞቹ ጥቃቶች ለፖሊስ መረጃ ሳይሰጥ፣ ክስም ሳይመሠረት ይቀራል።

ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሕይወታቸው ላይ እስከወዲያኛው ጠባሳ ጥሎባቸው እንደሚያልፍ እና መላው ሕይወታቸው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይናገራሉ።

ዳኛዋ ራጃኒ ራንጋ ብይን ሲሰጡ ባደረጉት ንግግር እነዚህ ጥቃቶች ሕጻናት ላይ ዘላቂ ቁስል እንደሚጥሉ ተናግረዋል።

ብይን የሰጡት "የወንጀሉን ሁኔታ በመመርመር፣ የደረሰውን ጉዳት ጥልቀት በመፈተሽ እንዲሁም በሕጻኗ የጣለውን የዕድሜ ልክ ጠባሳ ከግምት ውስጥ በማስገባት" መሆኑን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ሕጻኗ "እንድታገገም እና ሕይወቷን ወደነበረበት እንድትመልስ" ያለመ መሆኑን አክለዋል።