ማንቸስተር ሲቲ አሸንፎ የነጥብ ልዩነትን ቀንሷል፤ አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ስንት ነጥቦች ያስፈልጉታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ምሽት ብሬንትፎርድን 3 ለምንም በማሸነፍ አርሰናል ላይ ጫናውን እያበረታው ይገኛል።
ለሲቲ ዠርሚ ዶኩ፣ ኧርሊንግ ሃላንድ እና ኡማር ማርሙሽ በሁለተኛው አጋማሽ ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ቡድኑ ከአርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ሁለት ሆኗል።
አርሰናል ዛሬ ምሽት የመውረድ አደጋ ከተደቀነበት ዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያከናውናል።
አርሰናል ዋንጫውን ለማንሳት ምን ያህል ተጨማሪ ነጥቦች እንደሚያስፈልገው እና ድሉን መቼ ሊያሳካ እንደሚችል እንመለከታለን።
ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ምሽት ብሬንትፎርድን 3 ለምንም በማሸነፉ የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ሁለት ሳምንታት ቀርተውትም እስካሁን የዋንጫው ማረፊያ አልታወቀም።
አርሰናል የዋንጫው ጉዳይ በእጁ ውስጥ ይገኛል።
ዛሬ ወደ ዌስትሃም አጭር ጉዞ በማድረግ ጨዋታቸውን የሚጀምሩት አርሰናሎች የቀሩትን ጨዋታዎቻቸውን ካሸነፉ ወይም ከዚህ በኋላ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ተመሳሳይ ውጤት እያገኙ ከቀጠሉ ሊጉን ዋንጫ ያነሳሉ።
አርሰናል ስንት ነጥቦች ያስፈልገዋል?
አርሰናል እአአ ከ2004 ወዲህ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ ለማሸነፍ ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች ያስፈልጉታል።
ማንቸስተር ሲቲ አሁን ማግኘት የሚችለው ከፍተኛው ነጥብ 83 ሲሆን አርሰናል እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገው የነጥብ ብዛት ሰባት ብቻ ነው።
ይህ ማለት ከቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ድሎች እና አንድ አቻ ውጤት ካስመዘገቡ በጎል ልዩነት ዋንጫውን ወደ ኤምሬትስ መውሰድ ይችላሉ ማለት ነው።
ማንቸስተር ሲቲ ብሬንትፎርድን ካሸነፈ በኋላ በአንድ የጎል ልዩነት የበላይ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ መቼ ሊያሸንፍ ይችላል?
ሁለቱም ቡድኖች ሁሉንም ጨዋታዎቻቸውን ካሸነፉ አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሊያሸንፍ የሚችልበት ጊዜ የሚሆነው በመጨረሻው ሳምንት ከክሪስታል ፓላስ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል።
ማንቸስተር ሲቲ በተመሳሳይ ቀን ከአስቶን ቪላ ጋር ይጫወታል። በ2022 መጨረሻ ቀን ጨዋታ ኢካይ ጉንዶሃን ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ 3 ለ 2 ቪላን ያሸነፈበት ጨዋታ ይታወሳል።
ሲቲ ረቡዕ ዕለት ከክሪስታል ፓላስ ጋር ነጥቦችን ከጣለ ከዚያ ቀደም ብሎ አርሰናል ዋንጫውን ሊያሸንፍ ይችላል።
አርሰናል ዛሬ ዌስትሃምን ካሸነፈ እና ሲቲ ከፓላስ ጋር አቻ ቢለያይ ልዩነቱ አምስት ነጥብ ብቻ ሆነው ሁለት ጨዋታዎች ይቀራሉ።
ይህም ማለት አርሰናል ግንቦት 10 ከበርንሌይ ጋር ሲጫወት የሊጉን አሸናፊነት ያረጋግጣል ማለት ነው። ምክንያቱም ጨዋታውን ማሸነፉ ከሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ብቻ ከሚያገኘው ማንቸስተር ሲቲ በስምንት ነጥቦች ያስቀድመዋል።
ማንቸስተር ሲቲ የፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፍ ይችላል?
የማንቸስተር ሲቲ ወደ ዋንጫው ማሸነፍ የመመለስ ብቸኛው ተስፋው አርሰናል ነጥቦችን ከጣለ ነው።
ለምሳሌ አርሰናል ከዌስትሃም ጋር አቻ ቢለያይ ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን በማሸነፍ በጎል ልዩነት ወደደረጃ ሰንጠዡ አናት የመመለስ ዕድል ይኖረዋል።














