ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 'ተልዕኮዬ ሠላምን መስበክ ነው' ሲሉ ለትራምፕ ትችቶች ምላሽ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሰነዘሩባቸው ትችት ወንጌልን እና ሠላምን መስበክ እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ምላሽ ሰጡ።
ሊቀ ጳጳስ ሊዮ አክለውም ማንም ሰው ሊተቻቸው እንደሚችልም ተናግረዋል።
ስለሊቀ ጳጳሱ በቅርቡ አስተያየታቸውን የሰጡት ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቢኖራት ችግር የለውም ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲህ ዓይነት አለመናገራቸውን ነገር ግን አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የገጠሙትን ጦርነት መቃወማቸውን አስረድተዋል።
አቋማቸው ትራምፕን አስቆጥቶ ደጋግመው እንዲተቿቸው በር ከፍቷል።
የሰሞኑ ውዝግብ የመጣው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በዚህ ሳምንት ለሁለት ቀናት ጉብኝት ወደ ቫቲካን ሊያመሩ መሆኑን ተከትሎ የመጣ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሩቢዮ ከጣሊያን እና ከቫቲካን ጋር "የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማሳደግ" እና "በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታ" ከጣሊያን ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
ሩቢዮ ከጉብኝታቸው በፊት በትራምፕ እና በቫቲካን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ወደ ጣሊያን ይሄዳሉን መባሉን አስተባብለዋል።
"ከዚህ በፊት ያቀድነው ጉዞ ነው። በኋላም በግልጽ የተከሰቱ ነገሮች ነበሩን" ብለዋል፣ "ከቫቲካን ጋር ብዙ የምንነጋገረው ነገር አለ" ሲሉ አክለዋል።
ማክሰኞ ዕለት ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ ትችቶች ቢኖሩም የሠላም ጥሪ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
"የቤተክርስቲያኗ ተልዕኮ ወንጌልን ሰላምን መስበክ ነው" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
"አንድ ሰው ወንጌልን በመስበኬ ሊተችኝ ከፈለገ... የእግዚአብሔር ቃል ዋጋ ስላለው ብቻ እንዲሰማኝ ተስፋ አደርጋለሁ።"
በቅርቡ ትራምፕ ለወግ አጥባቂው የሬዲዮ ቶክሾው አዘጋጅ ሂዩ ሄዊት እንደተናገሩት ፖፑ "ብዙ ካቶሊኮችን እና ብዙ ሰዎችን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው" ምክንያቱም "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መያዟ ጥሩ ነው ብለው ያስባሉ" ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ግን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራት እንደሚደግፉ አልተናገሩም።
በቫቲካን የአሜሪካ አምባሳደር ብሪያን በርች በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጥረት ቢኖርም በአሜሪካ እና በቫቲካን መካከል "የተካረረ ግጭት" የለም።
"አገሮች አለመግባባት ሲኖራቸው እነዚህን ከሚፈቱበት መንገዶች አንዱ... በወንድማማችነት እና በእውነተኛ ውይይት በኩል ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ በርች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"በሆነ መንገድ ጥልቅ የሆነ መለያየት አለ የሚለውን ሃሳብ አልቀበልም" በማለት አክለው ሩቢዮ በጣሊያን በሚያደርጉት ጉብኝት ሁለቱ ወገኖች ማንኛውንም ልዩነት "እንዲወያዩ" ያስችላቸዋል ብለዋል።
አለመግባባቱ በትራምፕ እና በቀድሞዋ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊ እና በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ መካከል ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ጠቅላይ ሚንስትሯ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተችተው ፖፑን ተከላክለዋል።
በዚህ ሳምንት ሩቢዮን ያገኙ እንደሆነ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ሜሎኒ "እንደዛ አስባለሁ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖፕ ሊዮ ባለፈው ወር በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ግጭት በተደጋጋሚ ሲቃወሙ ከመቆየት ባለፈ "እንደ መጋቢ ጦርነትን መደገፍ አልችልም" ብለዋል።
"ሁሉም ከጥላቻ እና ከመለያየት ቦታ ሳይሆን ከሠላም ባህል የሚመጡ መልሶችን ለመፈለግ ጥረት እንዲያደርጉ ማበረታታት እፈልጋለሁ" ብለዋል።
ትራምፕ የመጀመሪያውን የአሜሪካ ተወላጅ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ "በወንጀል ላይ ደካማ" እና "ለውጭ ፖሊሲ የማይጠቅሙ" በማለት በመጥራት ምላሽ ሰጥተዋል።
"ፖፕ ሊሆኑ ከሚችሉት ዝርዝር ውስጥ አልነበሩም፤ በቤተክርስቲያኑ የተሾሙት አሜሪካዊ ስለነበሩ ብቻ ነው። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመቋቋም ይህ በጣም ጥሩው መንገድ እንደሆነ ስላሰቡ ነው" ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል። "ዋይት ሐውስ ባልሆን ኖሮ ሊዮ በቫቲካን አይሆንም ነበር።"
ሃይማኖታቸውን ወደ ካቶሊክ የለወጡት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስም የትራምፕን ሃሳብ ተከላክለው ቫቲካን "በሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባት" ብለዋል።














