አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የምትሰጠውን ቪዛ ገደበች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ መድልዎ ይፈጽማሉ ስትል በወነጀለቻቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ገደብ ጣለች።

የትራምፕ አስተዳደር ደቡብ አፍሪካን በበርካታ ጉዳዮች የተቸ ሲሆን ከእነዚህም መካከል እኩልነትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች የአገሪቱን ነጭ ማኅበረሰብ አባላት የሚያገልሉ ናቸው ብሏል።

የደቡብ አፍሪካ ነጮች አፍሪካና በመባል የሚታወቁ ሲሆን ዝርያቸው የሚመዘዘው ከደች እና ከፈረንሳይ ሰፋሪዎች ነው።

ደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ ይህንን ውንጀላ አጣጥላለች።

"የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቀደም ሲል ይፋ ያደረግናቸውን ስጋቶች በበቂ ሁኔታ አላስተካከለም" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት ገደቦቹን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የቪዛ ገደቦቹ "በዘር ላይ የተመሰረተ መድልዎን የሚያበረታቱ፣ ዓመፅ የሚያነሳሱ ወይም በደቡብ አፍሪካ ያለ ካሳ የመሬት ውርስን የሚያበረታቱን" ዒላማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሩቢዮ በእንቅስቃሴ ገደቡ ዒላማ የተደረጉ ግለሰቦችን ወዲያውኑ አላሳወቁም።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየቀነሰ መጥቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለአገሪቱ የሚሰጥ እርዳታን በማቋረጥ፣ የደቡብ አፍሪካን አምባሳደር ከአገራቸው ያባረሩ ሲሆን "ኢ ፍትሃዊነትን" ለሸሹ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን "የስደተኝነት ፈቃድ" ሰጥተዋል።

ነገር ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነጮችን ያሳድዳል ወይም መሬታቸውን እየወረሰ ነው የሚለውን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

የነጮችን ዘር የማጥፋት ክሶች በሰፊው ተቀባይነት እንደሌላቸው እና አስተማማኝ ማስረጃ እንደሌለ ተረጋግጧል ሲልም አስረድቷል።

የደቡብ አፍሪካ የቅርብ ጊዜ የወንጀል መረጃዎችን የሚያሳዩ ቁጥሮች ከሌሎች የዘር ቡድኖች በበለጠ ነጮች ለዓመፅ ወንጀል ሰለባ መሆናቸውን አያመለክትም።

ትራምፕ ባለፈው ዓመት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግሥት መሬት ያለ ካሳ እንዲወስድ የሚያስችል ሕግ ከፈረሙ በኋላ ለአፍሪካነርስ የስደተኛነት መብት ሰጥተዋል።

ሕጉ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ንብረት እንዲወርስ ይፈቅዳል፤ እንዲሁም ካሳ ላይሰጥ የሚችልባቸውን ሁኔታዎችም ይደነግጋል፤ ነገር ግን ባለሥልጣናት በቅድሚያ ከንብረት ባለቤቶች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲሞክሩ ይደነግጋል። በዚህ መካከል አለመግባባቶች የሚከሰት ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት ሊያመሩ እንደሚችሉ ሕጉ በግልጽ አስቀምጧል።

የአፓርታይድ አገዛዝ ካበቃ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ በደቡብ አፍሪካ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ውዝግብ ያለበት ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።

መንግሥት ታሪካዊ ኢ ፍትሃዊነትን ለመፍታት የመሬት ማሻሻያ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ አዲሱ ሕግ የዘፈቀደ ወረራዎችን እንደማይፈቅድ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል።

ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታይድ ሥርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬት አናሳ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።

በደቡብ አፍሪካ የነጮች ቁጥር 7 በመቶ ብቻ ቢሆንም 72 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የእርሻ መሬት ይቆጣጠራሉ።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በኦቫል ኦፊስ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገራቸው ውስጥ ነጭ ገበሬዎች እየተገደሉ እና "እየተሰደዱ" እንደሆነ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስም የተገደሉ ነጭ ገበሬዎች የቀብር ቦታዎችን የሚያሳይ ነው ያለውን ቪዲዮ አጫውቷል።

ቪዲዮዎቹ በ2020 በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተተከሉ መስቀሎችን የሚያሳይ ሲሆን ከዚያ ቀደም ለሞቱ ገበሬዎች መታሰቢያነት የተተከሉ ነበሩ።