ፌስቡክ ላይ በቀረበ ተማጽኖ ልቡ ተነክቶ ለማያውቃት እናት ኩላሊቱን የለገሰው ደግ ግለሰብ

የፌስቡክ ጽሑፏን ያየው ጌሪ ሰመርፊልድ ኩላሊት ሊለግሳት ፈቅዷል
የምስሉ መግለጫ, የፌስቡክ ጽሑፏን ያየው ጌሪ ሰመርፊልድ ኩላሊት ሊለግሳት ፈቅዷል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ካረን ዴቪ 41 ዓመቷ ነው። ኩላሊት ለማግኘት ያደረገቻቸው ጥረቶች ሁሉ አልሳካ አሏት። አማራጭ ስታጣ ፊቷን ወደ ፌስቡክ አዞረች።

ፌስቡክ ገጿ ላይ እባካችሁ ኩላሊት ስጡኝ ብላ ተማጸነች። ባልተጠበቀ ሁኔታ ፈጽሞ የማታውቀው ሰው ኩላሊት ሊሰጣት ፈቃደኛ ሆነ።

"ልጆቼን ያለ እናት መተው አልፈልግም" ትላለች ካረን።

የፌስቡክ ጽሑፏን ያየው ጌሪ ሰመርፊልድ ኩላሊት ሊለግሳት ፈቅዶ፣ ባለፈው ሐምሌ ላይ አንድ ኩላሊቱን ሰጥቷታል።

ካረን የአራት ልጆች እናት ናት። የፌስቡክ ጽሑፏን ያየው ጌሪ "ይቺ ሴት እኔ ሁለቱን ኩላሊቶቼን ከምፈልጋቸው በበለጠ አንዱ ኩላሊቴ ያስፈልጋታል ብዬ አሰብኩ" ይላል።

የካረን ቤተሰብ የጌሪን ውለታ መቼም ቢሆን መመለስ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በደጉ ጌሪ ምክንያት ካረን "እናት የመሆን ሁለተኛ ዕድል አግኝታለች" ይላሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ኩላሊት ለማግኘት በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት መጠበቅ ያስፈልጋል።

"ልጆቼን ያለ እናት መተው አልፈልግም" ትላለች ካረን
የምስሉ መግለጫ, "ልጆቼን ያለ እናት መተው አልፈልግም" ትላለች ካረን

ኩላሊት የሚለግስ ሰው ከተገኘ ግን ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ብቻ ይወስዳል።

ካረን ሕይወቷን የታደገ የኩላሊት ቀዶ ሕክምና ሲደረግላት የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ከ10 ዓመት በፊት የልብ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል። በ31 ዓመቷ ልጇ እግር ኳስ ሲጫወት እያየችው ሳለ የልብ ድካም ገጥሟት ነበር።

በቀዶ ሕክምና የሰውነት አካል ሲለወጥ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድል ይጨምራል። ለዚህም ምክንያቱ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምናው በኋላ መውሰድ ያለባቸው መድኃኒት እና ቀዶ ሕክምናን ተከትሎ የሚመጣ የጤና እክል ነው።

ካረን ኩላሊቷ መሥራት ያቆመው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።

"የልብ ቀዶ ሕክምናው ኩላሊቴን እንደሚጎዳው አውቅ ነበር። መጠኑን በተቻለው ሁኔታ ለመቀነስ ሞክረዋል። ከልብ ቀዶ ሕክምናው በኋላ የኩላሊት ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገኝ አውቅ ነበር። ይሄንን በአእምሮ መያዝ ከባድ ነገር ነው።"

ጌሪ "ይቺ ሴት እኔ ሁለት ኩላሊቶቼን ከምፈልጋቸው በላይ አንዱን ኩላሊቴን ትፈልገዋለች" ይላል
የምስሉ መግለጫ, ጌሪ "ይቺ ሴት እኔ ሁለት ኩላሊቶቼን ከምፈልጋቸው በላይ አንዱን ኩላሊቴን ትፈልገዋለች" ይላል

ካረን ደረጃ ሦስት የኩላሊት መድከም ነበረባት። ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ ከእሷ ጋር የሚጣጣም የደም ዓይነት ስለሌላቸው ኩላሊት ሊሰጧት አልቻሉም። እሷም ተማጽኖዋን ወደ ፌስቡክ ወስዳዋለች።

የተለየ የደም ዓይነት እንዳላት እና ኩላሊቷ መድከሙ ሕይወቷን ባለበት እንደገታው የሚገልጽ ጽሑፍ በፌስቡክ ገጿ አስፍራለች።

"ዋናው ትኩረቴ ልጆቼ ናቸው። ለእነሱ ስል መኖር እፈልጋለሁ" ብላለች።

የመጀመሪያ ልጇ 22 ዓመቷ ነው። ካረን የአንድ ዓመት የልጅ ልጅም አላት።

"የልብ ቀዶ ሕክምና ያደረግኩት ከ10 ዓመት በፊት ነው። ልጆቹ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በከባድ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ነው። የኩላሊቴ ጉዳይ ሌላ ፈተና ጨምሮባቸዋል" ትላለች።

ጌሪ የደኅንነት ጥበቃ ባለሙያ ነው። የካረንን የፌስቡክ ጽሑፍ ሲመለከት ሊረዳት ወሰነ።

"የካረንን ተማጽኖ አየሁት። ልጆቿን በጽሑፏ ጠቅሳለች። የካረን ዕድሜ እና የልጄ ዕድሜ ተቀራራቢ ነው። የመጀመሪያ ልጇ ከእኔ የልጅ ልጅ ጋር እኩል ዕድሜ አላቸው። ለልጆቿ እንዴት ከባድ እንደሆነ ተረዳሁ።"

የካረን ቤተሰብ የጌሪን ውለታ መቼም ቢሆን መመለስ እንደማይችሉ ተናግረዋል
የምስሉ መግለጫ, የካረን ቤተሰብ የጌሪን ውለታ መቼም ቢሆን መመለስ እንደማይችሉ ተናግረዋል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጌሪ "ልጄ ብትሆን ኖሮ በቤተሰቦቻችን እና በጓደኞቻችን በኩል ሁሉንም አማራጮች እንሞክር ነበር። የማናውቀው ሰው ለመለገስ እንዲመጣ እፈልጋለሁ። ያንን አለማድረግ ራስ ወዳድነት ነው" ይላል።

"ይቺ ሴት እኔ ሁለት ኩላሊቶቼን ከምፈልጋቸው በላይ አንዱን ኩላሊቴን ትፈልገዋለች" ሲልም ያክላል።

የ60 ዓመቱ ጌሪ ካረንን በአካል ባያውቃትም ኩላሊቱን ለመለገስ ሲወስን ጊዜ አልወሰደበትም።

ከካረን ጋር ተመሳሳይ የደም ዓይነት እንዳለው ለማወቅ፣ የኮሌስትሮል መጠኑን ለመለየት እንዲሁም የሥነ ልቦና ምርመራም ተደርጎለታል።

ጌሪ ለካረን ኩላሊት ሲሰጣት የስድስት ሰዓት ቀዶ ሕክምና አድርጓል። ቀዶ ሕክምናው የተከናወነው በዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ኦፍ ዌልስ ነው።

ጌሪ ኩላሊቱን ለመለገስ ከወሰነ በኋላ አንዳችም ጥርጣሬ እንዳልገባው ይናገራል።

"አሁን ካረንን ሳያት ደስ ይለኛል። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ጥሩ ሁኔታ ላይ ናት" ይላል።

"ኩላሊት መለገስ የማግባት እና ልጅ የመውለድ ያህል ደስታ ይሰጠኛል። በሕይወቴ ካደረግኳቸው ሦስት ትልልቅ ነገሮች አንዱ ነው" ሲልም ተናግሯል።

ጌሪ ለካረን ኩላሊቱን በመስጠቱ ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል። "ይሄ ለእሷ እና ለቤተሰቧ ይገባቸዋል" ይላል።

ካረን "አሁን 100 እጥፍ ተሽሎኛል" ትላለች።

ባለቤቷ ማቲው ጌሪ ኩላሊቱን በመለገሱ ደስተኛ ሆኗል።

"ዓለም ምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ሁሉም ሰው ያውቃል። አስከፊ ነገሮች ይፈጠራሉ። እንዲህ ያለ ደግነት ስናይ ግን ተስፋ ይሰጠናል" ይላል።

ማቲው "የጌሪን እና ቤተሰቡን ውለታ መቼም ቢሆን አንመልሰውም። ለካረን ሁለተኛ ዕድል ሰጥተዋል። ለልጆቻችን እናት የመሆን እና የሚገባትን ሕይወት የመኖር ሌላ ዕድል አግኝታለች። የሕይወት ስጦታ አበርክቶላታል" ሲልም አክሏል።

ካረን የማታውቀው ሰው ፈቃደኛ ሆኖ ሕክምና ለማድረግ በመፍቀዱ ትገረማለች።

"ምርመራው ብዙ ነው። ያንን ሁሉ ምርመራ ለማድረግ ፈቅዷል። አንድ ሰው አካሉን በዚህ ውስጥ ለማሳለፍ እና ኩላሊቱን ለማያውቀው ሰው አሳልፎ ለመስጠት ሲወስን ከአእምሮ በላይ ይሆናል። ውለታው አለብኝ።"

የካረን እና ማቲው ልጅ የ17 ዓመቱ ብራንደን እናቱ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ አገግማ ማየቱ "አስደሳች" እንደሆነ ይናገራል።

"አሁን በጣም ደኅና ናት። ለረዥም ጊዜ እንዲህ አልነበረችም። ቀዶ ሕክምና ስታደርግ አስፈሪ መሆኑ አያጠራጥርም። ግን በተስፋ እንጠብቃለን። በዚህ ዓለም ዛሬም መልካም ሰዎች መኖራቸው ያስደስታል።"