ሌ/ጄነራል ታደሰ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዳይቀበሉ በህወሓት ጫና ተደርጎባቸው እንደነበር ተናገሩ

ጄኔራል ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, DW/fb

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለአንድ ዓመት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው የሠሩት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በክልሉ መሪነት እንዳይቀጥሉ ከህወሓት በኩል ጫና እንደተደረገባቸው ተናገሩ።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ለፌደራል መንግሥቱ የአፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ እና የሥልጣን ጊዜያቸው ከተራዘመ በኋላ ህወሓት "ሥልጣን እንዳትቀበል" ብሏቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም. መቀለ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግብዣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ባለፈው ሳምንት የአንድ ዓመት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው ከመጠናቀቁ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሥልጣን ዘመናቸው ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተራዝሞላቸዋል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ህወሓት ስለተቃወመው የሥልጣን ዘመናቸው መራዘም በተመለከተ በሰጡት አስተያየት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ጊዜ ማብቃቱን ተከትሎ የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር እና ክልሉም አስተዳደር አልባ እንዳይሆን ሃሳብ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

"ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ" የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ጊዜ እንደሚያበቃ በመጥቀስ ለድርጅቱ አመራሮች ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን ከህወሓት በኩል ተተኪ ሰውም ሆነ ሃሳብ አልቀረበም ብለዋል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ የፕሪቶሪያ ውል ፈራሚ ከሆነው ህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር "በመመካካር እና በመስማማት" መሆኑን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

ይህንን የሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ንግግርን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከሕጋዊ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት ምንም ያለው ነገር የለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት መራዘሙ ይፋ ከተደረገ በኋላ ህወሓት እርምጃውን "የፌዴራል መንግሥት የተናጠል" ውሳኔ ነው በሚል ተቃውሞታል።

ህወሓት የጄነራል ታደሰ የሥልጣን መራዘምን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ማራዘም የሁለትዮሽ የፖለቲካ ውይይት ሳይደረግ እና የህወሓት እውቅና እና ተሳትፎ ሳይኖር የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የሰጠው ውሳኔ" መሆኑን ገልጿል።

ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመናቸው ከመጠነቀቁ በፊት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ ከመጠራታቸው በፊት በህወሓት የቀረበ አመራጭ ተተኪ ሰው ወይም ሌላ ሃሳብ እንዳልነበረም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የአንድ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ የሌ/ጄነራል ታደሰ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት የተራዘመ ሲሆን፣ ህወሓት ግን የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን መራዘምን እንደማይቀበል እንዲሁም ሌ/ጄነራል ታደሰም ኃላፊነቱን እንዳይቀበሉ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ከህወሓት በኩል "ሥልጣን እንዳትቀበል" መባላቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ ግፊት "ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን አመለክተዋል።

"'ሥልጣን አልፈልግም፤ እምቢ' ማለት መብት ነው፤ ነገር ግን አንተም 'እምቢ በል ሥልጣን እንዳትቀበል' ብሎ ማለት ግን ልክ አይደለም፤ እኔም ይህንን ሃሳብ አልቀበለውም" ሲሉ ሌ/ጄነራል ታደሰ በህወሓት አመራሮች ሃሳብ አለመስማማታቸውን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

"በመወራጨት እና በመዝለፍ የሚፈጠር ነገር የለም" ያሉት ፕሬዝዳንት ታደሰ ከቀያቻው "የተፈናቀሉትን ለመመለስ እና የትግራይን ክልል ሕገ መንግሥታዊ ግዛት ለማስከበር" ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ "የተፈናቀሉ ወገኖቻችን መመለስ እና የትግራይ ክልልን ግዛት ማስጠበቅ ከመፈክር ያለፈ መሆን አለበት" ብለዋል።

ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በአዲስ አበባ ለፌደራል መንግሥት ያቀረቡት ሪፖርት የክልሉ መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈጻጸምን መሠረት ያደረገ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ የፌዴራል መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘ ያወጧቸውን ዘገባዎች በሚመለከት ሲናገሩም፤ "እውነታዎቹ ሊታፈኑ አይችሉም እና በሪፖርቱ ውስጥ የቀረቡት ምሥሎች የቅርብ ጊዜ ናቸው" ብለዋል።

ነገር ግን የቀረቡ ችግሮችም አብረው ሪፖርት አለመደረጋቸው የመገናኛ ብዙኃኑ ክፍተት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በነበራቸው ውይይት እና ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በጦርነት የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፍ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ የበጀት መቋረጥን ተከትሎ የተከሰተው የመድኃኒት እጥረት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ በክልሉ ውስጥ ያለውን የበጀት፣ የመድኃኒት፣ የነዳጅ እና የሌሎች መሠረታዊ እቃዎች እጥረት ቢኖሩም "ትግራይ እጇን እና እግሯን አጣጥፋ አልተቀመጠችም" በማለት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥቱ በጀት ስላልተላከለት ላለፉት ወራት ለሠራተኞ ደሞዝ መክፈል አለመቻላቸውንም ሲናገር ነበር።

ፕሬዝዳንት ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ ፌደራል መንግሥቱ ለትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ፣ ለመንገድ ግንባታ፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለሌሎች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚውል የተወሠነ በጀት መላኩን ገልጸዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝን በተመለከተ ግን ቀጣይነት ያለው ውይይት ያስፈልገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የሌ/ጄነራል ታደሰ ለፌዴራል መንግሥቱ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ላይ በመመሥረት፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ሰፊ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች፣ የመልሶ ግንባታ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸውን አቅርበዋል።

ጊዜያዊ አስተዳዳሪው በመግለጫቸው ዘገባዎቹ "በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አለመጥቀሳቸው የሚዲያዎች ክፍተት ነው" ብለዋል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ተፈናቃዮች ወደ ቀያቻው የመመለስ ጉዳይ እና አወዛጋቢ ግዛቶችን በተመለከተ ያለው ጥያቄ እንዲሁም የታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት እና መሰናበት አሁንም መፍትሄ ያላገኙ ነጥቦች ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ጠንክረው መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና በምንም መልኩ ጦርነት እንዳይከሰት እንደሚሠሩ አመልክተዋል።