ኒጀር ውስጥ ወጣት ወታደሮች በቀሰቀሱት አመጽ በርካቶች መገደላቸው ተዘገበ

ጄነራል ቲቺያኒ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ወደታሮቹ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙትን የአገሪቱ መሪ ጄነራል ቲቺያኒ ቤተ መንግሥትን ዒላማ አድርገው ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በወታደራዊ አስተዳደር ሥር በምትገኘው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ኒጀር ውስጥ ወጣት የሠራዊት አባላት የቀሰቀሱትን አመጽ ተከትሎ በርካታ ወታደሮች መገደላቸውን እና በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘገበ።

በዋና ከተማዋ ኒያሚ ውስጥ ያመጹት ወታደሮች የተወሰኑ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ባመሩበት ጊዜ ግጭት የተፈጠረ ሲሆን የአገሪቱ ቴሌቪዥን ሥርጭትም ተቋርጦ ነበር።

ኒጀር እየተመራች ያለችው ከሦስት ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በያዙት በጄነራል አብዱራህማኔ ቲቺያኒ ነው። ይህ የወታደሮቹ አመጽ የተፈጠረው የእስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት አገሪቱን ክፉኛ እየፈተነ ባለበት ጊዜ ነው።

አርብ ከእኩለ ሌሊት በኋላ የተቀሰቀሰውን አመጽ ተከትሎ በዋና ከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በሚገኙ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ለሰዓታት የቆየ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።

የፕሬዝዳንቱ ታማኝ ወታደሮች አመጹን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ በርካታ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ አማጺያኑ ወታደሮች ይዘዋቸው የነበሩ ቁልፍ መንግሥታዊ እና ወታደራዊ ተቋማትንም መልሰው መቆጣጠራቸው ተገልጿል።

በወታደሮቹ ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር በተያያዘ የተገደሉ በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸው ቢሰማም፣ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን የተረጋገጠ አሀዝ የለም።

ከሩሲያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት አመጹን ለመቆጣጠር ባካሄደው ዘመቻ ውስጥ በቀድሞ ስሙ 'ቫግነር' አሁን ደግሞ 'አፍሪካ ኮርፕስ' ተብሎ የሚጠራው የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል የአየር እና የምድር ድጋፍ ማድረጉን አሶሺየትድ ፕሬስ ተንታኞችን እና ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ዘግቧል።

የፕሬዝዳንቱ ወታደሮች እና የሩሲያ ኃይሎች ሁለት ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን ተቆጣጥረው ከነበሩት አማጺ ወታደሮች ጋር ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ወታደራዊ ተቋማቱን መቆጣጠራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል የዲፕሎማቲክ እና የደኅንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ እና በቤተ መንግሥቱ አካባቢ እስከ ምሽት ከዘለቀው ተኩስ በኋላ በርካታ ያመጹ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ መንግሥታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያም በርካታ የተማረኩ ወጣት ወታደሮች ተሰልፈው አሳይቷል።

በአማጺያኑ እና በመንግሥታት ታማኝ ወታደሮች መካከል ግጭቱ በተካሄደበት ጊዜ እና ከዚያም በኋላ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ጄነራል አብዱራህማኔ ቲቺያኒ የት እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።

አማጺያኑ ወታደሮች ቅዳሜ ማለዳ ላይ ወደ ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት እና የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚውስደውን መንገድ መዝጋታቸውን ተከትሎ ተኩስ የተከፈተ ሲሆን፣ የጣቢያው ሥርጭትም ለሰዓታት ተቋርጦ ነበር። የመንግሥት ኃይሎች መልሰው ከተቆጣጠሩት በኋላም ስርጭቱ ሳይመለስ ቆይቷል።

የኒጀር የመከላከያ ሚኒስትር ጄነራል ሳሊፉ ሞዲ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ያመጹ ወታደሮች ዋና ከተማዋ ኒያሚ ውስጥ በሚገኝ ጦር ሰፈር ውስጥ የተወሰኑ ወታደሮችን ማገታቸውን እና ስማቻውን ባልገለጿቸው "አንዳንድ ቁልፍ ቦታዎች" ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ጨምረውም የመንግሥት ወታደሮች እና የደኅንነት ኃይሎች በፍጥነት ስፍራዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ገልጸው፣ ሕዝቡ እንዲረጋጋ መክረዋል።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተለያዩ የዋና ከተማዋ ክፍሎች ውስጥ የተቀሰቀሰው ከባድ ተኩስ ነዋሪዎችን ከእንቅልፋቸው መቀስቀሱን ተናግረዋል።

በተለይም በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ የሚገኘው እና የሩሲያ ኃይሎች ማዕከል በሆነው ወታደራዊ ሰፈር 101 በሚባለው የአየር ኃይል ሰፈር ውስጥ የነበረው ተኩስ ከባድ እንደነበር የዐይን እማኞች ጠቅሰዋል።

ከባድ ግጭት የተካሄደበት ይህ ቦታ ኒጀር ውስጥ ከሚመረተው ዩራኒየም ውስጥ ከፍተኛ መጠን የሚጓጓዝበት በመሆኑ ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት ነው። አመጹ ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ ተዘግቧል።

በተጨማሪም ጦር ሰፈሩ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት እንዲሁም ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ የፈጠሩት ወታደራዊ ኅብረት ዋና ማዘዣ ማዕከልም ነው።