ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወታደራዊ ሥልጠና ላይ መሆናቸውን አስታወቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የካቢኔ አባላቶች እና ሌሎች የመንግሥታቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሁርሶ ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን አሳወቁ።

ባለሥልጣናቱ የሚወስዱት ወታደራዊ ሥልጠና "የመደመር ሥልጣኔ ታላቁ ስትራቴጂ" የያዛቸውን ሃሳቦች "በተገቢው መንገድ ለመረዳትም ሆነ ለማስፈጸም" ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም. ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ወታደራዊ ልምምዶችን ሲያደርጉ የሚያሳዩ ምሥሎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።

በምሥሎቹ ላይ፣ ባለፈው መስከረም በተመሠረተው መንግሥት ውስጥ በሚኒስትር እና በሚኒስትር ዲኤታነት የተሾሙ ባለሥልጣናት እንዲሁም የሌሎች መሥሪያ ቤቶች አመራሮች የሠልጣኝ ወታደሮች ደንብ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ እና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከባለሥልጣናቱ መካከል ናቸው።

ዐቢይ ከምሥሎቹ ጋር ባጋሩት ፅሑፍ፣ "የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው" ብለዋል።

ወታደራዊ ሳይንስ "የሰውን ልጅ ዓላማና ሰብዕና በመቅረጽ ረገድ ተወዳዳሪ የለውም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሰው ልጆችን "በአካልም፣ በመንፈስም፣ በሥነ ምግባርም፣ በአፈጻጸምም ዲሲፕሊናዊ" ለማድረግ ሲያገለግል መቆየቱን አንስተዋል።

"የመደመር ሥልጣኔ ታላቁ ስትራቴጂን" ተግባራዊ ለማድረግ "ከወታደራዊ ሳይንስ እና ሕይወት" የሚቀሰሙ ዕውቀቶች፣ ክህሎቶች እና ልምዶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጻ "የመደመር ሥልጣኔ ታላቁ ስትራቴጂ" ውስጥ ከያዛቸው ሃሳቦች ውስጥ "የሀገርን ደኅንነት ምንጊዜም ማረጋገጥ"፣ "ለምንምና ለማንም የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባት" እንዲሁም "ከታች እስከ ላይ ያለውን መዋቅር ለሀገራዊ ዓላማ ማሣለጥ" የሚሉት ይገኙበታል።

እነዚህን "የስትራቴጂውን ሃሳቦች በተገቢው መንገድ ለመረዳትም ሆነ ለማስፈጸም ወታደራዊ ሥልጠናው የማይናቅ ሚና ይጫወታል" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

ዐቢይ፣ "ወታደሮች ዒላማ፤ ሲቪሎች ደግሞ ዓላማ አላቸው፡፡ የሁለቱም ግብ ድልን ማስመዝገብ ነው፡፡ ሁለቱን ዲሲፕሊኖች በማገናዘብ ዒላማውንም የሚመታ፤ ዓላማውንም የሚያሳካ ትውልድ እንፈጥራለን" ብለዋል

ባለሥልጣናቱ እየወሰዱ ያሉት ወታደራዊ ሥልጠና መቼ እንደጀመረ እና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቀ አልተገለጸም።

የከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ወታደራዊ ሥልጠና እየተሰጠ ያለው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ዳግም ውጊያ ተቀስቅሶ የአገሪቱ ሠራዊት ከትግራይ አጋሮቹ ጋር አብዛኛውን የክልሉን ክፍል በተቆጣጠረበት ወቅት ነው።

የመከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር ወደሚዋሰንበት አካባቢ እየተጠጋ ባለበት ጊዜ ላለፉት ዓመታት ፍጥጫ ውስጥ ባሉት ሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አይሏል።

በኢትዮጵያ ያሉ አማጺያንን ትደግፋለች በሚል እና በባሕር በር ይገባኛል ምክንያት እየተወዛገቡ ያሉት ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን ወታደራዊ አቅም በሁሉም ዘርፍ ማጠናከር ከዓላማዎቻቸው መካከል አንዱ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ወታደራዊ ሥልጠና እና በትጥቅ የመከላከያ ሠራዊቱን እያጠናከሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ሳምንት ባደረጉት የሩሲያ ቆይታ፣ ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት የመጀመሪያዋ ያደርጋታል የተባለውን ሱ-35 እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ ጄት መረከባቸውን አስታውቀዋል።