ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግብጿን አሌክሳንድሪያ ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ ከተሞች እየሰመጡ መሆኑን አዲስ የሳተላይት መረጃ አመለከተ
የተወሰኑ የአፍሪካ ትላልቅ ከተሞች ከዚህ ቀደም ከታሰበው በላይ በፍጥነት እየሰመጡ መሆኑን አዲስ ጥናት አመለከተ።
ተመራማሪዎች የአውሮፓ የህዋ የምርምር ተቋም ከሆነው ሴንቲኔል-1 ያገኙትን የሳተላይት መረጃዎች በመጠቀም የ20 የአፍሪካ የባሕር ዳርቻ ከተሞች መሬት ምን ያህል እንደተንቀሳቀሰ ማወቅ ችለዋል።
ጥናቱ የናይጄሪያዋን ሌጎስ እና የግብጿን አሌክሳንድሪያ ጨምሮ የተወሰኑ ከተሞች ከአምስት ዓመት በፊት በተባበሩት መንግሥት የአየር ንብረት ተቋም በሆነው 'ኢንተርገቭርመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ' ከተገመተው በላይ በፍጥነት እየሰመጡ መሆኑን ደርሶበታል።
ለዚህ ክስተት የተወሰኑት ምክንያቶች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም አብዛኞቹ ግን እንደ የከርሰ ምድር ውሃ መውጣት ካሉ የሰዎች እንቅስቃሴዎች ጋር የተገናኙ ናቸው።
የጥናቱ ዋና ጸሐፊ ኦሉዋስይ ዳሾ እንዳሉት የከተሞቹ የመስመጥ ውጤት ብዙውን ጊዜ በቀን በቀን ሕይወታችን የሚታዩ ባይሆኑም በአስርት ዓመታት ውስጥ "የጎርፍ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምሩ ይችላሉ" ብለዋል።
ይህ የሚከሰተው መሬቱ እየሰመጠ በሚሄድበት ጊዜ ከውቅያኖሱ ወለል ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ስለሚሆን እንደሆነ ያስረዱት ተመራማሪው፣ ይህም የባሕር ጠለል ከፍታ የመጨመር አደጋን እንደሚያስከትል ገልጸዋል።
በዚህም እአአ በ2050 ሰባት ሚሊዮን ሰዎች፣ አንድ ሚሊዮን ሕንጻዎች እና 180 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ንብረቶች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቱ ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህ ቀደም ተመራማሪዎች የክትትል ጣቢያዎች እጥረት በመኖሩ የተነሳ በአፍሪካ እየሰመጡ ያሉ ከተሞችን በሚመለከት ወቅታዊ መረጃዎች እንዳይገኙ ማድረጉን ዳሾ ተናግረዋል።
ሆኖም የቨርጂኒያ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም በዓመት እስከ አንድ ሚሊሜትር የሚደርስ የመሬት እንቅስቃሴ እንዳለ መለየት ችለዋል።
ከፍተኛ የጥናቱ ተመራማሪ የሆኑት ማኖችር ሻርዛኢ እንዳሉት 'የሴንቲንል- 1' ሳተላይቶች በቀጣናው መሬት ላይ በየ ከስድስት እስከ 12 ባሉት ቀናት ቅኝት ያደርጋሉ።
ሳተላይቶቹ ወደ ራዳር መልዕክቶችን በማስተላለፍ እና በመቀበል እና ሒደቱን እንዲደጋገም በማድረግ ጥልቅ ግምገማዎች መደረጋቸውን የጂኦ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል።
መልዕክቱ በሚላክበት እና በሚቀበልበት መካከል ያሉት ጊዜያት የተመዘገቡ ሲሆን ያሉ ለውጦች በጊዜ ብዛት መሬት ምን ያህል እንደተንቀሳቀሰች አሳይቷል ብለዋል።
በዚህም በኤክሳንድሪያ እና በሌጎስ ያለው መሬት በዓመት በአማካይ 6 ሚሊሜትር እና 6 ሚሊሜትር ሰምጠው ተገኝተዋል።
ይህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በአሌክሳንድሪያ ያለው የባሕር ጠለል መጠን በ2050 በአይፒሲሲ ከተተነበየው በ36 በመቶ ይጨምራል። ይህ የመሬት የሙቀት መጠን ምን ያህል ሊጨመር ይችላል በሚለው የተቋሙ አማካይ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው።
የአንጎላዋ ሉዋንዳ ከተማም እየሰመጠች ሲሆን እንደ ደቡብ አፍሪካዋ ደርባን ያሉ ሌሎች ከተሞች ደግሞ ባሉበት ወይም ደግሞ በትንሹ ከፍ እያሉ መጥተዋል።
ሺርዛኢ፣ አይፒሲሲ አደጋዎችን ዝቅ አድርጎ እንደገመተ ገልጸው፤ ነገር ግን ስጋቱ ከመጠን በላይ የተገመተባቸው ቦታዎችን ማሳየት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት እቅድ አውጪዎችን ሊረዳቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ይህ ክስተት በአብዛኛው በሰው ሠራሽ እንቅስቃሴዎች መፈጠሩን የገለጹት ተመራማሪው፣ ይህንን የአካባቢ ፖሊሲዎችን በማውጣት መዋጋት ይቻላልም ብለዋል።
ለዚህ አንዱና ዋና ምክንያት የሆነውን በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ከተሞች የውሃ ፍጆታ መጨመር ነው። ከመጠን በላይ የሆነን ውሃ ከመሬት ውስጥ ማውጣት አፈሩን ላይ ጫና ስለሚፈጥር መሬት እንዲሰምጥ ሊያደርግ ይችላል።
በአባይ ወንዝ ላይ የሚገኘው የአስዋን ግድብም ከላይኛው ተፋሰስ አገራት የሚመጣውን ደለል ስለሚያጠለው በአሌክሳንድሪያ እየሰመጠ ያለው መሬት እንዳይተካ እያደረገው እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።
በሌጎስ ደግሞ ሰው ሠራሽ ደሴቶችን ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት እና ልል በሆኑ መሬቶች ላይ የሚደረግ የሕንጻዎች ግንባታ ለመስመጧ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሰው ሰራሽ እንቅስቃሴዎች ናቸው።
ከተሞች እንዳይሰምጡ ለመከላከል ውሃ የሚገኝባቸውን ሌሎች አማራጮች ማቅረብ እና ብዙ ውሃ የማይጠቀሙ ሰብሎችን ማልማት ሊረዱ አንደሚችሉ ጥናቱ ጠቁሟል።
ኦሉዋሴይ ዳሾም 'በሳይንስ አድቫንስስ' ላይ የወጣው ጥናት የአፍሪካ መንግሥታት "ወደፊት የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች፤ በተለይም ደግሞ ለወደፊቱ ትውልዶች በበቂ ሁኔታ እንዲዘጋጁ" ሊረዳቸው እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።