ሩሲያ ዛሬ ከሚጀመረው ጉባኤ ጎን ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ዛሬ ረቡዕ ሞስኮ ውስጥ በሚጀመረው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች "ፍላጎት ካሳዩ" ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ሩሲያ አስታወቀች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ይህንን ያሉት ለሁለት ቀናት ከሚቆየው ጉባኤ አስቀድሞ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም. ከአፍሪካ አገራት ከተወጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።

ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች በመስከረም ወር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ካቋረጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ መድረክ የሚታደሙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ማክሰኞ ማለዳ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በጉባኤው ከመሳተፍ ባሻገር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ ዛሬ ረቡዕ ንጋት ላይ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለመታደም ሞስኮ መግባታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።

"ለሰላም፣ ደኅንነት እና ልማት" በሚል መሪ ቃል ከሚካሄደው ጉባኤ አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ፣ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በፈረንሳይኛ ቋንቋ የቀረበው ጥያቄ፣ "ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሩሲያ ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣለች? ሩሲያ ለቀጣናዊ መረጋጋት እንዴት አስተዋፆ ታደርጋለች?" የሚል ነበር። የሩሲያ እና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ትብብርን የተመለከተ ጥያቄም ተያይዞ ተነስቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ላቭሮቭ፣ "ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በተመለከተ፤ እንደተረዳሁት እየተነጋገርን ያለነው ባሕር በር ስለማግኘት ነው። ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት የተቋረጠውን ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ፍላጎት አለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን ያሳወቀችው የትግራይ ጦርነት በድጋሚ ከተጀመረ ከሳምንት በኋላ መስከረም 21/2019 ዓ.ም. ነበር።

በወቅቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችም በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መሰጠቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ በፈጸመቻቸው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።

አዲስ አበባ የነበሩት የኤርትራ ዲፕሎማቶችም "ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በሆኑ እንቅስቃሴዎች" ላይ ተሳትፈዋል የሚል ክስ ቀርቧል።

የአሥመራው መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ታጣቂዎችን ይደግፋል የሚል ክስ የምታቀርበው ኢትዮጵያ፣ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቱን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ አስታውቃለች።

ለተፈጸመባት ወረራ ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላትም ገልጻለች።

ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደችው ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማቋረጧን ያስታወቀችው በዚያው ዕለት ነው።

ኤርትራ በበኩሏ የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ሦስት ዓመታት ባሕር በር በማግኘት ሥም "የኤርትራ ወደቦችን እና የባሕር ዳርቻዎችን ለመውረር…በይፋ የጦርነት አዋጅ" ስታራምድ ነበር የሚል ክስ አቅርባለች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ከአፍሪካውን ጋዜጠኞች ጋር

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ፣ በአሁኑ ሰዓት በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለመኖሩን አስታውሰው፣ "ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም አንድ አገር እንደነበሩ ሁሉ፣ ለረጅም ጊዜ በጎረቤትነት አብረው ለኖሩ ሁለት አገራት ጥሩ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ "ከረጅም ዓመታት በፊትም" የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት አድርጋ ነበር። የሁለቱ አገራት ተወካዮች "ገለልተኛ ግዛት" በሆነችው ሞስኮ፣ "ስጋቶቻቸውን በሙሉ በመወያየት የሁለቱን ወገኖች የጋራ ፍላጎት ሚዛን ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ" እንዲነጋገሩ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ይህ ዓይነቱ ስብሰባ አንድ ጊዜ ተካሂዶ ነበር፤ ነገር ግን ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር" ያሉት ላቭሮቭ፣ ሩሲያ የአሁኑን የአገራቱ ውጥረት ለማርገብ የማደራደር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።

"አሁን፣ ነገ ወይም ከነገ በስቲያ [ረቡዕ ወይም ሐሙስ] በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሁለቱ አገራት መሪዎች ይህንን ዓይነት ፍላጎት ካሳዩ፣ በእርግጥም ግንኙነት እንዲያደርጉ ሁሉንም ዕድሎች እናመቻቻለን" ብለዋል። የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት አሁን ባለበት የተቋረጠ ሁኔታ አይቀጥልም ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

በጎረቤታሞቹ አገራት መካከል የሚነሳ "ማንኛውም ችግር መልካም ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ" በሚደረስ እና "ፍላጎቶችን በሚያማክል ስምምነት መሠረት ይፈታል" ሲሉም ተናግረዋል።

ሞስኮ ከጉባኤው ጎን ለጎን ሁለቱን አገራት ለማሸማገል ፍላጎት ፈቃደኛ መሆኗን የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር አሊሞቭ ከሳምንት በፊት ለአንድ አገሪቱ ጋዜጣ ተናግረው ነበር። ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ይህንን የሩሲያ ፍላጎት በተመለከተ በይፋ የሰጡት ምላሽ የለም።