እጃቸውን የታሰሩ የጋዛ ተሟጋቾች ላይ ያፌዙት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ሚኒስትር ውግዘት ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, Office Of Itamar Ben Gvir/Handout via Reuters
የፍልስጤም ደጋፊ ተሟጋቾች እርዳታ ጭነው በጀልባዎች ወደ ጋዛ ሲጓዙ በእስራኤል ባሕር ኃይል በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የተያዙበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ ውግዘት ደረሰበት።
የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢትማር ቤን-ጋቪድ እጃቸው ወደ ኋላ ታስረው የተንበረከኩ ተሟጋቾች ላይ ሲያሾፉ መታየታቸውን ተከትሎ ቁጣቸውን ከገለፁ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ካናዳ ይገኙበታል።
የሚኒስትሩ ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም ያልተለመደ ትችት የገጠመው ሲሆን፤ ድርጊታቸውን "ከእስራኤል እሴት ያፈነገጠ" ሲሉ ገልፀውታል።
በእርዳታ እንቅስቃሴው የተሳተፈው ከ40 አገራት የተውጣቱ 430 ሰዎችን የወከለው የመብት ተሟጋቾች ቡድን የታሰሩት ተሟጋቾቹ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ጀልባዎቹ በጦርነት ውድመት የደረሰባት ጋዛ ነዋሪዎች ያሉበትን ከባድ ሁኔታ ለማሳየት እርዳታ የጫኑ ነበሩ። እስራኤል እንቅስቃሴያቸውን "የሐማስ የሕዝብ ግንኙነት እንቅስቃሴ" በማለት አጣጥላዋለች።
50 የሚሆኑ ጀልባዎችን ያካተተው ዓለም አቀፍ ቡድን ባለፈው ሐሙስ ነበር ከቱርክ የተነሳው።
ተሟጋቾቹ ሠኞ ዕለት መሣሪያ በታጠቁ የእስራኤል ባሕር ኃይል ወታደሮች ከጋዛ በ460 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል። የጋዛ የውሃ ዳርቻ በእስራኤል የባሕር ጉዞ እግድ ተጥሎበታል።
"ግሎባል ሱሙድ ፎሎቲላ" የተባለው የተሟጋቾች እንቅስቃሴ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ ሁሉም ጀልባዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
እስራኤልን "ሕገ ወጥ የባሕር ጥቃት" በመፈፀም የከሰሰው ቡድኑ፤ የአገሪቱ ወታደሮች በስድስት ጀልባዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል። የውሃ ጥይት የመተኮስ እና ሆን ብሎ ጀልባ የመገልበጥ ድርጊቶችን እንደፈጸሙም በማንሳት ከስሷል።
የመብት ተሟጋቾቹ ያለፈቃዳቸው ወደ እስራኤል ግዛት እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ አክራሪ ብሔርተኛ የሆኑት የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ቤን-ጋቪር "እንኳን ወደ እስራኤል መጣችሁ" ከሚል ፅሑፍ ጋር ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል።
በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ሚኒስትሩ ተሟጋቾቹ የሚገኙበትን የማቆያ ጣቢያዎችን ሲጎበኙ ያሳያል።
"ነፃ፣ ነፃ ፍልስጤም" እያለች የምትጮህ የመብት ተሟጋችን አንድ የፀጥታ ኃይል እንዲገፋት ሲያበረታቱም ታይተዋል።
ሚኒስትሩ እጃቸው ወደ ኋላ ታስሮ የተንበረከኩ በደርዘን የሚቆጠሩ ተሟጋቾች አጠገብ ትልቅ የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡም ነበር። በሂብሪው ቋንቋ "ወደ እስራኤል እንኳን መጣችሁ። ጌታዎቹ እኛ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሌሎች ተሟጋቾች ደግሞ መርከቡ ላይ ተንበርክከው የእስራኤል ብሔራዊ መዝሙር ይዘመራል።
በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሀከቢ የሚኒስትሩን ሁኔታ "አፀያፊ" ብለውታል።
የሚኒስትሩን ሁኔታ የሥራ ባልደረባቸው የሆኑት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር የነቀፉት ሲሆን፤ በኤክስ ገፃቸው አገራቸው ላይ ሆን ብለው ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሰዋል። እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ሲፈፅሙ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
የእርዳታ ድርጅቱ የመብት ተሟጋቾቹ ሁኔታዎች አስከፊ ለሆኑባት እና 2.1 ሚሊዮን ነዋሪዎች ለተፈናቀሉባት ጋዛ ምግብ፣ የሕፃናት ወተት እና የሕክምና እርዳታዎችን ይዘው እንደነበር ገልጿል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋዛን "በእርዳታ የተትረፈረፈች" ሲሉ የገለጿት ሲሆን ባለፉት ሰባት ወራት 1.5 ሚሊዮን ቶን እርዳታ እና የሕክምና ግብዓት መግባቱን ተናግረዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በጋዛ ተፈናቃይ ቤተሰቦች በተጨናነቁ እና መሠረታቸው በተጎዳ ድንኳኖች እንደተጠለሉ እና የመሠረታዊ አገለግሎቶች አሁንም የተገደቡ መሆናቸውን ከሰሞኑ ተናግሯል።















