"ማስፈራሪያ፣ ቁጥጥር፣ አካል የሚያጎድል ቀዶ ሕክምና"- በጄፍሪ ኤፕስቲን ለዓመታት ብዝበዛ የደረሰባት ሴት ታሪክ

የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን በሞተበት ሳምንት አናያ (ስሟ ተለውጧል) በሯ ተንኳኳ። ኒው ዮርክ የሚገኘውን ቤቷን ያንኳኳው የኤፕስቲን ወንድም ማርክ ነበር።
ማርክ ቤቱን ጥላ መሄድ እንዳለባት እንደነገራት ትገልጻለች። በኒው ዮርክ፣ ማንሀተን የሚገኘው ቤቷ ኤፕስቲን ጥቃት ያደረሰባቸውን ሴቶች የሚያኖርበት ነበር። አናያ ከቤቱ ወጣች።
ማርክ ወንድሙ ኤፕስቲን ጥፋቶች ስለመፈጸሙ እንደማያውቅ ይናገራል።
"ለዓመታት ጥቃት ሲደርስብኝ እንደነበር አሁንም ለማመን እቸገራለሁ። ቤቱ ውስጥ ታስሬ አልተቀመጥኩም አይደል? ቤቱ ተቆልፎብኝ አልኖርኩም አይደል? ምናልባት ሰንሰለቱ አይታይ ይሆናል እንጂ አስሮኝ ነበር።"
ኤፕስቲን ሕጻናትን ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር ክስ ቀርቦበት ሳለ ነበር በአውሮፓውያኑ 2019 የሞተው።
ኤፕስቲን ሰዎች ተታልለው ወይም ተገድደው አባል የሚሆኑበት ቡድን (cult) መሪ እንደሆነ አናያ ታምናለች። እሷም የቡድኑ አባል ነበረች።
ኤፕስቲን ለዓመታት ተጎጂዎችን እንዴት ይዞ እንዳቆየ ለቢቢሲ ተናግራለች። ኤፕስቲንን የሚረዱት ብዙ ሴቶች እንደነበሩ ትናገራለች።
የሚያኖራቸው ኤፕስቲን ሲሆን ያለማቋረጥ ያገለግላሉ። ወሲባዊ ጥቃት ያደርስባቸውም ነበር።
ሥራ ታገኛላችሁ በሚል ማታለያ ተስበው ኤፕስቲንን ሲቀርቡ ሕይወታቸውን ይቆጣጠረዋል። ማንኛውንም ድክመት ካገኘባቸው ይጠቀምበታል።
ገንዘባቸውን ከመቆጣጠር ባሻገር ከማን ጋር እንደሚገናኙ እንደሚወስን እና በሥነ ልቦና ያንቋሽሻቸው እንደነበር ትናገራለች።
አናያ እንደምትለው ሰውነታቸውን አባዜ እንዳለበት ሰው አጥብቆ ይቆጣጠር ነበር። አላስፈላጊ የሆነ እና መልክን የሚያጠፋ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል።
ሳራ ኬለን የኤፕስቲን ረዳት ሠራተኛ ነበረች። ከአናያ ጋር ተመሳሳይ ምስክርነት ትሰጣለች።
ለአሜሪካ ምክር ቤት በሰጠችው ቃል፤ ኤፕስቲን ለረዳት ሠራተኞቹ ራሱን የሚያቀርበው ሊያድናቸው እንደመጣ ሰው ነው።
"ሰዎች በራሳቸው ያላቸውን የመወሰን አቅም እና ኃይል ማክሰም ይችላል። ይህም እሱ ላይ የበለጠ እንዲንተራሱ ያደርጋል" ትላለች።
እንዲህ ባለ ባህሪ ያላቸው ሰዎች የሚያታልሉት ልጆችን እንደሆነ ቢታመንም አዋቂዎችንም ሊያስት እንደሚችል የሥነ ልቦና ባለሙያ ዶ/ር ታራ ኩዊን-ክሪሎ ይናገራሉ።
በማስገደድ የሚቆጣጠሩ ሰዎች ጉዳት ካደረሱባቸው ጋር አብረው የሠሩት ባለሙያዋ የትኛውም ሰው ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice
ኤፕስቲን በአውሮፓውያኑ 2008 ታዳጊ ሴትን በመበዝበዝ ተከስሷል። የማሳጅ ሠራተኛ እንደምትሆን ነገሮ በማታለል ቤቱ ወሰዷታል።
ከዚያ በኋላ በሩሲያ እና በምሥራቅ አውሮፓ የሚኖሩ አዋቂ ሴቶችን ማጥመድ ጀምሯል።
አናያ እንደምትለው እሷ እና ሌሎችም ኤፕስቲን የመለመላቸው ሴቶች ታዳጊ ይመስሉ ነበር።
ያደረገችው ሩሲያ ነው። ወላጆቿ "ስኬት የምታገኚው በትምህርት ነው" እያሉ በጥብቅ ቁጥጥር ነው ያሳደጓት።
ነገር ግን ውስን የሥራ ዕድል ብቻ ነበር ያለው። ዲግሪዋን ይዛ ሞዴል ለመሆን ከአገሯ ወጣች። በአውሮፓ እንደ ፌንዲ እና ሽኔል ላሉ ቅንጡ ብራንዶች ሠርታለች።
ጓደኞች እና የሚደግፏት ወዳጆች ነበሯች። ቤተሰቧን ባሻት ጊዜ ሄዳ መጠየቅ ትችልም ነበር።
ከኤፕስቲን ጋር የተገናኘችው በ20ዎቹ ዕድሜ ሳለች ፓሪስ ወደሚገኝ ኤጀንሲ ሄዳ ነው። ሞዴሎች የሚመለምል ዳንኤል ሲያድ የሚባል ሰው ተዋወቀች።
"በሞዴሎች ዓለም ባልተለመደ ሁኔታ ብሩህ አእምሮ እንዳላት" ዳንኤል ነገራት።
የፋሽን ቢዝነስ ውስጥ ከሚያውቀው ሰው ጋር ሊያስተዋውቃት እንደሚፈልግ ነገራት። ይህ ሰው ኤፕስቲን ነበር።
'ዒላማ አድርገው አጠመዱኝ'
ወደ ኤጀንሲው ባትሄድ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አዘውትራ ታስባለች። ዒላማ እንደተደረገችም ታምናለች።
"ሁሉንም ነገር ቀድመው ነው ያዘጋጁት። ዳንኤል ሰው አዘዋዋሪ ነው" ትላለች።
የዳንኤል ስም በኤፕስቲን ሰነዶች ከሺህ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። የአሜሪካ መንግሥት ያለፈው ታኅሣሥ የኤፕስቲን ሰነዶችን ይፋ ለማድረግ ወስኗል።
የዳንኤል ጠበቃ አስተያየት መስጠት እንደማይችል ቢናገርም ከዚያ በፊት እንደገለጸው ግን ኤፕስቲን አደገኛ መሆኑን አያውቅም ነበር።
አናያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤፕስቲንን የተዋወቀችው 18 ክፍል ባለው የፓሪስ መኖሪያው እንደሆነ ትናገራለች።
ቢል ክሊንተንን ጨምሮ ከሌሎች የዓለም መሪዎች ጋር የተነሳቸው ፎቶዎች በቤቱ ተሰቅለዋል። በክፍሉ ሌሎች ሁለት ሴቶች ስለነበሩ አናያ ምቾት ተሰማት።
አንዷ ሴት ሩሲያዊት ስትሆን ሌላዋ የቀድሞው የኤፕስቲን የቀድሞ የሴት ጓደኛ የነበረች፤ ምሥራቅ አውሮፓዊት ናት።
አናያ ልብሷን እንድታወልቅ እና ሰውነቷ ለሞዴሊንግ ይሆን እንደሆነ ለመቃኘት ኤፕስቲን ጠየቀ።
በውስጥ ሱሪዋ ብቻ ሆና ቆመች። ኤፕስቲን "ሰውነቷ ጥሩ አቋም ላይ ስላልሆነ ስፖርት መሥራት እንድትጀምር" እንደነገራት እና "ሰነፍ" እንዳላት ታስታውሳለች።
ሞዴሎች እንዲህ ያለ አስተያየት እንደሚሰጣቸው ትናገራለች። ታትራ ከሠራች ከትክክለኞቹ ሰዎች ጋር እንደሚያስተዋውቃት አመነች።
ኤፕስቲን ስለ ቤተሶቦቿ እና ምን እንደሚያስደስታት ጠየቃት።
"ለምን ሞዴል መሆን እንደፈለግኩ እና በሕይወት ምን ማሳካት እንደምፈልግ ጠየቀኝ። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች በሞዴሎች ዓለም የተለመዱ አይደሉም" ትላለች።
በርካታ ሴቶች ለቢቢሲ እንደገለጹት ኤፕስቲን የሚያስደስታቸውን ነገር የሚጠይቃቸው ኋላ ላይ መረጃውን እንሱን ለመጉዳት ስለሚጠቀምበት ነው።
ኤፕስቲን "ጎበዝ ልጅ መሆንሽን ማየት እችላለሁ። ተጠራጣሪም ነሽ። እኔ አብሬሽ መተኛት አልፈልግም" እንዳላት ታስታውሳለች።
ይሄንን ስትሰማ ዘና ማለት ጀመረች። "ይሄ ሰው ድንቅ ነው። የውስጤት ማወቅ ይችላል" ብላ አሰበች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ምልመላ'
ይሄ ሁሉ የምልመላው መጀመሪያ ነበር። ለወራት ያህል የቀጠለ ሒደት ሲሆን፣ ለአናያ ብዙ እውነት የማይሆን ቃል እየተገባላት ነበር።
ለአንድ ዓመት ያህል ኤፕስቲን የሚፈልገው ዓይነት ሰውነት እንዲኖራት ያለመታከት ትሠራ ጀመር።
የኤፕስቲን ዋና አጋዥ ሠራተኛ ሌዝሊ ግሮፍ የዕለት ከዕለት ውሎ መዝገቡን ትቆጣጠር ነበር። አናያ ምን ላይ እንደደረሰች የሚገልጽ ኢሜል ትልካለች።
ኤፕስቲንም አናያ እርቃኗን ፎቶ ተነስታ እንድትልክ እና ይሄንን ለማድረግ "ዐይን አፋር" መሆን እንደሌለባት በመግለጽ ጫና ያሳድር ነበር።
ቃል እንደገባውም አናያን 'ኔክስት ኤጀንሲ' ከተባለ የሞዴል ተቋም ኃላፊ ፌዝ ኬትስ ጋር አገናኛት።
የተነጋገሩት ለ30 ደቂቃ ሲሆን ውጤቱን ኤፕስቲን እንደሚያሳውቃት ተነገራት።
የሞዴል ኤጀንሲው አናያ "ለኒው ዮርክ ገበያ ብቁ ስላልሆነች እንደማይፈልጋት" እንደገለጸ ኤፕስቲን ነገራት።
የሰውነት ቅርጿ "የተስተካከለ" እንዳልሆነም ገለጸላት።
አናያ በዚህ ክፉኛ አዘነች። ኤፕስቲንም ፍሎሪዳ፣ ፓልም ቢች ሄዳ እንድታገኘው ነገራት።
በወቅቱ ተከስሶ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ የዚያን ቀን ግን በፈቃድ ተለቅቆ ነበር። የተከሰሰው አንዲት ልጅ በሐሰተኛ መታወቂያ አሳስታው እንደሆነ በወቅቱ ሲናገር ተደምጧል።
አናያ በፖሊስ መዝገብ ላይ ስሟን ጽፋ ከኤፕስቲን ጋር ተገናኘች። ከጀርባ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት ፈጸመባት።
በፖሊስ ይዞታ ላይ ሳለ ቢያንስ ሁለት ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ተናግረዋል።
አናያ ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶ በጀርባ በር ካስወጣት በኋላ ውጪ ላሉ አጋሮቹ "ዐይን አፋር ናት" እያለ መቀለድ ጀመረ።
ሁሉም ስለሳቁባት ራሷን መውቀሷን ትናገራለች።
"ምናልባት የተፈጠረው ነገር ችግር የለውም ብዬ አሰብኩ። ችግሩ እኔ ለነገሩ ምላሽ የሰጠሁበት መንገድ እንደሆነ ተሰማኝ። ሩሲያዊ ቤተሰቦቼ ነገር ስለሚያጠብቁ እና በአስተዳደጌ ምክንያት መሰለኝ። ችግር ያለብኝ ግን እኔ ሳልሆን አሱ ነበር።"
የኤፕስቲን ፋይሎች ይፋ ሲሆኑ በትክክል የተከሰተውን ነገር እንዳወቀች አናያ ትናገራለች።
ሞዴሎችን የሚመለምለው ተቋም ኃላፊን ብታገኝም አብረዋት እንደማይሠሩ የገለጹላት ኤፕስቲን ባለው ወቅት ሳይሆን ከዓመት በኋላ በው።
ከኤፕስቲን ጋር አብራ ወራት ስታሳልፍ ለውድቀት እያዘጋጃት እንደነበር ትናገራለች።
"እየመለመለኝ ነበር" የምትለው አናያ፤ ኤፕስቲን ደካማ በሆነችበት እና ብቻዋን በሆነበችበት ጊዜ ጥቃቱን መፈጸሙን ትገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀስ በቀስ የሚደረግ ምልመላ፤ ዒላማ የተደረጉ ሰዎች እንዳይነቁ እና አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን እንዳይገነዘቡ ያደርጋል ስትል አናያ ትናገራለች።
የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶ/ር ታራ "ከዕይታ ውጪ የሆነ ቦምብ ማለት ነው" ሲሉ ይገልጹታል።
'ኔክስት ኤጀንሲ' የተባለው የሞዴል ተቋም ኃላፊ ፌዝ ኬትስ ጠበቃ በሰጡት መግለጫ፤ ኃላፊቷ በኤፕስቲን የሰዎች ሕገ ወጥ ዝውውር ውስጥ እጃቸው አለ ማለት ወይም ስለ ጉዳዩ ያውቃሉ ማለት "ሐሰተኛ እና ስም ማጥፋት" ነው።
የኤጀንሲውን ውሳኔ ለአናያ የሚያሳውቀው ኤፕስቲን ነው መባሉ "ያልተለመደ፣ ሐሰተኛ እና ማስረጃ የሌለው" መሆኑን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው ሞዴሎቹን የሚመርጠው በራሱ መንገድ እንደሆነ እና የኤፕስቲን ፈቃድ እንደማያስፈልገለው አክለዋል።
ከአንድ ጊዜም በላይ ሞዴሎችን ወደ ኤጀንሲው አለመቀበል የተለመደ አሠራር መሆኑን ጠቅሰዋል።
አናያ ሞዴል የመሆን ዕድል እንዳላት ኤፕስቲን መንገሩን ቀጠለ።
ኤምሲ2 ኤጀንሲ ከተባለ የሞዴሎች ተቋም መሥራች ዣን-ሉክ ብሩኔል ጋር አስተዋወቃት። ኤፕስቲን ተቋሙን በገንዘብ እንደሚደግፍ ግን አልነገራትም።
ተቋሙ አሁን ላይ በማያሚ እና ኒው ዮርክ ያሉትን ቅርንጫፎች የዘጋ ሲሆን፤ እስራኤል የሚገኘው ቅርንጫፍ ከኤፕስቲን ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።
በዚህ ኤጀንሲ በኩል ምንም ሥራ እንዳላገኘች አናያ ትናገራለች። ነገር ግን ቀጥታ ለሥራ ለመመዝገብ ወደ ፓልም ቢች እንድትሄድ በወኪሏ ይነገራታል።
ፓልም ቢች ስትሄድም ኤፕስቲን ብዝበዛውን ቀጠለ። ከዚያም የሞዴልነት ኢንዱስትሪ ስለመሞቱ እና እሷም ስኬታማ ስላልሆነች "ከእሱ ጋር እንድትሠራ" ጠየቃት።
"እኔ እውነተኛ ቢዝነስ አስተምርሻለሁ። ወደ ተለያዩ ቦታዎች ትጓዣለሽ፤ በመላው ዓለም ጠቃሚ ሰዎችን ትተዋወቂያለሽ" አላት።

የፎቶው ባለመብት, Miami Herald via Getty News
'አብረን እንሥራ'
አናያ የኤፕስቲን ረዳት ሆኖ መሥራት ምኞቷ አልነበረም። ኤፕስቲን ስለ ንግድ ምንም እንዳላስተማራት ትናገራለች።
ኤፕስቲን ሥራ እስከሚሰጣት ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ አልነበረትም። ሥራ እስከሚሰጣት ስትጠብቅም ምንም ሳታደርግ በመቀመጧ ያሸማቅቃት ነበር።
አንዳንዴ ስልክ የማንሳት ወይም የመጣውን እንግዳ ማንነት የመናገር ተራ ሥራ ይሰጣታል።
የኤፕስቲን ረዳቶች ሰባቱንም ቀን ለ24 ሰዓት በሥራ ላይ እንዲሆኑ ይጠበቃል።
አናያ ለምሳ ከሰው ጋር በተገናኘች ወቅት ኤፕስቲን እንዴት እንደተበሳጨ እና ያለ እሱ ፈቃድ እንዳትወጣ እንዳስጠነቀቃት ታስታውሳለች።
አናያ ኤፕስቲን ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ሆነች። ስትታመም "የጤና መድኅንሽ እኔ ነኝ" ይላታል።
የባንክ አካውንት አልነበራትም። ቤት እንዳትከራይም የግል ሰነዶች የሏትም።
ኤፕስቲን ማንሀተን ካለው ቤት የተወሰነ ጊዜ እንዳባረራት ትናገራለች። "የት እንደምትኖሪ አስቢ" እያለ ያባርራታል። ይህም ቁጥጥሩን የሚያጠናክርበት መንገድ ነበር።
ከዓመታት በኋላ በቪዛዋ ምክንያት ክፍያ ያስፈልጋት ስለነበር የተወሰነ ደመወዝ ይሰጣት ጀመር።
"አትጨነቂ፤ ሁሌም እደግፍሻለሁ" እያለ ወሲባዊ ብዝበዛውን ቀጠለ።
ሳራ ኬለንም ተመሳሳይ ታሪክ በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርባ ተናግራለች።
"ቤተሰብ አልነበረኝም፤ ገንዘብ አልነበረኝም፤ አልተማርኩም። የተሻለ እንደሚገባኝ አላወቅኩም ነበር" ትላለች።
ኤፕስቲን አቅሙን እና እነ ማንን እንደሚያውቅ ያሳያት ነበር።
"ከእሱ በሚጻረር መንገድ መሄድ ሕይወቴን እንደሚያስከፍለኝ እንዳውቅ አድርጓል" ስትል ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'የብዝበዛ መረብ'
አንድ የኤፕስቲን ተባባሪ ሠራተኛ ያመለጠችበትን ወቅት አናያ ታስታውሳለች።
ለአናያ ስትደውልላት ግን ፍርሃት ገባት። ስልኩን ኤፕስቲን ስለሚከታተል ማውራታቸውን እንዳይደርስበት ሰጋች።
ኤፕስቲን የግል መርማሪ ቀጥሮ ሠራተኛዋን እንዲከታተል አደረገ። ሰባት መቶ ሺህ ዶላር እዳ እንዳለባት ይናገር ነበር።
ኤፕስቲን እያስተላለፈ የነበረው መልዕክት አምልጣችሁ ብትጠፉ እዳ ስለሚኖርባችሁ አሳድጄ እይዛችኋለሁ የሚል ነው።
ኤፕስቲን ሴቶቹን ያሰረው በእዳ ብቻ አይደለም። አናያን እርቃን ምሥሏ እንዳለው ያስታውሳት ነበር።
በአንድ ወቅት ረዳት ሠራተኞቹን በአጠቃላይ ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን ሆነው በደስታ ሲዘልሉ እንዲቀረጽ አደረገ።
"አሁን ከእኔ በተቃራኒው አትቆሙም" እንዳላቸውም ታስታውሳለች።
ቪድዮ ለመቀረጽ ፈቃድ አልሰጠንም ማለት አይችሉም። "ማስረጃዎች የሚሰበስብበት መንገድ ነበር" ትላለች።
ሳራ ኬለን በምክር ቤት በሰጠችው ቃል ኤፕስቲን የሠራተኞቹን ራስን የመግዛት አቅም በማፈራረስ የተካነ ነበር።
"የምስጋና ደብዳቤ" በሚል ኢሜል እንዲልኩለት ያደርጋል።
አናያ "አመሰግናለሁ" ማለት ብቻ በቂ ላይሆን እንደሚችል በማሰብ ትፈራ ነበር።
"እነዚህ ኢሜሎች ያስፈለጉት 'በየጊዜው እያመሰገናችሁኝ ከሆነ እንዴት እኔን ልትገዳደሩ ትችላላችሁ' ለማለት ይመስለኛል።"
ሠራተኞቹ እርስ በራሳቸው እንዲጣሉም ያደርግ ነበር።
"ሰነፍ እና እርባና ቢስ ስለሆንሽ ተናዳብሻለች" ብሎ ስለ አንደኛዋ ሴት ለሌላኛዋ ይነግራል።
"እኔ ግን አንቺን ነው የምደግፈው" ሲልም ክፍፍል ይፈጥራል።
ሴቶቹ ትስስር እንዳይፈጥሩ በማድረግ በቀላሉ መቆጣጠር የሚችልበትን መረብ ዘርግቷል።
አናያ ሆዷ ላይ ጠባሳዎች ይታያሉ። ወጣት ሳለች ትንሽ ንቅሳት ነበራት። ኤፕስቲን ንቅሳቱን እንድታጠፋው ዶክተር ይዞ መሄዱን ትናገራለች።
በጨረራ ንቅሳቱን ማጥፋት ጊዜ ስለሚወስድ ንቅሳቱ ያለበት ቆዳ እንዲነሳ ኤፕስቲን አዘዘ።
"ይሄን ማሰብ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ" ማለቱን ታስታውሳለች።
ቀዶ ሕክምናው ጠባሳ ጥሎባታል። ከዓመት በኋላ በውጤቱ ደስተኛ ስላልሆነ ድጋሚ ቀዶ ሕክምናው እንዲደረግ ወስኗል።
ኤፕስቲን በዚህ ሁሉ ወቅት ሌሎች ሴቶችን እየመለመለ መቀጠሉ "በጣም ያሳፍራል" የምትለው እምባ እየተናነቃት ነው።
አንድ አጋዥ ሠራተኛ ቢያንስ ሌላ አጋዥ ሠራተኛ ማምጣት ይጠበቅባታል። እንደነሱ ያሉ ወጣት ሴቶችን እንዲመለምሉ ይነጋራቸው ነበር።
"አንድም ሆነ አሥር ሰው ተባባሪ ነን" ትላለች።
አሁን ላይ ታሪኳን መናገር የፈለገችው እንዴት ኤፕስቲን ሴቶችን እንደሚያጠምድ እና በወጥመዱ ልጆች ብቻ ሳይሆን አዋቂዎችም ተጠልፈው እንደሚወድቁ ለማሳወቅ እንደሆነ ትናገራለች።
"የብዝበዛ መረብ ዘርግቶ ነበር። ይህም ጠቅሞታል። እንደ ቢል ክሊንተን ያሉ ሰዎች ለእራት ቤቱ እየሄዱ ሲጨብጡት ስናይ 'እኔ ማነኝ ጥያቄ የማነሳው? ማን ስለሆንኩ ነው የምናገረው?' ብለን እናስባለን። ለጥቃቱ እውቅና የሚሰጥ ነው።"
አናያ እና ሳራ ለኤፕስቲን ተጎጂዎች የተዘጋጀው ካሳ ተሰጥቷቸዋል።
ካሳው ተጎጂዎችን በገንዘብ ለመደገፍ የዋለ ሲሆን ማስረጃዎችም ተሰባስበዋል።
"በሕይወት ሳለ ይሄንን ለአንድም ሰው አልተነፈስኩም። አሁን ድምጼ አንዲትም ሴት ብትሆን ከበዝባዥ ግንኙነት እንድትወጣ ይረዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የተለየሁ ሰው አይደለሁም። ግን ከዚህ ጥቃት ለመትረፍ አቅሙን ማግኘት ችያለሁ። እኔ ማድረግ ከቻልኩ አንቺም ትችያለሽ።"















