በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው የኢቦላ የስጋት ደረጃ ወደ "እጅግ ከፍተኛ" ከፍ ተደረገ

ሁለት ማስክ ያደረጉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ በማኅበረሰብ ጤና ላይ የፈጠረውን ስጋት ደረጃ ከነበረበት "ከፍተኛ" ወደ "እጅግ ከፍተኛ" ከፍ አደረገ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ወረርሽኙ በሰፊው የአፍሪካ ቀጣና ላይ የፈጠረው ስጋት "ከፍተኛ" እንደሆነ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን የስፋቱ ደረጃ አሁንም "ዝቅተኛ" መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው "ቡንዲቡግዮ" በተባለው ያልተለመደ የኢቦላ ዝርያ ነው። ከያዛቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛውን የሚገድለው ይህ ዝርያ እስካሁን የተረጋገጠ ክትባት የለውም።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተነሳው ወረርሽኝ እስካሁን ተይዘው እንደሞቱ የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር 177 ደርሷል። በበሽታው እንደተያዙ የተጠረጠሩት ደግሞ 750 ሰዎች ናቸው።

የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታውን የስጋት ደረጃ ከፍ ያደረገው በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለሕክምና ሙከራ ሊደርስ የሚችል አዲስ ክትባት እየሰሩ መሆኑ በተገለጸበት ጊዜ ነው።

ተመራማሪዎቹ ክትባቱን የሚሰሩት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት አስትራዜኒካ የተሰኘውን ክትባት ለማዘጋጀት የተጠቀሙትን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ነው።

ይሁን እንጂ ስለ ክትባቱ ውጤታማነት እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም። ውጤታማነቱን ለማረጋገጥም በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ምርምር መደረግ እንዲሁም በሰዎች ላይ መሞከር ይኖርበታል።

ተመራማሪዎቹ እንስሳት ላይ ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

ሕንድ ውስጥ የሚገኘው 'ሴረም ኢንስቲትዩት' የተባለ ተቋም የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች አስፈላጊውን የሕክምና ግብአት እንዳቀረቡ ክትባቱን በከፍተኛ መጠን ለማምረት ዝግጁ ነው።

ከኦክስፎርድ ሌላም የቡንዲቡግዮ ዝርያ ክትባት ምርምር እየተደረገ ነው። ይህኛው ክትባት ለሙከራ ዝግጁ ለመሆን ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት እንደሚወስድ ይጠበቃል።

የዓለም የጤና ድርጅት የምርምር እና እድገት አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ቫሲ ሞርቲ ከቀናት በፊት ይህ ክትባት "እጅግ ተስፋ ሰጪ" እንደሆነ ተናግረው ነበር።

'ዛየር' ለተባለው የተለመደ የኢቦላ ዝርያ ጥቅም ላይ የሚውለው 'ኢርቬቦ' ክትባት እኩያ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

አርብ ዕለት በጄኒቫ መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ቴድሮስ "አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረው የስጋት ምዘና እጅግ ከፍተኛ፣ በቀጣና ደረጃ ከፍተኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ በሚል እያሻሻልን ነው" ብለዋል።

"እስካሁን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ 82 ሰዎች [በኢቦላ] መያዛቸው፤ ሰባት ሰዎች በበሽታው መሞታቸው ተረጋግጧል" ሲሉም አክለዋል።

በቡንዲቡግዮ ዝርያ ሁለት ሰዎች መያዛቸው እና አንድ ሰው መሞቱ በተረጋገጠባት አጎራባቿ አገር ኡጋንዳ ውስጥ ያለው ሁኔታ "የተረጋጋ" መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጻ ኡጋንዳ ውስጥ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሁለት ሰዎች ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ አገሪቱ የተጓዙ ናቸው።