የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ወደ ሕዳሴ ግድብ የሚገባው ውሃ መቀነሱን በመግለጽ የግብፅን ክስ ውድቅ አደረጉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በኤል ኒኖ ምክንያት ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚገባው የውሃ መጠን "ከሚጠበቀው በታች" መሆኑን እና በዚሁም ምክንያት የግድቡን "ሙሉ አቅም በመጠቀም" ኃይል ለማመንጨት ተይዞ የነበረው ዕቅድ አለመሳካቱን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ክስ ያሰማችበት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተቋረጠውም በአገሪቱ ባለው ጦርነት "መሠረተ ልማቱን ስላወደሙት" እንደሆነም ገልጸዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 22/2018 ዓ. ም. ለመንግሥት ቅርበት ባለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተላለፈ ቃለ መጠይቃቸው ከሰሞኑ የግብፅ ባለሥልጣናት ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያቀረቧቸውን ክሶች ውድቅ አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ካይሮ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን "በፖለቲካዊ" እንዲሁም ግብፅ እና ሱዳን ላይ ተጽዕኖ በሚያደርስ መንገድ እያስተዳደረች ነው የሚል ክስ ማቅረባቸውን የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገራት ጋር "አስቀድማ ቅንጅት ሳታደርግ" በቅርቡ የያዘችው ውሃ "ሱዳን ውስጥ የውሃ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል" በማለት መክሰሳቸውንም ዘገባው ያመለክታል። ይህ የውሃ መጠን መቀነስ "የሱዳን ማኅበረሰብ የውሃ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረም" ተናግረዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ በትናንቱ ቃለ መጠይቅ ላይ ይህንን የግብፅ ሰሞነኛ ክስ አንስተዋል። "ጎረቤት አገርን ይዘው 'የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሱዳንን ጎድቷል፣ እኛንም ውሃ ቀንሶብናል' የሚል ፕሮፖጋንዳ ይዘዋል" ሲሉ ተናግረዋል። "እነሱን ማን ነው ሱዳን ውስጥ ያሉ ግድቦች ጠበቃ ሆነው እንዲቆሙ ያደረጋቸው?" ሲሉም ጠይቀዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ እንደሚያስረዱት፤ ዘንድሮ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ላይ የዝናብ እጥረት እንደሚያስከትል በተተነበየበት 'ኤል ኒኖ' ምክንያት በኢትዮጵያ የተገኘው "ከተጠበቀው በታች" የሆነ የዝናብ መጠን ነው።

"በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ፣ በብዙም ዓለም አገር የኤል ኒኖ ዘመን ነው… የዝናብ መጠን ከተጠበቀው በታች ነው እየመጣ ያለው" ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ፤ በተለይም "በዓባይ ቤዚን፣ ከሰሜን ምዕራብ አካባቢ የሚመጡ ወንዞች" ላይ ለውጡ መታየቱን አረስድተዋል።

በዚህ ክረምት የማዕከላዊ፣ ሰሜን ምሥራቅ እና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚያገኙት የዝናብ መጠን ከመደበኛው በታች ሊሆን እንደሚችል በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሥር ያለው 'ክላይሜት ፕሪዲክሽን ኤንድ አፕልኬሽንስ ሴንተር' መረጃ ያሳያል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ፤ "ምስራቅ አፍሪካ እያጋጠመ ያለው የዝናብ መዛባት ቀጥታ ተፅዕኖው ያለው በወንዞቻችን ላይ ነው" ብለዋል።

በዚህም ምክንያት "74 ቢሊየን ሜትሪክ ውሃ መያዝ" ወዳለበት ሕዳሴ ግድብ የገባው የውሃ መጠን መቀነሱን ጠቁመዋል። "ወደ ሕዳሴ የገባው የውሃ መጠን ራሱ ከሚጠበቀው በታች ነው ማለት ነው። ስለዚህ የሚገባው [ውሃ] ከዛ በታች ከመጣ ከየትም ልናመጣ አንችልም እኛ፣ ተፈጥሮ ስለሆነ" ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ሀብታሙ ገለጻ፤ ይህ የውሃ መጠን መቀነስ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ልታመነጭ አቅዳ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ዝቅ እንዲል አድርጓል። በዚህ ዓመት የሕዳሴ ግድብን "ሙሉ አቅም በመጠቀም" እንዲሁም በአጠቃላይ "38 ጊጋዋት" ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ እንደነበር አስረድተዋል።

"የሚፈለገው የውሃ መጠን ባለመኖሩ 35 [ጊጋዋት] ነው ያመረትነው፤ ሕዳሴ ግድብ፣ ጊቤ፣ ፊንጫ፣ መልካ ዋከና እና ሁሉም ተደማምረው ማለት ነው" በማለት አብራርተዋል።

"በሕዳሴ የሚገባው የውሃ መጠን ከሌለ ከሕዳሴ የሚወጣው ውሃ መጠንም ይቀንሳል" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ባገኙት አጋጣሚ ኢትዮጵያን ከማጠልሸት ወደ ኋላ አይሉም" ሲሉ የግብፅ ባለሥልጣናትን ከስሰዋል።

በሱዳን በኩል የሚነሱ ቅሬታዎች ግን "በዛ ልክ አይደለም" ሲሉ የካርቱም ጉዳይ ከካይሮ ጋር "በጅምላ" መታየት እንደሌለበት ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ እኛ በምናለማቸው ልማት ከማንም በላይ ሱዳኖች ተጠቃሚ ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሱዳኖች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ነበሩ" ሲሉም ለሱዳን የሚቀርበው ኃይል መቋረጡን ጠቁመዋል።

ከሦስት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ አስከፊ የእርስ በእስር ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ከፍተኛ የኃይል መቋራረጥ እያጋጠማት ነው።

የሱዳን የውሃ እና ነዳጅ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ12 ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማቋረጧ ለኃይል መቆራረጡ አንድ ምክንያት እንደሆነ በማንሳት መክሰሱን 'ሱዳን ትሪቡን' ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪ ኃይል ሽያጭ ከምታቀርብላቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት አንዷ ሱዳን ስትሆን፤ መንግሥት በአገሪቱ ባለው ጦርነት ምክንያት ያልተፈጸመ ክፍያ ቢኖርም ኃይሉን ኤክስፖርት ማድረጉን እንደቀጠል ሲገልጽ ነበር።

አሁን ይህ አቅርቦት መቋረጡን የጠቆሙት ዶ/ር ሀብታሙ፤ ምክንያቱ ግን "የመሠረተ ልማት ውድመት" መሆኑን አንስተዋል።

"ሱዳን እስከ ቅርብ ጊዜ፤ እርስ በራሳቸው ሲዋጉ መሠረተ ልማቱን ስላወደሙት የተቋረጠባቸው እንዳለ ሆኖ ከኢትዮጵያ ነበር ሃይል ሲያገኙ የነበሩት" ማለት ተናግረዋል።