ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍሪካ ኅብረት የሱዳን ጦርነት በሱዳናዊያን እንዲፈታ አሳሰበ
የአፍሪካ ኅብረት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ እና አካታች በሆነ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ጦርነት በንግግር እንዲፈታ ያቀረበውን ሐሳብ እና የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች የሰጡትን ምላሽ መመልከታቸውን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀናት በፊት የሱዳን ተዋጊ ኃይሎችን ለማወያየት ቁርጠኛ መኖናቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።
የአፍሪካ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር በበኩላቸው መሰል የእርቅ ሐሳቦችን እንደሚቀበሉ አስታውቀው ነገር ግን ውይይቱ አሳታፊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ በሱዳናዊያን የሚመራ ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ሊቀ-መንበሩ በቡሩንዲው ፕሬዝደንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የሚመራውን የሰላም ውይይት የአፍሪካ ኅብረት እንደሚደግፈው ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሐሙስ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር "ሱዳን [መፈንቅለ-መንግሥት] አጋጠመ፤ ሱዳን በዚያ ግጭት ጊዜ ሮጠን ሄደን ሁሉንም ፓርቲ፣ ሁሉንም ኃይል አስማምተን [በቅድሚያ የሽግግር መንግሥት] የፈጠርነው እኛ ነን" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት በሱዳን ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረባቸውን አውስተው ይህን የምናደርገው "የሱዳን ሰላም ሰላማችን ነው፣ ሕዝቡ ወንድማችን ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ አድርጋ የሱዳን ጉዳይ ወደነበረበት የሚመለስ ከሆነ እኛ ጊዜያችንን ገንዘባችንን ለማጥፋት ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ሐሳብ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) እና ሌሎች የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢቀበሉትም በጄነራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ግን ጥሪውን እንደማይቀበለው አስታውቋል።
የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ያደርጋሉ ሲሉ በተደጋጋሚ ወቀሳ ያቀርባል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ወቀሳ አይቀበለውም። ኢትዮጵያ በበኩሏ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ግብፅ የኢትዮጵያ አማፂያንን ይደግፋሉ ስትል ትከሳለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር "አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ ራሷ ጦርነት ውስጥ ችግር ውስጥ እያለች እንዴት የሰላም ጥሪ ታቀርባለች" ማለታቸው እውነት መሆኑን አምነው "ለዚህ ነው እኛ እየተዋጋን እናንተ ውጊያ የማታውቁ አገራት አትጋብዙ የምንላቸው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"እኛ ተዋግተን ስለምናውቅ መዋጋት መቻል ብቻ ሳይሆን አሸንፎ መስማማትም እናውቃለን፤ ልምዱ አለን ማለት ነው። ተዋግተው የማያውቁ፣ ውጊያ ግጭት እንዴት እንደሚፈታ የማያውቁ፣ ገንዘብ ብቻ የሚቀልቡ አገራት ሰላም ሊያመጡ አይችሉም።"
የሱዳን ጦር፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ አካላት "የሱዳንን አቋም እንዲያከብሩ" ጠይቆ የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ከሚደረግ የትኛውም ውይይት ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንዳትሆን ጠይቋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ የሱዳን ዲፕሎማቶች ከድንበር ከተማዋ ከሚገኝ ቆንስላ ያባረረች ሲሆን፣ ሱዳንም ተመሳሳይ እርምጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ላይ መውሰዷ ይታወሳል።
የሱዳን ጦርነት በሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አል-ቡርሐን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ደጋሎ (ሄሜድቲ) መካከል በተነሳ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 2023 ነበር የተጀመረው።
አራተኛ ዓመቱን በያዘው ጦርነት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 14 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥት መረጃ ያሳያል።