ኢራን "የተኩስ አቁም ጥሰት" በመፈጸሙ የሆርሙዝ ወሽመጥ አይከፈትም አለች

እአአ ሚያዚያ 22 2026 በኢራን ባንዳር አባስ ወደብ የቆመ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ንግግር ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ፤ አሜሪካ እና እስራኤል "የተኩስ አቁም ስምምነቱንን በግልጽ በመጣሳቸው" የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ሊከፈት "አይችልም" አሉ።

መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ረቡዕ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ እንደገለጹት "ከጥሰቶቹ" መካከል የአሜሪካ የባህር ኃይል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዙ ላይ የጣለው እግድ ይገኝበታል።

ይህ የዓለምን ምጣኔ ሃብት "ማሰር" ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፤ እስራኤል ደግሞ "በሁሉም ግንባሮች"፤ "ጦርነት ናፋቂ" አድርጓታል ብለዋል።

የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው ቴህራን ለድርድር ክፍት ሆና ቀጥላለች፤ ነገር ግን "የስምምነቶች መጣስ፣ እገዳ እና ዛቻዎች ለእውነተኛ ድርድር ዋና እንቅፋቶች ናቸው" ብለዋል።

ማክሰኞ ማለዳ ላይ አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አዲስ የሰላም ድርድር ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ቴህራን ወደ ኢስላማባድ ልዑካኗን ባለመላኳ አልተሳካም።

በዚህ የተነሳ የአሜሪካን ልዑክ ይመራሉ የተባሉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ወደ ስፍራው ሳይሄዱ ቀርተዋል።

ማክሰኞ ምሽት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የሚያበቃውን የሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አስታውቀዋል።

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት ፕሬዚዳንቱ ያራዘሙት የተኩስ አቁም የጊዜ ገደብ እንደሌለው አብራርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ላይ እያደረገች ባለው የባህር ጉዞ እገዳ "ደስተኛ" መሆናቸውን እና "ኢራን በጣም እየተዳከመች መሆኗን" መረዳታቸውን ጨምራ ተናግረዋል።

" መጫወቻ ካርዶቹ አሁን በፕሬዝዳንት ትራምፕ እጅ ናቸው" ብለዋል።

ጦርነቱ መቼ እንደሚያበቃ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ሌቪት፤ ይህንን የሚወስኑት ትራምፕ መሆናቸውን አስረድተዋል።

"የዩናይትድ ስቴትስ እና የአሜሪካ ሕዝብ ትክክለኛ ፍላጎት ያሳካ እንደሆነ ሲሰማቸው ይወስናሉ" ብለዋል።

የኢራኑ ተደራዳሪ አስተያየት የተሰማው አደገኛ እና ወሳኝ በሆነው የባሕር መስመር ላይ ግጭቶች በቀጠሉበት ወቅት ነው።

ኢራን በወሽመጡ ላይ እየተንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት መርከቦችን "መያዟን" አስታውቃለች።

ረቡዕ ጠዋት ኢራን ሁለት የጭነት መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ "ለምርመራ" መወሰዳቸውን አስታውቃለች።

የመርከቦቹ መወሰድ ይፋ የተደረገው በባህረ ወሽመጡ ውስጥ በሚገኙ ሦስት የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃቶችን መሰንዘራቸውን ተከትሎ ነው።

በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ጥቃት ከደረሰባቸው ሦስት ኮንቴይነር የጫኑ መርከቦች አንዷ የሆነችው ዩፎሪያ፣ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ባለ ወደብ አቅራቢያ መልሕቋን መጣሏን ቢቢሲ ቬሪፋይ አረጋግጧል።

የባህር ኃይል ደህንነት ላይ የተሰማራው ቫንጋርድ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለቤትነት የተያዘችው ዩፎሪያ ጥቃት የደረሰባት ከኢራን በስተ ምዕራብ መሆኑን ተናግሯል።

በመርከቡ ላይም ሆነ በሠራተኞቹ ምንም ዓይነት ጉዳት መድረሱ አልተመዘገበም።

ኢራን ስለ ዩፎሪያ ምንም ዓይነት አስተያየት ባትሰጥም፣ ሌሎቹን ሁለት መርከቦች ኤምኤስሲ ፍራንቼስካ እና ኢፓሚኖንዳስን መያዟን ተናግራለች።

ሁለቱም በደረሰባቸው ጥቃት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል ባወጣው መግለጫ መርከቦቹ "ያለ ፈቃድ እየተንቀሳቀሱ" እንደነበር ጠቅሶ "ተደጋጋሚ ጥሰቶችን የፈጸሙ" መሆናቸውን በመግለጽ የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ "በሚስጥር" ለቅቆ ለመሄድ እየሞከሩ እና የአቅጣጫ ስርዓቶችን እያዛቡ ነበር በሚል ወንጅሏቸዋል።

በተጨማሪም በባህረ ሰላጤው ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን "እየተከታተለ" እንደሆነ እና "ጥሰት በሚፈጽሙ" ላይ "ጠንካራ" እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው የኢራን የዜና ወኪል፣ ታስኒም በኋላ ላይ የኢራን ኮማንዶዎች ሁለቱን መርከቦች በቁጥጥር ስር ሲያውሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቅቋል።

መርከቦቹ ጥቃት ከደረሰባቸው ስፍራ ሳይንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ የባሕር ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መረጃ የሚከታተሉ ተቋማት ዩፎሪያ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመቅዘፍ ከኾር ፋካን ወደብ ርቆ በሚገኝ ስፍራ ቆማለች።

የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዮርጎስ ጌራፔትሪቲስ በግሪክ ባለቤትነት ስር ያለችው ኤፓሚኖንዳስ መርከብ ጥቃት እንደደረሰበት አረጋግጠዋል።

"በግሪክ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ማረጋገጥ እችላለሁ፤ ነገር ግን በኢራናውያን መያዟን ማረጋገጥ አልችልም" በማለት ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

እንዲሁም ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የባህር ኃይል አዛዡ "ከአሁን ጀምሮ" ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስታውቋል።

ጆን ፌላን ከኃላፊነታቸው ለምን እንደተነሱ የተሰጠ ምክንያት የለም። ይህ የሆነው የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የጦር አዛዡን ራንዲ ጆርጅን ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ከጠየቁ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው። የባህር ኃይል ምክትል ፀሐፊ ሃንግ ካኦ ተጠባባቂ ሆነው ቦታውን እንደሚሸፍኑ ተነግሯል።