የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, POOL / AFP via Getty Images
የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ከሰባት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የረዥም ዘመን አጋራቸውን ሰሜን ኮሪያን ሊጎበኙ መሆኑን የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።
ፕሬዝዳንቱ ሰሜን ኮሪያን የሚጎበኙት በኪም ጆንግ ኡን ግብዣ መሠረት በሚቀጥለው ሣምንት ከሰኔ 1-2/2018 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል።
ፕሬዝዳንት ዢ ፒዮንግያንግን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኙት በ2011 ዓ.ም. ነው።
ጉብኝቱ ፕሬዝዳንት ዢ በፒዮንግያንግን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን እና የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቤጂንግ በተቀበሉ በሳምንታት ውስጥ የሚካሄድ ነው።
ቻይና የሰሜን ኮሪያ ቁልፍ የምጣኔ ሀብት እና ፖለቲካ አጋር ስትሆን፤ በኒውክሌር መርሃ ግብሯ እና በሰብዓዊ መብት ረገጣዋ ምክንያት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የሚበረቱባት አገር ናት።
ፒዮንግያንግ ዋሽንግተንን ዋነኛ የፖለቲካ ባላንጣዋ አድርጋ የምትመለከት ሲሆን፤ ከሩሲያ ጋር ግን ወዳጅነታቸው እያደገ ሲሆን ኪም ለሞስኮ የማያወላውል ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ዢ ምንም እንኳ ከፒዮንግያንግ እና ሞስኮ ጋር የቅርብ ትስስር ቢኖራቸውም እያደረገ የመጣውን የኪም እና የፑቲን አጋርነት በጥርጣሬ ይመለከታሉ።
ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ 1,400 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድንበር የሚጋሩ ሲሆን፤ ቻይና የመከላከያ ትብብር ያላት ከፒዮንግያንግ ጋር ብቻ ነው። ስምምነቱ አንዳቸው ቢጠቁ የጋራ ትብብር ማድረግን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ ስምምነት በዚህ ዓመት 65ተኛ ዓመቱን ይዟል።
ቤጂንግ በኪም አገዛዝ እና በመላው ዓለም እንደ ድልድይ ሆና ለረዥም ጊዜ እያገለገለች ነው።
ፒዮንግያንግ ከደቡብ ኮሪያ ጋር መዋሃድን የሚያመለክተውን የሕገ መንግሥት ክፍል ማሻሻሏን ጨምሮ በሶል ላይ ጠብ አጫሪ ፖሊሲዋን ባጠናከረችበት ወቅት ዢ ሁለቱ ኮሪያዎችን እንዲያሸማግሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ለዚህ ጥሪ ፕሬዝዳንት ዢ "ትዕግሥት አስፈላጊ ነው" ብለው መመለሳቸውን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጃይ ሚኡንግ ተናግረዋል።
ምንም አንኳ ቤጂንግ በኮሪያ ሰርጥ የኒውክሌር መሣሪያ እንዲቀንስ የረዥም ጊዜ አቋም ቢኖራትም፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህን አቋሟን ላላ አድርጋለች።
በዚህ ወር ፕሬዝዳንት ዢ እና ትራምፕ ባደረጉት ንግግር ሁለቱ መሪዎች ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሣሪያዋን እንድትቀንስ የጋራ ግባቸውን ማረጋገጣቸውን የዋይት ሐውስ መረጃ ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ይህን ስምምነት በቀጥታ አላረጋገጡም። ይልቁንም የቻይና አቋም በጉዳዩ ላይ "ቀጣይነት እና ወጥነት ያለው" ነው ብለዋል።
ፒዮንግያንግ በበኩሏ ከኒውክሌር ፍላጎቷ የሚገታት ነገር እንደሌለ ግልፅ አድርጋለች።
በዚህ ሳምንት ኪም ጆንግ ኡን ባለፉት አምስት ዓመታት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማምረት የሚያስችል የንጥረ ነገር ምርት አቅም ከእጥፍ በላይ ማደጉን ተናግረዋል።















