አሜሪካ ከታሪክ ምን ትማራለች? ኢራን የሱዊዝ ቦይ ቀውስን በትራምፕ ላይ እየደገመችው ነው?

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, BBC World Service

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል ከአንድ ወር በፊት በኢራን ላይ የቀሰቀሱት ጦርነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ተወሳስቦ እየተካሄደ ይመስላል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ግርግሩን እያባብሱ እና ዓለም አቀፍ ገበያዎችን እያናወጡ ይገኛሉ።

የትራምፕ አስተያየት ብቻ ሳይሆን ታሪክም የዚህን ጦርነት አቅጣጫ እየቀያየረው ይመስላል።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ባለሙያዎች ጉዳዩን ለመረዳት እና ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለመተንበይ እየሞከሩ ነው። ከእነዚህ መካከል ሦስት ቁልፍ ታሪካዊ ጉዳዮች ጎልተው ይታያሉ።

ሱዊዝ ቦይ

የስዊዝ ቦይ

የፎቶው ባለመብት, Hulton-Deutsch/Hulton-Deutsch Collection/Corbis via Getty Images

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ በግጭቱ ውስጥ አዲስ ግንባር ተከፍቷል።

ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል በተለይ ወደ በሱዊዝ ቦይ የሚመያሩ መርከቦችን የማጥቃት አቅም ስላላቸው በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ መስተጓጎል እንዳይፈጥር ስጋት ደቅኗል።

ቡድኑ 30 በመቶ የሚሆነው ዓለም አቀፍ ኮንቴይነር እና 15 በመቶ ገደማ የሚሆነው የንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፍበትን ወሳኝ የውሃ መስመር መዝጋት ባይችል እንኳን አካባቢውን ሊያምስ ይችላል።

ይህ ደግሞ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የፈጠረችው መስተጓጎል ላይ ሲጨመርበት የዓለም ምጣኔ ሀብት ወደ ውስብስብ ቀውስ ውስጥ በመግባት ውጤቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል።

ተንታኞች የአሁኑን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስረዳት ከ70 ዓመታት በፊት የተከሰተውን የሱዊዝ ቀውስን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

የግብፅ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጋማል አብደል ናስር በአውሮፓውያኑ 1956 የሱዊዝ ቦይን ተቆጣጠሩ። ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ እና እስራኤል ይህንን ለመቀልበስ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀረ።

የግብጽ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጋማል አብደል ናስር

የፎቶው ባለመብት, Hulton-Deutsch Collection/CORBIS/Corbis via Getty Images

ለትራምፕ እና ለአጋራቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዚህ ረገድ ታሪክ አሳሳቢ መልዕክት ያስተላልፋል።

"ከሁሉም በላይ ብሪታንያ የዓለም ኃያል ሆና የቆየችበት ጊዜ እንዳበቃ የሚያሳይ ነው። ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ የነበራት የበላይነት መጨረሻ ነበር" ሲል የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አርታኢ ጄሬሚ ቦዌን ተናግሯል።

ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ወሳኝ በሆኑት መስመሮች ላይ ቴህራን እና ሁቲዎች እየተተገበሯቸው ያሉት ስልቶ ከናስር አካሄድ ጋር ይመሳሰላሉ።

የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ኃይሎች የሱዊዝ ቦይ ሰሜናዊ ጫፍ ዳርቻ ሲደርሱ፣ ናስር በደርዘን የሚቆጠሩ መርከቦችን በማስመጥ ቦዩን ዘግተው ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚጣውን ነዳጅ እንዳይጓጓዝ አቋርጠው ነበር ሲሉ አሜሪካዊው ታሪክ ፀሐፊ አልፍሬድ ደብሊው ማኮይ ጠቁመዋል።

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ድዋይት አይዘንአወር ከሶቪየት ጋር በገቡበት የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተፈጠረውን ይህንን ችግር ለመፍታት ጣልቃ በመግባት ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ እንዲወጡ አስገደዷቸው።

"በወቅቱ . . . ብሪታኒያ በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር። የገንዘቧ ዋጋም ሊጋሽብ አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር። ዓለም አቀፍ ኃያልነቷ ሊጠፋ እየተቃረበ ነበር" ሲሉ ማኮይ ጽፈዋል።

ተደጋጋሚ ጦርነቶች የነዳጅ ዋጋን ጨምረዋል

የፎቶው ባለመብት, Smith Collection/Gado/Getty Images

ነገር ግን የዚያን ወቅት የሱዩዝ ቀውስ ከዛሬው ግጭት ጋር ሙሉ በሙሉ ማመሳሰል ትክክል አይደለም ይላል ቦዌን።

"የአሜሪካን ኃያልነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከነበረችው ብሪታኒያ ጋር እያወዳደርኩ አይደለም። ሁሉም ኃያላን አገራት ግን ከፍ እና ዝቅ ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። ቻይና በማንሰራራት ላይ በምትገንበት ወቅት አሜሪካ ተመሳሳይ ነገር ከገጠማት ይህ በታሪክ ምሁራን እንደ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ሊጻፍ ይችላል።"

ሁኔታዎችን ለመረዳት በ70 ዓመታት ውስጥ ታሪክ የፈጠረውን ተጨማሪ ትምህርት መመልከት ጠቃሚ ነው።

የ1973 የነዳጅ ዋጋ

በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ የደም ስሮችን ማስተጓጎል በመቀጠሉ አካሄዱ ሊገመት የሚችል መሆኑን ታዛቢዎች ገልጸዋል።

አንደኛው ደግሞ የሱዊዝ ዘመቻ ከተጠናቀቀ ከ20 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተከሰተ ነው።

በአውሮፓውያኑ "1973 በእስራኤል፣ በግብፅ እና በሶሪያ መካከል ጦርነት ተካሂዷል። የዮም ኪፑር ጦርነት ተብሎ በሚጠራው በዚህ ጦርነት ግብፅ እና ሶሪያ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘሩ።

"አሜሪካም የጦር መሳሪያ ለእስራኤል በስፋት ሰጠች። የአረብ አገራት የዓለም የነዳጅ ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ የሚያደርግ እና በምዕራብ አውሮፓ ብዙ ጉዳት የሚያስከትል ማዕቀብ በመጣል ተቃውመዋል" ይላል ቦዌን።

የወቅቱ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ሚኒስትር ሼክ አህመድ ዛኪ ያማኒ እንደ ነዳጅ ያሉ ሃብቶች በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሳሪያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።

የአረብ ዓለምን ከፍተኛ ምርት "የነዳጅ የጦር መሳሪያ" ሲሉ ገልጸውታል፤ ይህም የዓለም ኢኮኖሚን በፍጥነት "ሊያወድም" ይችላል ብለዋል።

ማዕቀቡ ለአምስት ወራት ቢዘልቅም፣ ባለሙያዎች ግን ተጽዕኖው ለአስር ዓመታት ቀጥሏል። ለምሳሌ በአሜሪካ እና በነዳጅ ላይ በጣም ጥገኛ በሆኑት አገራት ላይ የዋጋ ግሽበት አስከትሏል።

ታንኮች

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive/Getty Images

ምንም እንኳን ነዳጅ ከ50 ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የበላይነት አሁን አብሮት የለም።

ዓለም አቀፍ የነዳጅ ፍላጎት ከመቀነሱም በላይ በተለይም ምዕራቡ ዓለም አማራጭ የኃይል ምንጮችን በመጠቀም ላይ ይገኛል። ሆኖም በ1973 እና ከዚያ በኋላ የተከሰቱት ሁኔታዎች ለትራምፕ ቁልፍ ትምህርትን ይሰጣሉ።

አሜሪካ አሁን ከውጪ ከምታስገባው በላይ ነዳጅ በራሷ ብታመርትም አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው ድፍድፍ ነዳጅ ከውጭ ታስገባለች። በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፍ ገበያ ለሚወሰነው የነዳጅ ዋጋ ተጋላጭ ናት። ይህ ደግሞ የአሜሪካዊያንን ሸማቾች ኑሮ ይጎዳል።

በተጨማሪም አገሪቱ በእስያ ባሉ ቁልፍ የንግድ አጋሮቿ ምክንያት በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ሊያድርባት ይችላል።

"አሁን እየሆነ ያለው ነገር ሳዑዲ እና ኤምሬትስን የመሳሰሉት አገራት ነዳጃቸውን በአውሮፓ ላሉ ደንበኞቻቸው እንደማይሸጡ መግለጻቸው አይደለም። ነገር ግን ኢራን እና ሁቲዎች ወደ ገበያ ለማድረስ የሚደረጉትን ጉዞዎች በጣም አስቸጋሪ እያደረጉት ነው። ነዳጅ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህንን አቅርቦት ካቋረጡት በርካታ ዓለም አቀፍ ችግሮች ይከሰታሉ" ይላል ቦዌን።

የኢራን-ኢራቅ ጦርነት

የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ውስጥ ተከናወነው የኢራን እና የኢራቅ ጦርነት፤ የዋሽንግተን ጠላቶች ወሳኝ የኢኮኖሚ መስመሮችን እንዴት ማገድ እንደሚችሉ በማሳየት ለትራምፕ ትምህርት የሚሰጡ የቅርብ ጊዜ ታሪካዊ ምሳሌዎች ናቸው።

በዚያ ጦርነት ወቅት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚጓዙ መርከቦች በቴህራን እና በባግዳድ ዒላማ ተደርገው ነበር። ይህም ዓለም አቀፍ ኃይሎችን ወደ ጦርነቱ ለመሳብ የታለመ እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ጥቃቶቹ በጣም ከባድ ስለነበሩ ኩዌት መርከቦቿን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ እርዳታ ጠየቀች። በቀዝቃዛው ጦርንት ባላንጣዋ ሩሲያ ላላመቀደም በሚል ዋሽንግተን ተስማማች።

መርከቦች በባሕር ላይ አየቀዘፉ

የፎቶው ባለመብት, Barry Iverson/Getty Images

ዘመቻ 'ኧርነስት ዊል' ተብሎ በተሰየመው ስምምነት መርከቦችን በአጃቢ የማንቀሳቀስ ሥራ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 1987 ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ብሪጅተን የተሰኘችው እና በአጃቢነት የተመደበችው መርከብ በኢራን መመታቷ ለአሜሪካ ትልቅ ውርደት ሆነ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ክስተት ዋሽንግተን ባሕር ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎችን የማስገድ ችሎታዋ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

ትራምፕ ከኢራን ጋር በሚደረገው በአሁኑ ጦርነት ሌሎች አገራት የባሕር ኃይል አጃቢዎችን በማቅረብ የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት እንዲሆን ድጋፍ አንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸው መልዕክቱን ግልጽ ያደርገዋል።

በአሁኑ ወቅት የዋሽንግተን ፈተና የበለጠ ከባድ ነው ይላሉ ተንታኞች። የጦር መሳሪያዎች መሻሻል፣ ለምሳሌ የድሮኖችን መስፋፋት እና ኢራን ከኢራቅ ጋር የረዥም ጊዜ ጦርነት ውስጥ አለመሆኗን ይጠቅሳሉ።

በአሁኑ ጦርነት ውስጥ ለተሳተፉ ዋና ዋና ተዋናንዮች በሙሉ ታሪክ ብዙ ትምህርትን ይሰጣል። ይህንንም የሚገነዘቡበት መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ለውጥ እና የጦርነት ጊዜ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።