የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ላለመውረድ ክስ መሠረቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በፓርላማ የወጣ እና የሕዝብ ተወካዮች ከሥልጣን እንዲያነሷቸው የሚያደርገውን ሂደት ለመቀልበስ ሕጋዊ ተቃውሞ ጀመሩ።

እ.አ.አ በ2022 አንድ ገለልተኛ ኮሚቴ ራማፎሳ በእርሻቸው ውስጥ ሶፋ ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ገንዘብ ከስርቆት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ከባድ የአስተዳደር ጉድለት ፈፅመው ሊሆን ይችላሉ ሲል አስታውቆ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ግን ምንም የተሳሳተ ተግባር እንዳልፈፀሙ አስተባብለዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከአራት ዓመት በፊት ፓርላማው ከሪፖርቱ በኋላ ከሥልጣን የማውረድ ምርመራ እንዲጀመር የሰጠው ድምፅ የሕግ ጥሰት እንዳለበት አስታውቋል።

ይህ የፓርላማ ድምፅ ሲሰጥ የራማፎሳ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ነበረው።

ነገር ግን በ2024 ጠቅላላ ምርጫ አብላጫነቱን ካጣ በኋላ የጥምር መንግሥት አካል ሆኖ እያስተዳደረ ነው።

ራማፎሳ ማክሰኞ ዕለት በኬፕ ታውን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስገቡት የሕግ መቃወሚያ ሪፖርቱን የሰራው ቡድን "ኃላፊነቱን በትክክል አልተረዳም፣ የቀረቡለትን መረጃ አላገናዘበም እና በእኔ ላይ አራት ክሶችን በተሳሳተ መንገድ አቅርቧል" ብለዋል።

ክሶቹ ሕገ መንግሥቱን መጥለፍ እና ከባድ የስህተት ተግባር እንደተፈጸሙ ያካትታሉ።

"ይህን ማመልከቻ ቀላል አድርጌ አላቀርበውም" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በፍርድ ቤት ማመልከቻቸው ጠቅሰው፤ ሪፖርቱ ወደ ጎን እንዲባል እና ከሥልጣን የማንሳት ሂደቱ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል።

የፓርላማው አፈ ጉባኤ የጥምር መንግሥቱ መሪ የሆነው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን ጨምሮ ከ16 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 31 አባላት ያሉበት ከሥልጣን የማስወገድ ኮሚቴ መስርተዋል።

ኮሚቴው ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን የማስወገድ ሂደት መጀመር ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ይወስናል።

በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን "የእርሻ ቅሌት" ተብሎ የሚጠራው ድርጊቱ እ.አ.አ በ2020 በሰሜን ሊምፖፖ ግዛት ከሚገኘው የራማፎሳ እርሻ 580 ሺህ ዶላር ተሰርቆ ተገኝቷል።

ከሁለት ዓመት በኋላ ገለልተኛው ኮሚቴ ፕሬዝዳንቱ ቃለ መሀላቸውን መጣሳቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ያገኘ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ መልስ መስጠት አለባቸው ብሎ ነበር።

ደቡብ አፍሪካ የውጭ ምንዛሬ መያዝ ላይ ጠንካራ ሕጎች ያሏት ሲሆን፤ ሕጎች የውጭ አገር ገንዘቦች በ30 ቀናት ውስጥ በባንክ እንዲመዝገቡ ያስገድዳሉ።

በወቅቱ ራማፎሳ ገንዘቡ ከእርሻ ንግድ በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ነው ብለው ነበር።