ቀጥታ, የኢራን እና አሜሪካ ልዑካን ከተጠባቂው ድርድር አስቀድሞ ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በተናጠል ተነጋገሩ

በአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው የዋሽንግተን ልዑክ እና በኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ የሚመራው የቴህራን ተደራዳሪ ቡድን ለተጠባቂው ንግግር ፓኪስታን ገብተዋል። የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች ንግግሩን እያመቻቹ ያሉትን የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር በተናጠል አግኝተው አነጋግረዋል። የሁለቱም አገራት ተደራዳሪዎች በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ ቢገኙም፤ አሁንም ድረስ ኢራን ያስቀመጠቻቸው ቅደመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ እንደማትሳተፍ እየገለጸች ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ ለመጫን እየመጡ ነው አሉ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከልጃቸው ኤሪክ ጋር ከዋይት ሀውስ ሲወጡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከልጃቸው ኤሪክ ጋር ከዋይት ሀውስ ሲወጡ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እና ሙሉ በሙሉ ባዶ የሆኑ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ እና ጋዝ ለመጫን እየመጡ አሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ ወደ አሜሪካ እየተጓዙ ያሉት “እጅግ ከፍተኛ ቁጥር” ያላቸው ባዶ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

    “በዓለም የትኛውም ቦታ ከሚገኘው [ነዳጅ] ምርጥ እና ‘ጣፋጭ’ የሆነውን የነዳጅ ዘይት (እና ጋዝ!)” ይጭናሉ ሲሉም ተናግረዋል።

    አሜሪካ “ቀጣዮቹ ሁለት ትላልቅ የነዳጅ ባለቤት አገራት ተደምረው ካላቸው በላይ የሆነ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ አላት” በማለት ጽፈዋል። “እየጠበቅናችሁ ነው” ሲሉም አክለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በጦርነቱ ምክንያት ለተቃወሰው የነዳጅ አቅርቦት መፍትሔ የሚመስሉ ዜናዎች ሲሰሙ ደግሞ ዋጋው ሲቀነስ ተስተውሏል።

    የነዳጅ ዋጋን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውለው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ ቤርሜል ዋጋው በሳምንቱ መጀመሪያ ከነበረበት 111 ዶላር በ15 በመቶ በመቀነስ 92 ዶላር ገብቷል።

    የነዳጅ ዋጋ የቀነሰው የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን የሚያካትተው የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም በመደረጉ ነው።

    ኢራን ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ መዝጋቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ የጨመረ ሲሆን ይህ ጭማሪም የምግብ ዋጋን አንሯል።

    በዚህ ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ ቢታይም አሁንም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር ከፍተኛ ነው። ከኢራን ጦርነት በፊት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 70 ዶላር ገደማ ነበር።

  2. አሜሪካ የያዘቻቸውን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣናት አስተባበሉ

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ

    አሜሪካ ለዓመታት እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው የቆዩትን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣን ማስተባበላቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አንድ ኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን አሜሪካ የቴህራን ሀብቶችን የመልቀቅ እርምጃ መውሰዷ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

    እንደ ምንጩ ገለጻ ሀብቱን የመልቀቅ እርምጃው “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን ደኅንነት ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ” ነው።

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍም ድርድር ከመጀመሩ በፊት ሀብቶቹ መለቀቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ጉዳዩን ለደጋፊዎቻቸው ለማብራራ ችግር ይገጥማቸዋል።

    ዘገባው ከወጣ በኋላ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ምላሽ የሰጡ የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ግን ጉዳዩን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዲለቀቀ ያልፈቀደው 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢራን ሀብት እንደያዘች የገለጸችው ኳታርም ማስተባበሏል በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

  3. የሄዝቦላህ ባለሥልጣን ከእስራኤል ጋር ንግግር የሚያደርገውን የሊባኖስ መንግሥት ወቀሱ

    ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የሄዝቦላህ አባል የሆኑት ሕግ አውጪው ሀሰን ፋድላላህ ከእስራኤል ጋር ንግግር ሊያደርግ ተዘጋጀው የሊባኖስ መንግሥት ላይ ወቀሳ አቀረቡ።

    ሕግ አውጪው አስተያየት የሰጡት፤ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ንግግር እንደሚካሄድ ካስታወቁ በኋላ ነው።

    እስራኤል በበኩሏ ከሊባኖስ ጋር በምታደርገው የተኩስ አቁም ንግግር ውስጥ ሄዝቦላህ እንደማይሳተፍ ገልጻለች።

    ሕግ አውጪው ፋድላላህ በሄዝቦላህ በሚተዳደረው አል ማናር ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በወጣው መግለጫቸው፤ የአገሪቱን መንግሥት እርምጃ “ግልጽ የሕገ መንግሥት እና የሊባኖስ ሕግጋት ጥሰት” ሲሉ ጠርተውታል።

    ድርድሩ በሊባኖስ ያለውን “የአገር ውስጥ ክፍፍል ያባብሰዋል” ሲሉም ተችተዋል።

    አክለውም፤ "ጠላት በውጊያ ሜዳ ሊያሳካ ያልቻለውን ነገር... የውሳኔ ሰጪነት አቅም በሌለው፣ መሠረታዊ ግዴታዎቹን በዘነጋ፣ ሕዝቡን መጠበቅ በተሳነው እና የሀገርን ሉዓላዊነት ያስከብራል ተብሎ ሊታመን በማይችል አካል በኩል በሚደረግ ድርድር አያገኘውም” ብለዋል።

  4. የኢራን ባለ 10 ነጥብ እቅድ - ተደራዳሪዎች ማሳካት የሚፈልጉት ምንድነው?

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ (መሐል) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ (ግራ) ከድርድሩ አስቀድሞ ፓኪስታን ገብተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Iranian Foreign Ministry/EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ (መሐል) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ (ግራ) ከድርድሩ አስቀድሞ ፓኪስታን ገብተዋል

    ለዛሬው ድርድር ቀጠሮ ከመያዙ አስቀድሞ ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ድርድር ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ተዘግቶ በከረመው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች ለማለፍ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጾ ነበር።

    ኢራን በበኩሏ የራሷን ባለ 10 ነጥብ የድርድር እቅድ አቅርባለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "እቅዱ ለድርድር መነሻነት ሊያገለግል ይችላል" ብለዋል።

    በዚህ የኢራን እቅድ እና አሜሪካ ባቀረበችው ባለ 15 ነጥብ መደራደሪያ ውስጥ ምን ጉዳዮች እንደተካተቱ የሚገልጹ የተለያዩ ዘገባዎች ቢወጡም እስካሁን ድረስ የእቅዶቹ ይዘት በይፋ አልተገለጸም።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በቴህራን እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በቀጣናው የሚደረግ ጦርነት በሙሉ እንዲቆም የሚጠይቀው ነጥብ ይገኝበታል።

    ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲሰጥ እንዲሁም በአሜሪካ የተያዙት የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶች እንዲለቀቁ ተጠይቋል። በጦርነቱ ኢራን ላይ ለደረሰው ጉዳት “መልሶ ግንባታ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን ሙሉ የካሳ ከፍያ” እንዲፈጸም የሚለውም ቴህራን ባቀረበችው እቅድ ውስጥ ተካትቷል።

  5. የኢራን እና አሜሪካ ተደራዳሪዎች ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ

    የአሜሪካውን ልዑክ የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ እና የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Pakistan Prime Minister's Office

    የኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናት እየተጠበቀ ካለው ድርድር አስቀድሞ ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ጋር ተገናኙ።

    የአሜሪካውን ልዑክ የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍን ማግኘታቸው ተገልጿል።

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቫንስን ከማግኘታቸው አስቀድሞ ከኢራን ተደራዳሪዎች ጋር ለምሳ መገናኘታቸውን የአገሪቱ መንግሥት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት የፓኪስታኑን መሪ ያገኙት ከልዩ መልዕክተኛው ስቲክ ዊትኮፍ እና ከትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ጋር መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ፤ ይህ ንግግር በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መወጣጫ ደረጃ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸው ጽሕፈት ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በምን መልኩ እንደሚካሄድ እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ይገናኙ እንደሆን ማወቅ አስቸጋሪ ነው።

    ከዚህ ቀደም እንደተደረጉ ድርድሮች ሁሉ ፓኪስታን በሰላም እቅዱ ላይ ለውጥ ይኖር እንደሆን ለማየት አንዴ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቀጥሎ ደግሞ የኢራን ልዑክ ወደሚገኙባቸው ክፍሎች እየገባች ልታደራድር ትችላለች።

    የኢራንን ተደራዳሪ ልዑክ የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ የኢራንን ሀብት ለመልቀቅ መስማማት አለባት ብለዋል።

    የቴህራን ሀብት ስለመለቀቁ የሚጠቁሙ የኢራን ሪፖርቶች አሉ። ሆኖም ትክክለኛነቱ ከአሜሪካ በኩል እስካሁን አልተረጋገጠም። እናም ደግሞ ጉዳዩ በአሜሪካ ለሚገኘው የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ እሾሃማ እንደሚሆን ይጠበቃል።

    ኢራን ለአሜሪካ ባቀረበችው ባለ 10 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ላይ የተያዙ የቴህራን ገንዘቦች እና ሀብቶች እንዲለቀቁ የሚጠይቀው ነጥብ ይገኝበታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢስላማባድ የሚገኙ የኢራን ጋዜጠኞች የቴህራን ቅድመ ሁኔታዎች የማይሟሉ ከሆነ ድርድሩ እንደሚሰረዝ እየተናገሩ ነው።

    የኢራን ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ወኪል የሆነች ጋዜጠኛ የኢራንን ጥቅም፣ ጥያቄ እና ቀይ መስመሮች ከማያስከብር ድርድር መውጣት በራሱ “ስኬት ነው” ብላለች።

  6. በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄዎች

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እስላማባድ ሲገቡ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበቀ ነው። ነገር ግን ስለ ድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች በቂ መረጃ አልወጣም።

    የአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪ ልዑካን በኢስላማባድ የፓኪስታን ባለሥልጣናትን ለማግኘት በተቃረቡበት በአሁኑ ሰዓት አራት ቁልፍ ጥያቄዎችን እንመልከት።

    በንግግሩ ማን ይሳተፋል?

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አማች ከሆኑት ልዩ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በመሆን ከኢራን ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ ገብተዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ቁልፍ የኢራን መንግሥት ባለሥልጣን ሆነው ብቅ ያሉት የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከንግግሩ ቀደም ብለው ማምሻውን ኢስላማባድ ደርሰዋል።

    የፓኪስታን ሚና ምንድን ነው?

    ሁለቱም ወገኖች በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር እና በአገሪቱ የወታደራዊ አዛዥ አሲም ሙኒር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

    ፓኪስታን በሁለቱ ተፋላሚ አገራት መካከል ቁልፍ አደራዳሪ ሆናለች። ከወዲሁ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስም ሚና ተጫውታለች።

    ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

    በአጭሩ ለመመለስ ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ግልፅ አይደለም። ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ቁርኝነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ንግግሩ አንድ ቀን ምን አልባትም እስከ ቅዳሜ ምሽት እንደሚካሄድ ዘግቧል።

    የሚጠበቁ ቁልፍ የንግግሩ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

    የድርድሩ ዋነኛ ነጥቦች፤ ኢራን በመዳፏ የጠረነፈችው የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ በሊባኖስ የቀጠለው ግጭት እና ኢራን ያከማቸችው የበለፀገ ዩራኒየምን ያካትታል።

  7. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢራን ድርድር ፓኪስታን ገቡ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን ባለሥልጣናት አቀባበል ሲደረግላቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና ተደራዳሪ ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ድርድር ከልዑክ ቡድናቸው ጋር ፓኪስታን ገቡ።

    ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ጋር ኢስላማባድ ከተማ የገቡት ቫንስ ከሰዓታት በኋላ በሚጀምረው የንግግር ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    ለአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት አቀባበል ያደረጉት የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐማድ ኢሻቅ ዳር ዋሽንግተን ለዘላቂ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

    ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ እና ኢራን “ገንቢ በሆነ መልኩ ተሳትፎ ያደርጋሉ” የሚል ተስፋቸውን መግለጻቸውን የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ፓኪስታን ሁለቱም ወገኖች ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ያላትን ፍላጎት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

    ጄዲ ቫን ወደ ፓኪስታን ከመጓዛቸው በፊት ባደረጉት ንግግር “ድርድሩ እንዲካሄድ እየጠበቁ” እንደሆነ ገልጸው፤ ነገር ግን ኢራን “ለመጫወት እንዳትሞክር” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራኑን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው “ቀና ፍላጎት አለን፤ ነገር ግን እምነታችንን አንጥልም” ሲሉ ፓኪስታን ከደረሱ በኋላ መናገራቸውን የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

    “ከአሜሪካውያን ጋር በነበረን የድርድር ልምድ ሁልጊዜም ሲያጋጥመን የነበረው ክሽፈት እና የቃል ኪዳኖች መሰበር ነው” ብለዋል።

  8. አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ የደረሰባቸው ከፍተኛ እና አካል የሚያጎድል ጉዳት እንደሆነ ሮይተርስ ዘገበ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጠቅላይ መሪነት ሥልጣንን ከተረከቡ ወዲህ በአካል ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት ከደረሰባቸው የፊት እና የእግር ጉዳት እያገገሙ እንደሆነ በቅርባቸው ካሉ ምንጮች መስማቱን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው አዲሱ ጠቅላይ መሪ በጥቃቱ ፊታቸው እንደተበላሸ እና አንድ ወይም ሁለት እግሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ሦስት ምንጮች ተናግረዋል።

    ይህም ቢሆን ግን የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ከጉዳታቸው እያገገሙ እንደሆነ እና አዕምሯቸው ስል ሆኖ መቀጠሉን ምንጮቹ ገልጸዋል ተብሏል።

    በድምጽ በሚደረጉ የኦንላይን ስብስብሰባዎች ላይ እየተሳተፉ እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር እንደሚሄደው ድርድር ባሉ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

    በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት አባታቸውን ተክተው ወደ ሥልጣን የመጡት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ በዚሁ ዕለት የደረሰባቸው ጉዳት መጠን እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

    ከዚህ ቀደም የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ጥቅም ላይ የሚውልን ቃል በመጠቀም ያሉበት ሁኔታ ጠቁሞ ነበር።

    የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በበኩላቸው ኻሜኒ “መቁሰላቸውን እና አካል መጉደል ደርሶባቸው ሊሆን እንደሚችል” ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካ የስለላ መረጃ ግን ኻሜኒ እግራቸውን አጥተዋል ተብሎ እንደሚታመን ማሳየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ መናገራቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

  9. አሜሪካ እና ኢራን የሚያስማማቸውን መንገድ ያገኙ ይሆን?

    የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር የሚካሄድበት ፓኪስታን እስላማባድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፓኪስታን እስላማባድ በሚካሄደው የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ምን ውጤት ሊመጣ ይችላል የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

    ሁለቱም ወገኖች በይፋ የሚያወሩት ነገር እጅግ የተራራቀ እና የሚቀራረብ የማይመስል ነው።

    የዚህም ከፊል ምክንያቱ መሪዎች እና ተደራዳሪዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚያወሩት በቀጥታ አድማጫቸው ለሆነው የአገራቸው ሕዝብ ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን እያንዳንዳቸው የጦርነቱን አውድ ለመቅረፅ እየሞከሩ ነው። ማን ማንን ለምኖ ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንደቀረበ ምስል ለመሳል እየተሯሯጡ ናቸው።

    አሁንም ቢሆን ሁኔታዎችን ለማሻሻል ግን ተስፋ አለ። ቢያንስ ቢያንስ ጥርጣሬ ያሳደረውን የተኩስ አቁም ስምምነት መጠበቅ ይቻላል።

    ማስታወስ የሚያስገልገው ጉዳይ፤ አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው የካቲት እየተደራደሩ ሳለ ዋሽንግተን ጠረጴዛውን በመርገጥ ከእስራኤል ጋር ሆና ጦርነቱን ከፍታለች።

  10. የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን ሊያደርጉ ያቀዱትን የሰላም ንግግር በበጎ እንደሚቀበሉ ገልጸው፤ ሁለቱም ወገኖች “በቅን ልቦና" ወደ ድርድር እንዲገቡ አሳሰቡ።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ያደረጉት የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ደዣሬክ፤ ጉቴሬዝ “ሁሉም ወገኖች ይህንን የዲፕሎማሲ እድል በመያዝ ወደ ዘላቂ እና አጠቃላይ ስምምነት ለመድረስ በቅን ልቦና እንዲሳተፉ” መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

    ዋና ጸሐፊው፤ ንግግሩ ውጥረቱን “የማርገብ እና ወደ ግጭት እንዳይመለስ የመከላከል” እድል እንደሚሰጥም አስታውሰዋል።

    “ዋና ጸሐፊው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ተጨባጭ አማራጭ እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ደዣሬክ ተናግረዋል።

    የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የግል ልዑክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለማገዝ ቀጣናው ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።

  11. የኢራን ተደራዳሪዎች ፓኪስታን ደርሰዋል፤ የአሜሪካ ልዑክም ወደ አገሪቱ እያመራ ነው

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images/EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ

    በኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ የሚመራው የቴህራን ተደራደሪ ቡድን ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ንግግር ፓኪስታን መድረሱን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው የዋሽንግተን ልዑክም ወደ ዋና ከተማዋ ኢስላማባድ ጉዞ ጀምሯል።

    ከ40 ቀናት ውጊያ በኋላ ተኩስ አቁም ላይ ደረሱት አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ፓኪስታን ውስጥ ለድርድር ይቀመጣሉ። የኢራን ልዑክ ለድርድሩ ከተያዘው ጊዜ አስቀድሞ ፓኪስታን ደርሷል።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚመለክተው ተደራዳሪ ቡድን ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ፣ የመከላከያ ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ አክባር አህማዲና፣ የማዕከላዊ ባምክ ገዢው አብዶልናስር ሄማቲ እንዲሁም በርካታ የፓርላማ አባላት ተካትተዋል።

    ልዑኩ የሚመራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢራን መንግሥት ውስጥ ጎልተው እየወጡ ባሉት አፈ ጉባኤው ጋሊባፍ እንደሆነ ተገልጿል። አፈ ጉባኤው ቡድኑን እየመሩ ቢሆንም ባለፉት ቀናት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሯቸው ጽሑፎች አሜሪካ ወደ ንግግር የማምራቷ ጉዳይ ላይ ኢራን ያላትን ጥርጣሬ ሲገልጹ ነበር።

    ሌላኛው ቡድኑ አባል አባል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ናቸው። አራግቺ በአውሮፓውያኑ 2015 ተደርሶ የነበረው የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

    በአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው ልዑክም በተመሳሳይ ወደ ፓኪስታን ጉዞውን ጀምሯል። በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አማካሪያቸው የነበረው የልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ የተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ናቸው።

    ኩሽነር እና ዊትኮፍ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ሲካሄዱ በነበሩ ድርድሮች ላይም አሜሪካን ወክለው ሲነጋገሩ ነበር። የጋዛ ጦርነት እንዲቆም ባደረገው የተኩስ አቁም እንዲሁም በሩሲያ እና ዩክሬን ድርድሮች ላይም ተሳትፈዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢራናውያን በጥሩ ልቦና ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆኑ ያለጥርጥር እጃችንን ከፍተን እንዘረጋለን” ብለዋል።

    አክለውም ግን “ሊጫወቱብን የሚሞክሩ ከሆነ ግን ተደራደሪ ቡድኑ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ ያገኙታል” ሲሉ አሳስበዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአሜሪካው ተደራደሪ ቡድን “ግልጽ መመሪያዎችን” መስጠታቸውንም ጠቅሰዋል።

  12. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርድሩ ካልተሳካ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከኢራን ጋር ፓኪስታን ውስጥ ቅዳሜ የሚጀመረው ድርድር የማይሳካ ከሆነ ለቀጣይ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የሰላም ንግግሩ የማይሳካ ከሆነ በሚል አሜሪካ የጦር መርከቦቿን “ምርጥ የተባሉ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቀች ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ኒው ዮርክ ፖስት ከተባለው ጋዜጣ በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት የድርድሩን ውጤት “በ24 ሰዓታት ውስጥ የምናውቅ ይሆናል” ብለዋል።

    “መርከቦቻችንን በታሪክ ውስጥ ከተሠሩት ሁሉ የላቁ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቅን ነው፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ከተጠቀምበንት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የበለጠ ነው።

    "እናም ከስምምነት ላይ ካልደረስን እነዚህን የጦር መሳሪያዎች በጣም ውጤታማ በመሆነ መንገድ እንጠቀማቸዋለን” ሲሉ ፕሬዝዳቱ አክለዋል።

    ኢራናውያንን በተመለከተም “የሚናገሩት እውነታቸውን ይሁን አይሁን ማወቅ የሚቻሉ ሕዝቦች አይደሉም" በማለት ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።

    ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም አሜሪካ እና ኢራን ከደረሱ በኋላ ፓኪስታን ውስጥ የመጀመሪያውን ድርድር ቅዳሜ ዕለት ይጀምራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራናውያን ”ዓለም አቀፍ የባሕር መተላለፊያዎችን በኃይል በመዝጋት ለማስገደድ ካሆነ ሌላ አማራጭ የላቸውም" ሲሉ ጽፈዋል።

    አሁንም "በሕይወት ለመቆየታቸው ብቸኛው ምክንያት ለመደራደር ነው” በማለት ከስምነምት ላይ ከመድረስ ውጪ ምንም ማድረግ አይችሉም ብለዋል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉበኤ ግን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሂደው ጥቃት ሳይቆም እና የታገዱ የኢራን ሀብቶች ሳይለቀቁ ድርድር አይኖርም የሚል ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።

  13. እስራኤል በሊባኖስ ተኩስ ሳታቆም ከአሜሪካ ጋር ደርድር እንደማትጀምር ኢራን አስታወቀች

    አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ነገ ቅዳሜ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማበድ ውስጥ ንግግር ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ውስጥ ተኩስ አቁም ሳይደረግ ድርድር እንደማይጀመር ኢራን ገለጸች።

    በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው አገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባጌር ጋሊባፍ እንዳሉት ከአሜሪካ ጋር የሚካሄደው ድርድር የሚጀመረው ሁለት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው።

    አፈ ጉባኤው ወሳኝ ያሏቸው የድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ጥቃት የሚያስቆም ተኩስ አቁም እና እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የኢራን ሀብት መለቀቅ ናቸው።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳሉት እነዚህ ሁለት እርምጃዎች አሜሪካ እና ኢራን ከሁሉ በፊት ተግባራዊ እንዲሆኑ የተስማሙባቸው መሆቸወውን አመልክተዋል።

    ሁለቱ ነጥቦች “ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሊፈጸሙ የሚገቡ ናቸው” በማለት ቅድመ ሁኔዎች መሆቸወውንም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እንደከፈቱ እስራኤል በሌላ በኩል የኢራን አጋር በሆነው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያካሄደች ሲሆን፣ ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላም ዘመቻዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

    በርካታ የኢራን ባለሥልጣናት በሊባኖስም ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ እንዲሆን እየጠየቁ ሲሆን፣ አሁን አፈ ጉባኤው የሰነዘሩት አስተያየት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገውን ድርድር እንዳያጨናግፈው ተሰግቷል።

  14. በኢራን ጥቃት ጉዳት የደረሰበት የሳዑዲ ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ ተዘጋ

    ጥቃት የተፈጸመበት የሳዑዲ ማጣሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ በጦርነቱ ምክንያት በደረሰበት ጉዳት መዘጋቱን የፈረንሳዩ ቶታል ኩባንያ አስታወቀ።

    የሳዑዲ አረቢያ ኤነርጂ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው የሳዑዲ መንግሥት ንብረት በሆነው አራምኮ እና በቶታል ሽርክና የሚሠራውን ማጣሪያ ጨምሮ ባለፉት ቀናት በነዳጅ ዘይት እና በጋዝ ማምረቻ ተቋማት ላይ “ተደጋጋሚ ጥቃቶች” ተፈጽመዋል ብሏል።

    ነገር ግን በማጣሪያው ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደደረሰ ወይም ሥራ መቆሙ በምርቱ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

    ቶታል እንዳስታወቀው ግን “ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ሌሊት ባጋጠሙት ጥቃቶች በማጣሪያው ሁለት ክፍሎች ላይ ጉዳት ሰርሷል።”

    ጥቃቱን ተከትሎ በደረሰው ጉዳት ላይ ምርመራ እየተደረገ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ሁለቱ ክፍሎች እንዲዘጉ ቢደረጉም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።

    የሳዑዲ የኤነርጂ ሚኒስቴር አንድ ባለሥልጣን ለአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪል እደንተናገሩተ ጥቃቶቹ “በቁልፍ የምርት ተቋማት ሥራዎች ላይ በርካታ መቋረጥን አስከትለዋል” ብለዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለሳምንታት ባደረገችው ጦርነት ውስጥ ሳዑዲን ጨምሮ በበርካታ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የነዳጅ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

  15. ኢራን በቅና ልቦና የምትደራደር ከሆነ አሜሪካ ለስምምነት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

    ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ

    ከኢራን ጋር ፓኪስታን ውስጥ በሚካሄደው ድርደር ላይ ለመሳተፍ ጉዞ ጀመሩት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢራናውያን በቀና ልቦና ለድርድር እንዲቀመጡ አሳሰቡ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ለጎዞ ወደ አውሮፕላን ከመግባታቸው በፊት በሰጡት ቃል ኢራናውያን ተደራዳሪዎች የማይሆን ሙከራ እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

    "ድርድሩን ለማካሄድ እየጠበቅን ነው” በማለት ኢራናውያን በቀና ልቦና የሚመጡ ከሆነ አሜሪካ “እጆቿን ዘርግ ታትቀበላቸዋለች” ብለዋል።

    ነገር ግን ኢራናውያኑ ተደራዳሪዎች “ሊያሞኙን የሚሞክሩ ከሆነ” አሜሪካ ይህንን የመቀበል ፍላጎት የላትም በማለት ከስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ንግግር ፕሬዝዳንት ትራምፕ የድርድር መመሪያዎችን እንደሰጧቸው አሳውቀዋል።

    ድርድሩ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ውስጥ ነገ ቅዳሜ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሊቬት አስታውቀዋል።

    አሜካንን በመወከል በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከፕሬዝንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር ጋር በመሆን ነው።

    የኢራን ተደራዳሪዎችም ፓኪስታን ይገባሉ ተብሎ እተጠበቀ መሆኑን በፓኪስታን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

  16. የኢራን ፓርላማ የአሜሪካ እና የእስራኤል መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ሊያግድ ነው

    ከተኩስ አቁሙ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ካለፉት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መካከል አንዱ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከተኩስ አቁሙ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ካለፉት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መካከል አንዱ

    በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚመረተው የነዳጅ ምርት የሚተላለፍበት ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር የሚያስችል ወሳኝ ዕቅድ የኢራን ፓርላማ አዘጋጅቶ በሚቀጥለው ሳምንት ድምጽ እንደሚሰጥበት ተነገረ።

    በዚህ ዕቅድ ውስጥ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በመተላለፊያው በኩል እንዳይጠቀሙ በዘላቂነት ዕገዳ የሚጥል ሃሳብ እንደተካተተበት ፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ያለውን ደኅንነት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚል በተዘጋጀው በአዲሱ ዕቅድ መሠረት በመርከቦች እንቅስቃሴ እና የሚገኝ ገቢን በተመለከተ ጉልህ ለውጥ እንደሚኖር የፓርላማው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮሚሽን ኃላፊ ተናግረዋል።

    ኃላፊው ለፋርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተዳደርበት አዲሱ አሠራርን የተመለከተው ዕቅድ በኢራን ፓርላማ “ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ተግባራዊ” ይሆናል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም የኢራን መንግሥት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚኖረውን ቁጥጥር እና የበላይነት ለማረጋገጥ በተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ ውስጥ አምስት ዋና ዋና ነጥቦች መካተታቸውን ኃላፊው ዘርዝረዋል።

    የጠላት መርከቦች እንዳይተላለፉ መከልከል፡ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው ነዳጅ ጫን መርከቦች በዘላቂነት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ይታገዳሉ።

    በወሽመጡ ከሚተላለፉ መርከቦች ክፍያ መሰብሰብ፡ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ለደኅንነታቸው እና ለሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ለሚያገኙት አገልግሎት ክፍያ ይጠበቅባቸዋል።

    የኢራን ገንዘብን ማጠናከር፡ የኢራን ገንዘብ የሆነውን ሪያል ለማጠናከር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚያልፉ መርከቦች የሚሰበሰቡት ሁሉም ክፍያዎች በኢራን ገንዘብ ብቻ ይሆናል።

    ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚለው ስም ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፡ ሁሉም በወሽመጡ የሚተላለፉ መርከቦች በሚኖራቸው የደብዳቤ ልውውጥ፣ በሚያዘጋጇቸው ሰነዶች እና የሬዲዮ መልዕክቶቻቸው ይፋዊውን እና ታሪካዊውን ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚለውን ስያሜ እንዲጠቀሙ ማድረግ።

    የሚሰበሰበው ገንዘብ አጠቃቀም፡ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚገኘው ገቢ ውስጥ 30 በመቶው የኢራን ወታደራዊ አቅምን ለማጠናከር ሲውል፣ 70 በመቶው ደግሞ የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት ለማሻሻል ይውላል።

    ለስድስት ሳምንታት በተካሄደው ጦርነት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ ፍጆታ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ችላለች።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር የደረሰችውን የተኩስ አቁም ተከትሎ ፓኪስታን ውስጥ በሚደረገው ድርድር የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።

  17. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆርሙዝ ጋር በተያያዘ ስለ ወታደራዊ አማራጮች መወያየታቸውን ገለጹ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, UK Pool

    በመካለኛው ምሥራቅ ጉዞ እያደረጉ ያሉት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ለማድረግ ስለሚያስፈልጉት ወታደራዊ አቅሞች እና ሎጂስቲክስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ።

    “በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ ዕቅድ ላይ እየሠራን ነው፤ ነገር ግን ወታደራዊ አማራጮች እና… በወሽመጡ በኩል መርከቦች ለማንቀሳቀስ [ስለሚያስፈልገው] ሎጂስቲክስ እየተመለከትን ነው” ማለታቸውን የዜና ወኪሎ ሮይተርስ ዘግቧል። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ “የአገራት ጥምረት” እንዲኖር እየሠሩ መሆኑንም አክለዋል።

    ትናንት ምሽት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያደረጉት “ውይይት ትኩረትም” ይህ ጉዳይ እንደነበር አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ መረጃዎችን አልሰጡም።

    ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ንግግር አሜሪካ ከኔቶ ልትወጣ ትችላለች ስለሚለው ስጋት አንስተው እንደሆነ የተጠየቁት ስታርመር፤ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጡም ጥምረቱ ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ ጥቅም የሚበጅ መሆኑን ገልጸዋል።

    "ኔቶ ላለፉት አስርት ዓመታት እኛ ከምናደርገው በላይ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደረገ የመከላከያ ጥምረት ነው” ብለዋል።

  18. ሊባኖስ በድርድሩ የምትሳተፈው ተኩስ አቁም ከተደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገለጸች

    ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሊባኖስ በሚቀጥለው ሳምንት ከእስራኤል ጋር ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር የምትሳተፈው ከንግግሩ በፊት ተኩስ አቁም ላይ ከተደረሰ ብቻ እንደሆነ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ አረጋገጠ።

    ባለፉት ቀናት የእስራኤልን ከፍተኛ ጥቃቶች ያስተናገደቸው ሊባኖስ በሚቀጥለው ሳምንት አሜሪካ ውስጥ ከቴል አቪቭ ጋር ንግግር እንደምታደርግ ተገልጾ ነበር።

    ሊባኖስ እና እስራኤል ቀጥተኛ ንግግር ማድረጋቸው ከዚህ በፊት ያልታየ ባይሆንም ያልተለመደ ነው። ብዙውን ጊዜ ሁለቱ አገራት የሚነጋገሩት እንደ አሜሪካ ባሉ በአሸማጋዮች አማካኝነት ነው።

    በትናትነው ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር ንግግር እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጸው፤ ተኩስ አቁም ግን እንደማይኖር አስታውቀዋል።

  19. ፓኪስታን እና ፈረንሳይ በሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት “ከፍተኛ የተኩስ አቁም ጥሰት” ነው አሉ

    በፓኪስታን እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው ድርድር በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ የሚገኙ መንግዶች ተዘግተዋል

    የፎቶው ባለመብት, PA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, በፓኪስታን እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው ድርድር በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ የሚገኙ መንግዶች ተዘግተዋል

    የፓኪስታን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሊባኖስ ውስጥ እየተፈጸመ ባለው “ከፍተኛ የተኩስ አቁም ጥሰት” የተሰማቸውን ስጋት ገለጹ።

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን ኖይል ባሮት ከፓኪስታን አቻቸው መሐማድ ኢሻቅ ዳር ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር፤ አገራቸው የፓኪስታንን የሰላም ጥረት እንደምትደገፍ አስታውቀዋል። ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ “በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት” ሊያመጣ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ “ሁለቱም መሪዎች በሊባኖስ እየተፈጠረ ያለውን ከፍተኛ የተኩስ አቁም በተመለከተ ስጋታቸውን ገልጸዋል” ብሏል።

    “የተኩስ አቁሙ በሙሉ በሙሉ መተግበር እና ስምምነቱን ማክበር ስላለው አስፈላጊነትም አጽንኦት” እንደሰጡ ገልጿል።

    የሁለቱ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይህንን ያሉት አሜሪካ እና ኢራን በመጪዎቹ ቀናት ፓኪስታን ውስጥ የሚያደርጉት የሰላም ንግግር እየተጠበቀ ባለበት ጊዜ ነው። ድርድሩ የመካሄዱ ጉዳይ ግን ጥርጣሬ እየተነሳበት ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድርድሩ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች “እስካሁን እንዳልተጠናቀቁ” ተናግሯል። በትናትናው ዕለት የኢራን ልዑክ ወደ የፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እንደደረሰ የተሰራጨው መረጃ ማስተባበያ ተሰጥቶበታል።

    ድርድሩ በእቅዱ መሠረት የመካሄዱ ነገር ላይ እርግጠኛ የሆነች የምትመስለው ፓኪስታን በበኩሏ ዝግጅት ማድረጓን ቀጥላበታለች። በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ የሚገኙ መንገዶች እንዲሁም የመንግሥት ሕንጻዎች እና ኤምባሲዎች ተዘግተዋል።

  20. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙ “በመጣሱ” በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

    የሄዝቦላህ ባንዲራ የያዙ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በሊባኖስ የሚገኘው የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድን ሄዝቦላህ፤ እስራኤል በአሜሪካ እና በኢራን ተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት “በመጣሷ” በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኝ ከተማ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።

    ሄዝቦላህ እንደገለጸው ሮኬቶችን የተኮሰው በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኘው ኪርያት ሽሞና እንዲሁም በሰሜናዊ እስራኤል ሚስጋቭ አም አካባቢ ነው።

    “እስራኤል እና አሜሪካ በአገራችን እና በሕዝባችን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እስከሚቆም ድረስ ይሄ ምላሽ ይቀጥላል” ብሏል።

    አሜሪካ እና ኢራን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስቆም የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደው ጥቃት ቀጥሏል። ኢራን እና አሸማጋይዋ ፓኪስታን የተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጸዋል። አሜሪካ እና እስራኤል በበኩላቸው ሊባኖስ የስምምነቱ አካል እንዳልሆነች እየተናገሩ ነው።

    እስራኤል የተኩስ አቁሙ በተደረሰ ማግሥት ረቡዕ ዕለት በከፈተችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቆስለዋል። እስራኤል አሁንም የደቡባዊ ሊባኖስን ሰፊ መሬት ተቆጣጥራ ይዛለች።

    የእስራኤሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ድርድር እንደሚደረግ ቢናገሩም፤ “ሊባኖስ ውስጥ ተኩስ አቁም አይኖርም” ሲሉ ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።