ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር በስልክ መነጋገር እንደሚመርጡ እና ተደራዳሪዎቻቸውን እንደማይልኩ ተናገሩ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሁለት ወር ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት ለመቋጨት ድርድር ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ በስልክ መነጋገር ትችላለች አሉ። ትራምፕ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ “መነጋገር ከፈለጉ፤ ማውራት እንችላለን። ሰዎችን ግን አንልክም” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራት ግብዣው ላይ ተኩስ ሲከፈት “አልሰጋሁም ነበር” አሉ

    የደኅንነት አባላት ትራምፕን ሲያስወጡ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቅዳሜ ምሽት ሲካሄድ በነበረው የጋዜጠኞች ራት ግብዣ ላይ የተከፈተው ተኩስ ፕሬዝዳንቱን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልታናትን ዒላማ በማድረግ እንደሆነ ቢታመንም ዶናልድ ትራምፕ በወቅቱ “ሰግተው እንዳልነበረ” ተናግረዋል።

    ትራምፕ ከሲቢኤስ ኒውስ ’60 ሚኒትስ’ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “አልሰጋሁም ነበር። ሕይወትን እረዳለሁ። የምንኖረው ያበደ ዓለም ውስጥ ነው” ብለዋል።

    የዋይት ሀውስ ዘጋቢ ጋዜጠኞች ራት ግብዣ ላይ የተፈጠረው ክስተት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ እንደተቃጣ ሦስተኛ የግድያ ሙከራ ተወስዷል። ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ፔንስልቬኒያ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ሰዓት እንዲሁም ባለፈው መስከረም ላይ በጎልፍ ክለባቸው ውስጥ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ በመጀመሪያ እንዲወጡ የተደረገበት የቅዳሜው ጥቃት እንዴት እንደተከሰተ ትራምፕ ተጠይቀዋል። ፕሬዝዳንቱ የሴክሬት ሰርቪስ አባላት ከክፍሉ እንዲያስወጧቸው ሁኔታዎች “ቀላል እንዳላደረጉ” በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    “ምን እንደተፈጠረ መመልከት ፈልጌ ነበር… ምን እየተካሄደ መሆኑን ማየት ፈልጌ ነበር። ሁኔታውን በተገነዘብኩበት ሰዓት፤ ምናልባትም መጥፎ ሁኔታ ነበር” ብለዋል።

    ከክፍሉ ሲወጡ “እንዲያጎነብሱ” ስለመደረጉ የተነሳላቸው ትራምፕ፤ “[ከደኅንነት አባላት ጋር] መራመድ ጀመርኩ። ዞርኩ፣ መራመድ ጀመርኩ፤ ከዚያም ‘እባክህ አጎንብስ፣ እባክህ ወደ ወለሉ አጎንብስ’ አሉኝ” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።

    “ስለዚህ አጎነበስኩ፤ ቀዳማዊት እመቤቷም አጎነበሰች” ሲሉም አክለዋል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ከተጠርጣሪው ኮል አለን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚታመን በእጅ የተጻፈ ሰነድን ተመልክቷል። ሰነዱ፤ “ከከፍተኛ ደረጃ እስከ ታች” ያሉ የትራምፕ አስተዳደር አባላትን ዒላማ ማድረግ እንደሚፈልግ ያሳያል።

    ጽሑፉ ላይ “የህጻናት ወሲብ ጥቃት ፈጻሚ፣ ደፋሪ እና ከሃዲ” በሚል ስለሰፈሩት አገላለጾች በቃለ መጠይቁ በተነሳበት ወቅት በትራምፕ እና በጋዜጠኛዋ ኖራህ ኦ’ዶኔል መካከል ውጥረት ተስተውሎ ነበር።

    ጋዜጠኛዋ ስለ እነዚህ አገላለጾች በመጠየቋ “ወራዳ” ሲሉ ጠርተዋታል። “ይህንን በማንበብሽ ልታፍሪ ይገባል፤ ምክንያቱም እኔ ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም አይደለሁም” ብለዋል።

  2. ኢራን ሆርሙዝ እንዲከፈት እና የኒውክሌር ንግግር እንዲዘገይ የሚጠይቅ እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧ ተዘገበ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እና ጦርነቱ እንዲቋጭ፤ የኒውክሌር ጉዳይ ግን በስምምነቱ ቀጣይ ደረጃ ንግግር እንዲደረግበት የሚጠይቅ የሰላም እቅድ ማቅረቧን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘገበ።

    አክሲዮስ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣንን እና ከጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው፤ ኢራን እቅዱን ያቀረበችው በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል ነው።

    እቅዱ በዋነኛነት የሚያተኩረው ከሁሉም በፊት በሆርሙዝ ወሽመጥ እና አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ በጣለችው እገዳ ምክንያት ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ ማበጀት ላይ ነው።

    በዚህም መሠረት የተኩስ አቁሙ ለረጅም ጊዜ እንዲራዘም ወይም ሁለቱ አገራት በቋሚነት ጦርነት ለማቆም እንዲስማሙ የሚጠይቅ ሀሳብ እቅዱ ውስጥ መካተቱን ዘገባው ጠቅሷል።

    በኢራን እቅድ መሠረት የኒውክሌር ድርድር የሚጀመረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተከፈተ እና የአሜሪካ እገድ ከተነሳ በኋላ ነው።

    ዋይት ሀውስ የኢራን እቅድ የደረሰው ሲሆን የትራምፕ አስተዳደር የኢራንን እቅድ ይመለከተው እንደሆነ አለመታወቁን አክሲዮስ ዘገቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ፓኪስታን ሲጓዙ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ንግግር በድጋሚ ይጀምራል የሚል ተስፋን ጭሮ ነበር። አራግቺ እንደተጠበቀው ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ባይነጋገሩም ስለ ሰላም ድርድር ማንሳታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

    አክሲዮስ እንዳስነበበው ከሆነ፤ አራግቺ በኢስላማባድ ቆይታቸው የኒውክሌር ጉዳይን ወደ ጎን የማድረግ ሀሳብን አንስተዋል።

    አክሲዮስ ያነጋገራቸው አንድ ምንጭ የአሜሪካ ጥያቄ የሚመለስበትን መንገድ በተመለከተ በኢራን አመራር መካከል ስምምነት አለመኖሩን አራግቺ ለፓኪስታን፣ ግብጽ፣ ቱርክ እና ኳታር አሸማጋዮች መናገራቸው ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር ለሚደረግ ድርድር ልዑካኖቻቸውን እንደማይልኩ እና በስልክ ንግግር ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

  3. እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 14 ሰዎች ተገደሉ

    ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል እሁድ ዕለት ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 14 ሰዎች ሲገደሉ፤ ሁለት ሕጻናት እና ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 37 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

    የደረሰው ጉዳት ከመገለጹ አስቀድሞ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በተለያዩ የደቡባዊ ሊባኖስ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲጡ አስጠንቅቀው ነበር።

    ነዋሪዎች በአፋጣኝ “መውጣት እንዳለባቸው” የሚያስጠነቅቅ መልዕክት የጻፈው ጦሩ፤ እዚያው መቆየት “ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥለው” ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ከቆይታ በኋላ የሄዝቦላህ ወታደሮች እና “የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም” ይውላሉ ያላቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራዎችን “በከባድ መሣሪያ እና የአየር ጥቃት” መምታቱን አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በፈጸመው ጥቃት የ19 ዓመት የእስራኤል ወታደር መገደሉን እና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውንም ገልጿል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ለሦስት ሳምንት የሚቆይ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት መስማማታቸው ይታወሳል።

    ይህ ስምምነት “በየትኛውም ጊዜ ራሷን ከታቀደ፣ አይቀሬ እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ የመውሰድ መብትን” ለእስራኤል ሰጥቷል።

    ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንስቶ እስራኤል እና ሄዝቦላህ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ ከስሰዋል።

    14 ሰዎችን ከገደለውን ጥቃት አስቀድሞ ቅዳሜ ዕለትም የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ “ወታደራዊ ይዞታዎች” ባላቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    ጦሩ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሁለት ፈንጂ የተሸከሙ ድሮኖችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል በሚል ነው።

    ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአገሪቱ ጦር ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ “የሄዝቦላህ ዒላማዎችን በኃይለኛው እንዲያጠቁ” ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዚሁ ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።

  4. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር በስልክ መነጋገር እንደሚመርጡ እና ተደራዳሪዎቻቸውን እንደማይልኩ ተናገሩ

    የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ጃሬድ ኩሽነር (ግራ) እና ስቲቭ ዊትኮፍ (ቀኝ) ቅዳሜ ዕለት ወደ ኢስላማባድ እንዲጓዙ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስቀድመው ከፓኪስታን ከወጡ በኋላ ጉዟቸው ተሰርዟል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ጃሬድ ኩሽነር (ግራ) እና ስቲቭ ዊትኮፍ (ቀኝ) ቅዳሜ ዕለት ወደ ኢስላማባድ እንዲጓዙ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስቀድመው ከፓኪስታን በመውጣታቸው ጉዞው ተሰርዟል

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሁለት ወር ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት የሚቋጭ ድርድር ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ በስልክ መነጋገር እንችላን አሉ።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ “መነጋገር ከፈለጉ፤ ማውራት እንችላለን። ሰዎችን ግን አንልክም” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ይህንን የተናገሩት አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ እንደጣለችው ገደብ ያሉ የስምምነት እንቅፋቶች እንዲወገዱ ከጠየቀች በኋላ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ተደራዳሪዎቻቸው ስቲቭ ዋትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነርን ወደ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እንደሚልኩ ከተናገሩ በኋላ ሁለቱ አገራት በድጋሚ ድርድር ይጀምራሉ የሚል ተስፋ ጭሮ ነበር።

    አርብ ዕለት ፓኪስታን ገብተው የነበሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ ግን የአሜሪካኑ ልዑካን ከመድረሳቸው አስቀድሞ ወደ ኦማን ተጉዘዋል።

    ትናንት እሁድ ለአጭር ቆይታ ተመልሰው ወደ ፓኪስታን ተጉዘው የነበረ ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተደራዳሪዎቻቸውን የመላክ እቅዳቸውን አስቀድመው ሰርዘዋል።

    አራግቺ ከፓኪስታን ወጥተው ወደ ሩሲያ አምርተዋል። በዚያም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዚህ ቀደም ኢራን እና አሜሪካን ስታደራድር ወደ ነበረችው ኦማን ባደረጉት ቆይታ ስለ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ እንደተነጋገሩ ተገልጿል።

    ትራምፕ በፎክስ ቃለ መጠይቃቸው “መነጋገር ከፈለጉ ወደ እኛ መምጣት ወይም ሊደውሉልን ይችላሉ። ታውቃለህ፤ ቴሌፎን አለ። ጥሩ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ መስመር አለን” ሲሉ በድጋሚ ልዑካን እንደማይልኩ ጠቁመዋል።

    አክለውም፤ “ስምምነቱ ውስጥ ምን መኖር እንዳለበት ያውቃሉ። በጣም ቀላል ነው፤ የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራቸው አይችልም። ይህ ካልሆነ የምንገናኝበት ምክንያት አይኖርም” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ከቆይታ በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ማድረግ ያለባቸው መደወል ነው” በማለት ጽፈዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት የፓኪስታን የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል የተኩስ አቁም እንዲፈረም እየጣሩ ባሉበት ወቅት ነው።

    የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው አንድ የፓኪስታን ባለሥልጣን ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት እንዲቆይ የተስማሙት ተኩስ አቁም ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ቢጠናቀቀም፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውታል። ይህም የካቲት ላይ የተጀመረው ውጊያ እንዲገታ አድርጓል።

    በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት እና የዓለምን ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የከተተውን ጦርነት በዘላቂነት የሚቋጭ መፍትሔ ላይ ግን እስካሁን አልተደረሰም።