
የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው የአየር ድብደባ ሦስት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መግደሉን የሊባኖስ
ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዋሺንግተን በበኩሏ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በ45 ቀን መራዘሙን ይፋ አድርጋለች።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በሃሮፍ ከተማ የሚገኘው የሲቪል መከላከያ ማዕከል ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አራተኛው የሕክምና ባለሙያ
“ከፍተኛ ጉዳት” እንዳጋጠመው አስታውቋል።
አርብ ዕለት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል እና ሊባኖስ ለሁለት ቀናት በዋሺንግተን ድርድር ካደረጉ በኋላ የተኩስ
አቁሙን ለማራዘም መስማማታቸውን ገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚያዚያ 8 2018 ዓ.ም. በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን
ይፋ ቢያደርጉም ከሄዝቦላህ ጋር የሚደረገው ውጊያ ግን ቀጥሏል።
ረቡዕ ዕለት የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ስምንት ሕጻናትን ጨምሮ 22 ሰዎች
መገደላቸውን አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት “እነዚህ ንግግሮች በሁለቱ አገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጡ፣ ሁለቱም
አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት እንዲሁም የግዛት አንድነት እንደሚያከብሩ፣ እንዲሁም በሚጋሯቸው ድንበሮች አካባቢ ትክክለኛ ደህንነትን
እንደሚያሰፍኑ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በሰኔ ወር “የፖለቲካ ድርድሩን ለመቀጠል ዳግም እንገናኛለን” ሲል አስታውቋል።
ፒጎት አክለውም “በተጨማሪም ግንቦት 21 2018 ዓ.ም. አዲስ የደህንነት እና መከላከያ ውይይቶች በፔንታጎን ይጀመራሉ”
ብለዋል።
በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ይቼል ሌይተር ውይይቱ “ግልጽ እና ገንቢ” ነበር ብለዋል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከእስራኤል ጋር በሚደረጉ “ድርድሮቹ ያለንን ስፍራ ከፍ ለማድረግ የሁሉም የአረብ
እና ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ” ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
እስራኤል እና ሄዝቦላህ የሚያካሄዱትን ውግያ ተከትሎ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። አብዛኞቹ
ተፈናቃዮች ሄዝቦላህ ከሚቆጣጠራቸው ከደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል፣ ከምሥራቃዊ ቤካ ቫሊ እንዲሁም ከቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ዳሄህ ናቸው።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው የኢራን ጦርነት በተጀመረ በሁለተኛው ቀን የካቲት 23 2018 ዓ.ም.
ነው።
በወቅቱ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ያስወነጨፈ ሲሆን የእስራኤል ጦር በበኩሉ በደቡባዊ ሊባኖስ መጠነ ሰፊ የአየር
ጥቃት እና የምድር ጦር ዘመቻ ከፍቷል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በግጭቱ በሊባኖስ ብቻ ቢያንስ 2,896 ሰዎች ሲገደሉ 18 የእስራኤል
ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎችም ሞተዋል።