በፓሪስ ትምህርት ቤቶች የተንሰራፋው የታዳጊዎች ወሲባዊ ብዝበዛ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው።
ታዳጊ ተማሪዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም የተከሰሰ የትምህርት ቤት ሠራተኛ የፊታችን ሐሙስ በፓሪስ ፍርድ ቤት ይቀርባል።
በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ለአንድ ዓመት መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው።
ለተማሪዎች ድጋፍ ለመስጠት ከሚቀጠሩ መምህራን ያልሆኑ ሠራተኞች ላይ ከወሲባዊ ብዝበዛ ጋር የተያያዙ ክሶች ሲቀርቡ ቆይተዋል።
በፓሪስ 15,000 የሚደርሱ አጋዥ ሠራተኞች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያገለግላሉ።
አሁን ላይ መዋለ ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 100 በሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ምርመራ እየተካሄደ ነው።
አጋዥ ሠራተኞች ሥነ ምግባር በማጣት፣ ኃይል በመጠቀም እና ወሲባዊ ባህሪ በማሳየት ተከስሰዋል።
በቀጣይ ወራት ሦስት ክሶች ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሲሆን ተጨማሪ ክሶች እንደሚከፈቱም ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ፖሊስ ሦስት ትምህርት ቤቶች ላይ ፍተሻ አድርጎ 16 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ለልጆች ያልተገባ ወሲባዊ ባህሪ በማሳየት እንደሚከሰሱ ተገልጿል።
ከነገ በስትያ ፍርድ ቤት የሚቀርበው ግለሰብ በአልፎንሴ ቦውዲን ትምህርት ቤት አምስት ሕጻናትን ወሲባዊ በሆነ መንገድ በመንካት ተከስሷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2025 አካባቢ የአራት ዓመት ሴት ልጁ እንግዳ ባህሪ ማሳየት መጀመሯን አንድ ወላጅ ለቢቢሲ ገልጿል።
ሌላ ወላጅ ደግሞ ልጁ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰባት ተናግሯል።
"ባለቤቴ ልጃችንን ወደ መናፈሻ ወስዳ ትምህርት ቤት ሳለች ሰዎች ነክተዋት ከሆነ ጠየቀቻት። ልጃችንም 'አዎ ዴቪድ ይነካኛል፤ ያቅፈኛል' ስትል ተናገረች።"
ባለቤቱ ልጃቸው እንዴት እንደተነካች ስትጠይቃት "ጀርባዋን እንግዳ በሆነ መንገድ እየዳበሰች" እንዳሳየች አባቷ ገልጿል።
"ያንን ስናይ መጥፎ ነገር መከሰቱን አወቅን" ይላል።
እነዚህ ክሶች መሰማት ከጀመሩ በኋላ ታዳጊ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ስጋት ገብቷቸዋል።
የትምህርት ቤት አጋዥ ሠራተኞችን የሚቀጥረው የፓሪስ ማዘጋጃ ቤት የሚቀርቡለትን ክሶች ትኩረት ሰጥቶ እንዳልተመለከተ ወላጆች ይናገራሉ።

ኤስኦኤስ ፐሪስኮላሪዬ የተባለው ማኅበር እንደሚለው፤ የችግሩ መንስዔ ሙያዊ ብቃት ያላቸው አጋዥ ሠራተኞች አለመቀጠራቸው ነው። አብዛኞቹ የሚከፈላቸው አነስተኛ ደመወዝ ሲሆን፤ ልጆችን በመንከባከብ ረገድ መሠረታዊ ሥልጠና ብቻ እንደሚወስዱም ማኅበሩ ገልጿል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው አጋዥ ሠራተኞችን ለመቅጠር ሲባል የቅጥር ቅድመ ሁኔታዎች ችላ እንደሚባሉም አክሏል።
የማኅበሩ መሥራች ኤልዛቤት ጉትማን እንደተናገችው፤ አጋዥ ሠራተኞች በተማሪዎች ላይ መሳለቅ፣ ማንጓጠጥ እና ሌሎችም ነውረኛ ድርጊቶች ፈጽመዋል በሚል በወላጆች ይከሰሳሉ።
"በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠሩ አጋዥ ሠራተኞች የድብድብ ቡድን አደራጅተው ልጆችን እርስ በራሳቸው ያጋጥማሉ። ሌሎች ተማሪዎች ከበው 'በለው በለው' እያሉ ይጮሀሉ" ስትል ኤልዛቤት ምሳሌ ትሰጣለች።
የፓሪስ አዲሱ ከንቲባ ኢማኑኤል ግሪጎሬ፤ አጋዥ ሠራተኞች የሚቀጠሩበትን ሒደት ለማስተካከል 20 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አስታውቀዋል።
ገንዘቡ አጋዥ ሠራተኞችን ለማሠልጠን እና ለመከታተል እንደሚውል ተናግረዋል።
አጋዥ ሠራተኞች ላይ ማንኛውም ዓይነት ቅሬታ ከተሰማ ወዲያውኑ እንደሚባረሩ ከንቲባው ገልጸዋል።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት 80 ሠራተኞች ታግደዋል።
አብዛኞቹ አጋዥ ሠራተኞች በአጭር ኮንትራት ይቀጠራሉ። ተማሪዎችን በምሳ እረፍት ሰዓት እና ከትምህርት በኋላም ያግዛሉ።
ለተማሪዎች መዝናኛ እና ስፖርታዊ ክንውን ማዘጋጀት ከኃላፊነቶቻቸው መካከል ናቸው።
ክሶች መሰማት ከጀመሩ ወዲህ ሁሉም ሠራተኞች በጅምላ ተፈርጀው በጥርጣሬ እንደሚታዩ እና መገለል እንደደረሰባቸው የተናገሩ ሠራተኞችም አሉ።
ኤፍኦ ዩኒየን በተባለው ማኅበር የምትሠራው ካርላ ቦኔት "ወላጆች ሪፖርት ማድረግ አለባቸው፤ ግን ሁሉም ሪፖርት የሚደረግ ነገር ትክክል ነው ማለት አይደለም" ብላለች።
ለተማሪዎች አጋዥ ትምህርት የሚሰጠው ረሚ በበኩሉ የፓሪስ ማዘጋጃ ቤት "ገለልተኛ" እንዳልሆነ ይናገራል። ማዘጋጃ ቤቱ "ክሶችን አይመረምርም። እኛንም አይከላከልም። በአሁን ሰዓት ከልጆች ጋር በሚሠራበት ወቅት ማንኛውም ነገር ወደ ክስ ሊያመራ ይችላል" ሲልም አክሏል።
የወላጆች ማኅበር የሆነው ኤፍሲፒኢ አባል የሆነው ግሪጎሪ ኤንሰል "ሠራተኞች በአግባቡ አይከፈላቸውም፤ አይሠለጥኑም፤ ቁጥጥር አይደረግባቸውም" ብሏል።
"በቂ ገንዘብ አልተመደበም። ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ መውጣታቸው አይገርምም" ሲልም አክሏል።
ክሶች እየተሰሙ ያለው በፓሪስ ቢሆንም ችግሩ በመላው ፈረንሳይ የተንሰራፋ መሆኑን የመብት ተሟጋቾች ተናግረዋል።















