የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች አስቸጋሪ የሚሆኑ የኤአይ ሞዴሎችን ማጥፋት የሚያስችል ረቂቅ ሕግ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ሕግ አጪዎች የአገሪቱ መንግሥት ሕዝብን ስጋት ውስጥ የሚከት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መገልገያን በሚኖር ጊዜ በፍጥነት እንዲጠፋ ማዘዝ የሚያስችል ሥልጣን እንዲኖረው የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አዘጋጁ።
ዴሞክራቱ የኮንግረስ አባል ቴድ ሊዩ እና ሪፐብሊካኑ የኮንግረስ አባል ናታኒኤል ሞራን 'ኤአይ ኪል ስዊች አክት' የተባለ ረቂቅ ሕግ ሐሙስ ዕለት ይፋ አድርገዋል።
የኮንግረስ አባላቱ ይህንን ረቂቅ ያስተዋወቁት የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው ኦፕንኤአይ፤ ገና ይፋ ያላደረጋቸው የኤአይ ሞዴሎች "ከዚህ ቀደም ባልታየ" ሁኔታ ሌላ ኩባንያ ውስጥ ሰርገው በመግባት 'ሀክ' እንዳደረጉ ካመነ በኋላ ነው።
ዴሞክራቱ ሊዩ፤ የኤአይ ሥርዓቶች የሚጠፉበት አሰራር መዘርጋት እንዲሁም "ፌደራል መንግሥት አስቸጋሪ የኤአይ ሞዴሎችን ለመዝጋት የሚያስችለው ግልጽ ሥልጣን እና አሰራር" እንዲኖረው ማድረግ "አስፈላጊ" መሆኑን ተናግረዋል።
ሪፐብሊካኑ ሞራን በበኩላቸው፤ "ኤአይ እየተሻሻለ ነው የሚሄደው፤ እንዲያም መሆን አለበት ብለዋል። አክለውም ግን "መሪነት ማለት የሰው ልጅ በምንሰራው ቴክኖሎጂ ላይ የመቆጣጠር አቅም እንደሚኖረው ማረጋገጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ከመስራቾቹ አንዱ በሆነው ሳም አልትማን የሚመራው ኦፕንኤአይ ስለ ረቂቅ ሕጉ ወዲያውኑ አስተያየት አልሰጠም።
ከዚህ ቀደም ግን ኩባንያው በከፊል በመንግሥት ፖሊሲ አማካኝነት የኤአይ ቴክኖሎጂ በጥቅሉ "የሰው ልጅን በሙሉ የሚጠቅም" መሆኑን የማረጋገጥ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኤአይ ስርዓት ማጥፊያ እንዲበጅለት የሚጠይቀው ረቂቅ ሕግ፤ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት አንድ የግል ኩባንያ የኤአይ ሞዴል ወይም መገልገያን እንዲዘጋ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን እንዲኖረው ያደርጋል።
መሰል የኤአይ ቴክኖሎጂዎችን የሚሰሩ ኩባንያዎችም ሞዴሎቹን "የመገደብ፣ የማገድ ወይም የመዝጋት ቴክኒካዊ አቅማቸውን" እንዲያስጠብቁም ያዝዛል።
በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚሰሯቸውን የኤአይ ሞዴሎች እና መገልገያዎች ለአሜሪካ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለማሳየት እና እና ለማጋራት ተስማምተዋል። ነገር ግን በእንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ ጣልቃ የመግባት ወይም የኤአይ ሞዴሎችን የማጥፋት ሥልጣን የሚሰጥ አሰራር የለም።
በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ፤ ኤአይ ኩባንያዎች ስለሚያጋጥሟቸው የቴክኖሎጂ ክስተቶች ወይም ብልሽቶች ለመንግሥት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ያደርጋል። ይህ ዓይነት ክስተቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ "ከመጀመሪያ ደረጃ የማዘግየት እርምጃ እስከ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት" የሚደርስ የምላሽ ማዕቀፍም ለመንግሥት እንዲያቀርቡም ይጠይቃል።
ዴሞክራቱ የኮንግረስ አባል ሊዩ ባወጡት መግለጫ፣ የኤአይ ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ በሚደረገው ፉክክር ቁልፍ የኦፕንኤአይ ተቀናቃኝ የሆነውን አንትሮፒክን እና የኩባንያው መገልገያ በቅርቡ ያጋጠመውን ክስተት ጠቅሰዋል።
ኩባንያው የሰራቸው 'ሚቶስ' እና 'ፌብል' የተሰኙ ሞዴሎች ባላቸው የሳይበር ጥቃት የማድረስ አቅም ምክንያት ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆኑ በአሜሪካ ንግድ መስሪያ ቤት ታግደው እንደነበር አንስተዋል።
አንትሮፒል ስለ ጉዳዩ ወዲያውኑ አስተያየት አልሰጠም።
የአንትሮፒክ መስራቾች አንዱ የሆነው ጃክ ክላርክ ባለፈው ወር ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ላይ ኤአይን ማበልጸግ ሂደትን በተመለከተ ተጨማሪ የመንግሥት ፖሊሲ እንዲኖር እንደሚፈልግ ተናግሮ ነበር።
ዴሞክራቱ ሊዩ ባቀረቡት ረቂቅ ሕግ ላይ ኤአይ ለጥያቄዎች መልስ ከሚሰጥ ቴክኖሎጂነት ተሻግሮ እንደ "የፋይናንስ ግብይቶችን መፈጸም፣ የትራንስፖርት ሥርዓቶችን መቆጣጠር ወይም በሳይበር ጥቃትን መከላከል እና ማድረስ" ያሉ ድርጊቶችን የሚወስድ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎ፣ የአገሪቱ ሠራዊት "ለኤአይ ቅድሚያ የሚሰጥ" ተዋጊ ኃይል እየሆነ መምጣቱን በዚህ ዓመት አስታውቋል። ወደዚህ ደረጃ የተሸጋገረውም ከጉግል፣ ኦፕንኤአይ፣ አማዞን፣ ማይክሮሶፍት፣ ስፔስ ኤክስ፣ ኦራክል፣ ንቪዲያ እንዲሁም ሪፍሌክሽን ከተባለው አዲስ ኩባንያ ጋር በፈጸማቸው ስምምነቶች አማካኝነት መሆኑን ገልጿል።














